መውሊድ በሐበሻ ምድር

0
1482

ዛሬ፣ ጥቅምት 29/2012 የመውሊድ በዓል ነው፤ በእስልምና እምነት ተከታዮች የነብዩ መሐመድ ልደት የሚከበርበት ቀን። ይህን በዓል ስለማክበር በቁርዓንም ሆነ በነብዩ ትዕዛዝ የተባለ ነገር ባይኖርም ጥቂት የማይባሉ የእስልምና እምነት ተከታይ በብዛት ያለባቸው አገራት ያከብሩታል። በዓሉ ነብዩ “የሐበሾች ምድር” ብለው በጠሯት በኢትዮጵያ ደግሞ ከሌሎች አገራት በተለየ ትርጉም አለው።

ሐጂ አደም ከሚል ኢትዮጵያ በአረቡ ዓለምና በእስልምና ውስጥ ያላትን ታሪክ በስፋት አጥንተዋል። በዚህም ከሠላሳ በላይ ጥናቶችን ያከናወኑ ሲሆን ከጥናቶቻቸው መካከልም ሰባቱ የኅትመት ብርሃን አግኝተዋል።

በእስልምና ሃይማኖት አረፋ እና ኢድ እንዲከበር በቁርዓንና በነብዩም የታዘዘ መሆኑን ያወሳሉ። ይህ ማለት ስለ መውሊድ የመጣ ማስረጃ በዛ የለም ማለት ነው። መውሊድ መከበር የጀመረው ከነብዩ ህልፈት በኋላ በአራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

ታድያ እንዲከበር የታዘዘበት ዓላማ ነበረው። ሐጂ አደም ሲናገሩ፤ እስላማዊ ክልል ወደ ሰሜኑ የዓለም ክፍል ሲስፋፋና አዳዲስ አማኞች ሲቀላቀሉ አረብኛ ቋንቋ የማይችሉም ይገኙበት ነበር። ታድያ ይህንን ጉዳይ እነዚህ አማኞች በወቅቱ ኢራቅ ውስጥ የኩርድ ገዢ ለነበረ ንጉሥ ጥያቄ ያቀርባሉ።

ጥያቄው “ቁርዓን ባለቤት አግኝቶ ይተረጎማል፣ የነብዩን ሐዲሶችም የሚያዘጋጁ አሉ። ነገር ግን የነብዩን ታሪክ በተመለከተ አዲስ ገቢ ነንና ምንም ልናገኝ አልቻልንም” የሚል ነበር። እናም እሱን የሚያብራሩ እና የሚጽፉ ሊቃውንት መድቡልን ሲሉ ጠይቀዋል። ንጉሡም ከሊቃውንቱ መካከል አልሃፊዝ ቢን ዳሂያ የተባሉትን ጠርተው የአማኞቹን ጥያቄ መልስ የሚሰጡ መዛግብትን እንዲያዘጋጁ ይነገራቸዋል፤ እርሳቸውም አጥንተው ያቀርባሉ። በዚህም “ማብራሪያ የሚሰጥ የነብዩን ታሪክ የሚያስረዳ” የሚል መጽሐፍ ተዘጋጀ። ይህን ተከትሎ በአልሐፊዝ ኀላፊነት በየዓመቱ ሰዎችን እየሰበሰበ መውሊድን ማክበር ተጀመረ።

ታድያ የዚህ ዓላማ ኹለት ነው። አንደኛው የነብዩን ታሪክ ማሳወቅ ሲሆን ኹለተኛው የተቸገሩትን ማብላት ነው። ይህ ነገር እየተስፋፋ በሙስሊሙ አገር መከበር ጀመረ። ይህን ግን ብዙ አገራት እንዳልተቀበሉት ሐጂ አደም ይገልጻሉ። በተለይ እንደ ሳዑዲ ያሉ አገራት አልተቀበሉትም። በአንጻሩ እንደ ግብጽና ሞሮኮ ያሉ አገራት ደግሞ ሥራ ዘግተው መሪዎቻቸው ሳይቀር የሚሳተፉበት በዓል ሊሆን ችሏል።

መውሊድ በኢትዮጵያ
መውሊድ በኢትዮጵያ መከበር የጀመረበት ሦስት ምክንያት አለ። ይህም ቀሪው የመውሊድ አክባሪ እንዲያከብር ምክንያት ከሆነው ኹለት ጉዳይ ላይ አንድ ተጨምሮበት ነው። ሐጂ አደም እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ እንደ አገርና ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ለነብዩ የሰጠነው ስጦታ በመኖሩ ነው ብለዋል።

ታድያ መውሊድ እንደ አምልኮ የሚከበር በዓል እንዳይደለ ደጋግመው ይጠቅሳሉ። እንደሚታወቀው ነብዩ ከኢትዮጵያ ጋር የተለየ ግንኙነት ነበራቸው። በተለይም በነበሩበት የእስልምናን መሠረት ሲጥሉ፤ ከግራና ከቀኝ በተለያዩ ሰዎች ተወጥረው ነበር። በ613 ጥሪያቸውን እንዳወጁ ደግሞ ከፍተኛ ችግር ገጠማቸው። ይህም ጥሪ እንዳያስተላልፉና መሠረት እንዳይጥሉ ነው።

እናም ጥሪያቸውን የተቀበሉ ተከታዮቻቸው ችግር እንዳያጋጥማቸው ተሰድደው እንዲጠለሉ አሏቸው። ተከታዮቻቸውም የት እንሒድ ብለው በጠየቋቸው ጊዜ፣ ፍትሕና ሃቅ ወዳለበት ወደ ሐበሻ ምድር ሒዱ ይሏቸዋል፤ ያኔ 12 ውንዶችና 4 ሴቶች ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

ኢትዮጵያ ውስጥ እስልምና በ615 ነው የገባው፤ ከማንም አገር በፊት ነው። በዛም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ አይሁድን፣ ክርስትናን እንዲሁም እስልምናን ቀድማ የተቀበለች አገር መሆኗን ሐጂ አደም ይጠቅሳሉ። “እስልምናን ዓለም ዐቀፍ ጥሪ በመቀበል ከመዲና በ7 ዓመት እንቀድማለን፤ ከሶርያና ኢራቅ 18 ዓመት፣ ከፍልስጤም በ21 ዓመት፣ ከግብጽ በ24 ዓመት፣ ከሞሮኮና አልጀርስ በ27 ዓመት፣ ከሱዳን በ36 ዓመት፤ ከቱርክና ኢራን በ76 ዓመት፣ ከሕንድ በ170 ዓመት እንቀድማለን። እኛ የእስልምና መሥራች ነን። የእውነት ምድር በመባል ከመካ በ16 ዓመት እንቀድማለን” ሲሉ በአኀዝ ያስቀምጣሉ።

ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ትብብር ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን ከዛም በሻገር እንደነበረ ሐጂ አደም ያነሳሉ። ለምሳሌም 14 የሚሆኑ ሀበሾች ከነብዩ ጋር ሆነው ተዋግተዋል።

ነብዩ የእስልምናን መሠረት ከጣሉ በኋላ 632 ላይ አረፉ። ከነብዩ እረፍት በኋላ ሌላ ስደት ተከስቶ ነበር፤ ይህም ኹለተኛው ስደት ነው። ያኔም ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የነብዩ ወገኖች እንደነበሩና መጥተውም በአትዮጵያ ጠረፍ ዙሪያ እንደሰፈሩ ሐጂ አደም ከታሪክ ያታቅሳሉ። ገጠር ላይ የሚገኘው በተለይም አርብቶ አደሩ የማያነብና የማይጽፍ በመሆኑና በየጊዜው የመጡ ነገሥታትም እንዲማርና እንዲጽፍ ያደረጉ ባለመሆኑ፤ ሃይማኖቱን በማስተማርና በማሳወቅ በገጠሩ ሊቃውንት የተባሉ ኡለማዎች ትልቅ ድርሻ እንደነበራው ያወሳሉ።

ይህም የነብዩ ልደት እንዲከበር ምክንያት ሆኗል። ሐጂ እንዳሉት፤ “የእኛም አርብቶ አደር እነርሱን ተከትሎ ማክበር ጀመረ” እናም አርብቶ አደሩ የሚሰማ እንጂ የማያነብ በመሆኑ፤ በመንዙማ እየጻፉ የነብዩን ታሪክ ከልደት እስከ ህልፈታቸው ድረስ አስተምረዋል። አርሶ አደሩ ግንዛቤ እንዲኖረው አደረጉ። ታድያ ለዛም ነው “የኢትዮጵያ ገበሬ ከአረቡ ዓለም ፕሮፌሰር በላይ ስለ ነብዩ ያውቃል” የሚባለውም።

ወሎን እንደ ምሳሌ ወስደው ያነሱት ሐጂ አደም፤ በወሎ የሚገኙ 22 ማዕከላት 646 ሊቃውንት አፍርተዋል ይላሉ። ይሔ የሆነው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በወሎ 12 አውራጃ በነበረ ጊዜ ነው። እናም መውሊድ ኡለማዎች ባሉበት አርብቶ አደር እየቀና ስለነብዩ ታሪክ እያወቀና እየተማረ በዓሉን ያከብር ነበር።
ዘንድሮ የመውሊድ በዓል ለ1494ኛ ጊዜ ይከበራል። የአዲስ አበባ ወጣት ማኅበር ጀማአ የመገናኛ ብዙኀን ኀላፊ አዲል መሐመድ ስለ በዓል አከባበሩ ሲናገሩ፤ በዓሉ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ በድምቀት ይከበራል ብለዋል። በዚህም ታላላቅ የተባሉ አሊሞችና ኡለማዎች እንዲሁም ምሁራን ይታደማሉ።

ታድያ ምዕመናን የእምነቱ ተከታዮችና የበዓሉ አክባሪዎች ማልደው በመስጂድ ተሰባስበው በቁርዐን የሚከፈተውን የበዓል ክዋኔ ይከታተላሉ፤ ተሳታፊም ይሆናሉ። “ራምሳ” የተባለ መንዙማ የሚቀርብ ሲሆን፤ ተከትሎም በአሊሞችም ስለ ነብዩ የሕይወት ታሪክ ትምህርት ይሰጣል። መንዙማዎች እንዲሁም ነሺዳ በልጆች ይቀርባል፤ ዱአ ይደረጋልም።

አዲል እንደሚሉት በበዓሉ ስለ ሰላምና ስለ አንድነት፤ በጋራ በአብሮነት በሰላም ስለመኖር መልዕክቶች ይተላለፋሉ፤ ትምህርቶች ይሰጣሉ። ነብዩ ሰው በሰላም መኖር እንዳልበት ማስተማራቸው ለዚህ ምክንያት ነው። እንዲህ እያለ የሚቀጥለው መርሃ ግብር በግማሽ ቀን ሲጠናቀቅ፣ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቀጥለው ነብዩን የሚያወድስ ግጥምና ውዳሴ ያሰማሉ/ያዜማሉ።

ነብዩ መሐመድ እና ኢትዮጵያ
በመንዙማዎችና በትምህርቱ ታድያ ሰላም ሲሰበክ፣ አንድነት ሲነገር በአንድ በኩል ነብዩ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ትልቅ ድርሻ አለው። ሐጂ አደም እንደውም ነብዩ ከማንም ዓረቡ ዓለም ጋር የሌላቸው ግንኙነት ነው ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ይላሉ። በነብዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሚናም ቀላል የሚባል አልነበረም ሲሉ ይጠቅሳሉ።

በጊዜው ከነብዩ ጎን የነበሩ ሐበሻ የሆኑ አገልጋዮች፣ ሐዲሳቸውን የሚመዘግቡ ሰዎች፣ የሚያማክሯቸው ሊቃውንት፣ የተወሰኑ የጦር መሪዎቻቸው እንዲሁም የመጀመሪያውን አዛን ያለው ቢላል ኢትዮጵያዊ መሆኑ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያሳያል። ሐጂ አደም በበኩላቸው፤ “ይህ ግንኙነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ይላሉ። የጦር መሪዎች፣ አዛን በተመለከተ ቢላል ነው የተመደበው።

መንዙማ በመውሊድ
ለማያነበው ነገር ግን ለሚሰማው ማህበረሰብ የሚዘጋጀው መንዙማ ነበር። በመንዙማዎች ነበር ስለ ነብዩ መወለድ፣ ሕይወትና ታሪክ ዙሪያ ትምህርቶች ይሰጡ የነበረው። ይህም በአረብኛ እንዲሁም በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ነው። ሥነ ጽሑፋዊ ፋይዳውም የላቀ እንደሆነ ነው ሐጂ የሚጠቅሱት።
አናመስግነው ለሰጠን መደድ፤ ኢማን ጋር አርጎ በነብይ መውደድ።

አረቦች ታድያ እነዚህን መንዙማዎች መረጃ አድርገው ይጠቀሙ ነበር። በክርስትያን ጦርነት እንዲሁም በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ክፍፍል የተበከሉ በመሆናቸው ብዙ ጉዳዮቻቸው የተበረዙ በመሆናቸው ነው።

ወጣልን የክብሩ ጀምበር
ማማሩ የለውም ድንበር፤
እንደ ኢትዮጵያ መንዙማ ያዘጋጁ ሊቃውንት በሌሎች አገራት አለመኖራቸውን ሐጂ ይጠቅሳሉ። ግብጽ ውስጥ አንድ መንዙማ ነው የተዘጋጀው ሌላውም ጋር እንደዛው ጥቂት ናቸው ይላሉ። ያውም እነዛ አገራት ሁሉም በአካባቢያቸው ቋንቋ መጠቀም ችለውና በሙስሊም አገር የሚመራው በመሆኑ ጥቅም ያለው ሆኖ ሳለ፤ በዛ ልክ ድጋፍ የማያገኙት ኢትዮያውያን የእስልምና መምህራንና ሊቃውንት ግን ከማንም በላይ በርካታ ድርሰቶችን ማቅረብ ችለዋል።

“እነዚህ ሊቃውንት የቀረው ዓለም ፕሮፌሰሮች የማይሠሩትን ነው በጫካ ሆነው በዛፍ ሥር የሠሩት። ይህን ሊያደርጉ የቻሉትም ምግባቸው ንጹህ ነበር፤ ትኩረታቸውም የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ፍቅር ላይ ስለሆነ ነው” ይላሉ።

ዛሬስ በአረብ አገራት?
የዛሬ አምስት እና ስድስት ዓመት ነው አረብ አገራት የነቁት፤ ሐጂ አደም እንዳሉት። ይህም የሆነበት አጋጣሚ አንድ መምህር ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ስለነብዩ ይጠይቃሉ። “ከነብዩ ሚስቶች መካከል ንገሩኝ” ብለው። ተማሪዎች ግን የነብዩን ልጆች ሥም ነበር የጠሩት። እናም “ትውልዱ ነብዩን እንዲረሳ አድርገናል ብለው፤ እኛ ከአንድ ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት የጀመርነውን አሁን ነው የሚጀምሩት” ይላሉ ሐጂ አደም።

የነብዩ ልደት መከበር አሁን ላይ ሽፋን እያገኘ መሆኑ በአንድ ጎን መልዕክታቸውን ማድረስ እንደሚጠቅም ያነሳሉ። ይሁንና ጠንካራ የእስልምና ጉባኤ ባለመኖሩ የመውለዲን ዓላማ አብራርቶ የሚያሳውቅ የለም ባይ ናቸው። ሐበሻ የከፈለችውን መስዋዕትነት አሳውቀን፣ ያ መስዋዕትነት ባይከፈል ኖሮ ነብዩ ለሃይማኖቱ መሠረት ሊጥሉ እንደማይችሉ ማሳወቅ አለብን፤ እንደ ሐጂ ገለጻ።

ሐጂ አደም፤ “እንደውም በዓለም ላይ ያለው 2 ቢሊዮን ሙስሊም ባለ እዳ ነው” በዛች ቀውጢ ሰዓት በሐበሻ የተከፈለለት መስዋዕትነት ቀላል አይደለምና። የሐበሻ ምድር የተባለችው ኢትዮጵያ ከልጆቻቸው አንድ፤ አራት ሚስቶቻቸውን አስተናግዳለች። ያሳደጓቸውን ኢትዮጵያዊቷ ሐበሻዊት እመቤት የተባሉት ሴት ኡማ ኢመን “ከእናቴ ቀጥሎ እናቴ” ብለው መስክረውላቸዋል፤ ኢትዮጵያ በልደታቸውም አለች። ይህን ውለታ ያልዘነጉት ነብዩ ለዛ ነው ሐበሾችን አትንኩ ያሉት።

እና ይህን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማሰብ እንደሚያስፈልግ ሐጂ ይገልጻሉ። ኢስላማዊ ቅርሶችን ሙዝየም አዘጋጅቶ በማቀመጥ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከእስልምና ሃይማኖት አንጻርም በመንገርና ውለታዋን በመጥቀስ በቂ ግንዛቤ ስለኢትዮጵያ መስጠት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፤ ሐጂ አደም። ይህም በአንድ በኩል ለቱሪዝም ያለው ዋጋ ተያይዞም የሚመጣው ጥቅም ቀላል አይደለም ብለው ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here