ሥራውን የዘነጋው የፌደራል ፖሊስ

0
2006

የፌደራል ፖሊስ በሕግ ከተሰጡት ኀላፊነቶች መካከል የተደራጀ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ ሙስና፣ አሸባሪነት እና የጸጥታ ማደፍረስ ወንጀሎችን መከላከል እና መመርመር እንደሚገኙበት እንዲሁም እነዚህን ኀላፊነቶች ለመወጣት ደግሞ በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል የመሥራት ግዴታ እንዳለበት የሚገልጹት ሚኒሊክ አሰፋ፥ ተቋሙ ግን ሥልጣኑን በሚገባ የተረዳው አይመስል ሲሉ ሕጎችን በማጣቀስ ይተቻሉ፤ ሥራውንም ለማከናወን የክልሎች ይሁንታም አያስፈልገውም ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከተከሰቱ አወዛጋቢ ክስተቶች መካከል አንዱ የፌዴራሉ መንግሥት የሕግ አስከባሪ አካላት በክልል ወሰኖች ውስጥ መግባት ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለው ጉዳይ ነው። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በአውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተነስተው መቀለ ያረፉ 45 የፌደራል ፖሊስ አባላት ከኹለት ሳምንታት በላይ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን ተከትሎ እገዳው “የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ያለ ክልሉ ፈቃድ ወይም ጥያቄ ወደ ክልሉ መግባት አይችሉም የሚል አቋም በመያዙ ምክንያት የሆነ ነው” የሚሉ መረጃዎች ከመገናኛ ብዙኀን ተሰምቷል። በተለያዩ ጊዜያትም በተለያዩ ክልሎች የጸጥታ ችግሮች ሲያጋጥሙ የፌዴራል መንግሥት የጸጥታ አካላት ወደ ቦታው ደርሰው ሁኔታውን ለመቆጣጠር ሲዘገዩ ተስተውሏል። ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ይህን የጸጥታ ማስከበር ሥራ ለመሥራት የክልል መንግሥታት ይሁንታ እስኪያገኝ ነው የሚል ምክንያት ሲቀርብ ይስተዋላል። የፌዴራሉ መንግሥት ለጸጥታ ማስከበር የሚያሰማራው ዋነኛው ኀይልም የፌዴራል ፖሊስ ከመሆኑ ይልቅ የመከላከያ ሠራዊት መሆኑም ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ከርሟል።

ለመሆኑ ጸጥታ እና ደኅንነትን በማስከበር ረገድ ክልሎች እና የፌዴራሉ መንግሥታት ያላቸው ኀላፊነት ምን ድረስ ነው? ጸጥታ እና ደኅንነትን የማስከበር ቀዳሚ ኀላፊነት ያለበት የትኛው የመንግሥት መዘውር ነው? ፌዴራል መንግሥት ወይስ የክልሎች?
በመሰረቱ የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ አገራት ውስጥ የክልል እና የፌደራል መንግሥታት ሥልጣኖች ተለይተው የሚቀመጡት በአገራቱ ሕገ መንግሥት ላይ ነው። በክልሎች እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው የሥልጣን ክፍፍልም የሚመሰረተው በሕገ መንግሥቱ በዝርዝር በሚቀመጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው። የፌደራል መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን የሚያስፈፅመው በሁሉም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ግዛት ውስጥ ሲሆን የክልል መንግሥታት ግን የተሰጣቸውን ሥልጣን የሚተገብሩት በራሳቸው የክልል ወሰን ውስጥ ብቻ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ጸጥታ እና ደኅንነትን የማስከበር እና ወንጀልን የተመለከተ ሥልጣን በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መካከል የተከፋፈለበት መንገድ ግልፅነት ይጎድለዋል። ብዥታውን ከፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ የወንጀል ነገረ ሥልጣን (criminal jurisdiction) በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የተከፋፈለበት መንገድ ወጥነት የጎደለው በመሆኑ ነው። (በዚህ ዓውድ የወንጀል ነገረ ሥልጣን የሚለው አገላለጽ የወንጀል ሕግን የማውጣት፤ ወንጀልን የመከላከል እና የመመርመር እንዲሁም ክስ የመመስረት እና የመዳኘት ሥልጣንን በሙሉዕነት ያካትታል)
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50(1) መሰረት የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው። ይህ አንቀጽ የሚሰጠው ትርጓሜ ለፌደራል መንግሥት ተለይቶ የተሰጠ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ የማውጣት፣ የማስፈፀምና የመተርጎም ሥልጣን ይኖረዋል፤ ለክልል የተሰጡ ጉዳዮች ላይም የክልል መንግሥታት ተመሳሳይ ሙሉዕ ሥልጣን ይኖራቸዋል የሚለውን ነው። ይሁንና ከዚህ መርህ ወጣ ያሉ ልዩ ሁኔታዎች መኖራቸውም መዘንጋት የለበትም (ለማሳያነት አንቀጽ 51/5 እና 52/1/መ በጥቀስ ይቻላል)።

የኢ.ፌ.ዴሪ ሕገ መንግሥት የወንጀል ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ቀዳሚ ሥልጣን የፌደራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55/5 ይደነግጋል። ክልሎች የወንጀል ሕግ ማውጣት የሚችሉት የፌዴራሉ የወንጀል ሕግ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መሆኑን ይህ አንቀጽ ጨምሮ ያስቀምጣል። ቀደም ብለን በጠቀስነው መርህ መሰረት ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው የወንጀል ሕግ የደነገጋቸውን ወንጀሎች የመከላከል እና የመመርመር ኀላፊነት የፌደራል ፖሊስ መሆኑ አያጠራጥርም። እንዲሁም በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ የመመስረት እና ወንጀሎቹን የመዳኘት ኀላፊነት የፌዴራሉ መንግሥት ዐቃቤ ሕግ እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መሆኑም ግልፅ ነው። በዚህ መሰረት ክልሎች በፌዴራሉ የወንጀል ሕግ ያለተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ የወንጀል ሕግ የማውጣት እና በፖሊስ ኀይሎቻቸው አማካኝነት ይህንን ሕግ በክልላቸው ወሰን ውስጥ በማስከበር ሥልጣን ይኖራቸዋል።

ሆኖም በዚህ መልኩ ለፌዴራል መንግሥት እና ለክልሎች የተከፋፈለው የወንጀል ሥልጣን በተግባር ብዙ ብዥታዎች ተፈጥረውበታል። ይህም ብዥታ የሚጀምረው በ1988 ከወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 ውስጥ ከተካተቱ ድንጋጌዎች ነው። ይህ አዋጅ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸውን የወንጀል ዳኝነት ሥልጣን በአዋጁ አንቀጽ አራት ሥር በተዘረዘሩ አሥራ ኹለት ጥቅል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ይደነግጋል። ነገር ግን ይህ አዋጅ ከፀደቀ ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ የወጣው የፌዴራሉ የወንጀል ሕግ (አዋጅ ቁጥር 414/1996) ከሃምሳ በላይ ጥቅል ርዕሰ ጉዳዮችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንጀሎችን አካቷል። ነገር ግን የፌዴራሉ መንግሥት ይህን የወንጀል ሕግ ሙሉ በሙሉ የማስፈፀም እና የመተርጎም ኀላፊነትን አልወሰደም። ይህም የሆነው በሦስት ተያያዥ ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያው ምክንያት ቀደም ሲል የተገለፀው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ እስካሁን ያልተሸሻለ በመሆኑ አሁንም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል ዳኝነት ሥልጣን በአሥራ ኹለቱ ጥቅል ጉዳዮች እና በሌላ አዋጅ በተደነገጉ ውስን ወንጀሎች ላይ ብቻ የተወሰነ መሆኑ ነው። ኹለተኛው ጉዳይ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ (ቁጥር 720/2004) ለፌደራል ፖሊስ የሚሰጠው የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ሥልጣን በፌዴራል ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ሥር የሚወድቁትን ጥቅል የወንጀል ጉዳዮች ሌሎች ጥቂት ርዕሰ ጉዳዮችን ብቻ መሆኑ ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በአዋጅ ቁጥር 943/2018 መሰረት መርመራ የማስጀመር እና ክስ የመመስረት ሥልጣን የሚኖረው በእነዚሁ ውስን ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። ከእነዚህ ውጪ ያሉ በፌዴራሉ የወንጀል ሕግ የተቀመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የወንጀል ዓይነቶች የፌዴራሉ መንግሥት የደነገጋቸው ቢሆኑም የፌዴራል ፖሊስ የማያስፈፅማቸው፤ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ የማይመሰርትባቸው እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶችም የማይዳኟቸው ሆነው ቀርተዋል። በዚህ ረገድ እነዚህ ከፌደራል ፖሊስ እና ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ውጪ የተደረጉ ወንጀሎች በግልፅ ለክልሎች በውክልና የተሰጡበት ሕግ የሌለ ቢሆንም በተግባር የክልል ፖሊሶች እና የክልል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን እንደሆኑ ተቆጥረው እየተሰራባቸው ይገኛል።

ለባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት ግልፅ የሆነ ውክልና በሌለበት ሁኔታ ክልሎች የፌዴራሉን የወንጀል ሕግ እያስፈፀሙ እና እየዳኙበት ቆይተዋል።
ይህ ሆነ ተብሎ የተደረገ ከሆነ ቀድሞውኑ የፌዴራሉ መንግሥት የወንጀል ሕጉን ሲያወጣ ሊያስፈፅማቸው እና ሊዳኛቸው የሚችሉትን ብቻ ለይቶ የቀሩትን ክልሎች ሕግ እንዲያወጡባቸው፣ እንዲያስፈፅሟቸው እና እንዲዳኟቸው ማድረግ ይቻል የነበረ ሲሆን ይህ እንኳን ባይሆን በአዋጅ ግልፅ የሆነ ውክልና ለክልሎች በመስጠት ሁኔታውን ግልፅ ማድረግ ይቻል ነበር። ሆኖም በሕገ መንግሥቱ እና አሁን በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች መሰረት የወንጀል ሕጉን የማስፈፀም ኀላፊነት የፌዴራል ፖሊስ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሆኑ ግልፅ ነው። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የፍርድ ቤቶች የውክልና አሠራር እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ሕጉ የተዘረዘሩ ሁሉም ወንጀሎችም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነገረ ሥልጣን ሥር የሚወድቁ መሆናቸው እሙን ነው። በመሆኑም የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ሕጉን ለማስፈፀም ሙሉ ሥልጣን ያለው እና ያለክልሎች ፍቃድ እና ይሁንታ ሊሠራበት የሚችል ነው።

በፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ከተሰጡት ኀላፊነቶች መካከል የተደራጀ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ ሙስና፣ አሸባሪነት እና የጸጥታ ማደፍረስ ወንጀሎችን መከላከል እና መመርመር ይገኝበታል። በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ደግሞ በሕግ ተለይተው የተሰጡትን ኀላፊነቶች ለመወጣት በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ የመሥራት ግዴታ አለበት። ይሁንና ቀደም ብለን ከጠቀስናቸው አጋጣሚዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የፌዴራሉ መንግሥት ይህንን ሥልጣኑን በሚገባ የተረዳው አይመስልም።

በተለይ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ብዥታን ፈጥሯል። ይህ አዋጅ መነሻ ያደረገው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ የተቀመጡት ሦስት የተለያዩ ጣልቃ የመግባት ሁኔታዎችን ነው። የመጀመሪያው ሁኔታ በአንቀጽ 51/14 መሰረት ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ ጥያቄ መሰረት የፌደራል መንግሥት የአገሪቱ መከላከያ ኀይልን ወደ ክልሉ ማሰማራት እንደሚችል የሚደነግግ ነው። እዚህ ጋር የፌደራል መንግሥት በክልሎች ፈቃድ ማሰማራት የሚችለው ኀይል የመከላከያ ሠራዊት መሆኑን እንጂ የፌደራል ፖሊስን መተመለከት የክልሎች ጥያቄና ይሁንታ ስለማስፈለጉ የተገለፀ ነገር እንደሌለ ልብ ይሏል።

ይህ ዓይነት ጣልቃ ገብነትን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱ ላይ አንድ መሰረታዊ ችግር መጥቀስ ይቻላል። ይህም ሕገ መንግሥቱ የወንጀል ሕግን የማውጣት እና የማስፈፃም ቀዳሚ ኀላፊነትን (original jurisdiction) ለፌደራል መንግሥቱ ተሰጥቶት ሲያበቃ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም” በማለት የአገሪቱን ጸጥታና ደኅንነት የማስከበር ቀዳሚ ኀላፊነት የክልሎች እንደሆነ የሚያስመስል አንቀጽ ማስቀመጡ የሕገ መንግሥቱ ራሱን በራሱ እንዲጣረስ ያደርገዋል። ከላይ እንደተገለፀው በዋናነት የወንጀል ሕግን የማውጣት እና የማስፈፀም ቀዳሚ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የፌዴራል መንግሥቱ ነው። አሁን በሥራ ላይ ባሉ ዝርዝር ሕጎች መሰረት ደግሞ፤ በተለይም በተደጋገሚ የጸጥታ ችግር እየሆኑ የመጡትን የተደራጀ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ አሸባሪነት እና የጸጥታ ማደፍረስ ወንጀሎችን መከላከል እና መመርመር ተግበር የፌደራል ፖሊስ ዋና ኀላፊነቶች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ የመከላከል እና ከተከሰቱ በኋላም የመመርመር ቀዳሚ ኀላፊነት የፌዴራል ፖሊስ እንጂ የክልል የጸጥታ አካላት መሆን የለበትም። ሆኖም ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51/14 ላይ እነኚህን ሁኔታዎች በተመለከተ ቀዳሚ ኀላፊነት ያላቸው የክልል መንግሥታ እንደሆኑ ታሳቢ በማድረግ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም” በማለት የፌደራሉ መንግሥት የመከላከያ ኀይሉን የሚያስገባበትን ሁኔታ ያስቀምጣል።

በመሰረቱ ከአቅም በላይ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም የአገራት የመከላከያ ኀይል ጉዳዩን ለመቆጣጠር የሚገባበትን ሁኔታ በዝርዝር መደንገግ ያስፈልጋል። ይህም በተለይ የፌዴራል ስርዓትን በሚከተሉ አገራት ውስጥ የመከላከያ ኀይልን ማሰማራት የክልሎች ሉዓላዊነት እንደመድፈር ስለሚቆጠር እና ከሰብኣዊ መብት አያያዝ ጋር የሚያስነሳቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ ነው። ለዚህም ሲባል የመከላከያ ኀይሉ ከመግባቱ በፊት የክልሎች ይሁንታ እንዲኖር ያስፈልጋል።

በእኛ አገር ሕገ መንግሥትም ይህ ሁኔታ መቀመጡ ተገቢ ሆኖ ሳለ ‹ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም› የሚል ቃል ማስቀመጥ የጸጥታ መደፍረሱን የመቆጣጠር ዋና ኀላፊነት ያላቸው ክልሎች ናቸው ወደሚል የተሳሳተ ትርጓሜ እንዲወሰድ ሊያደርግ ይችላል። ከላይ ባለው ሐተታ ለመግለፅ እንደተሞከረው በሕገመንግሥቱና አሁን በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች መሰረት ጸጥታና ደህንነትን የማስከበር ሥልጣን የክልሎች ሳይሆን የፌዴራል ፖሊስ ነው። በመሆኑም ‹ከአቅም በላይ› የሚለው አገላለፅ ከፌዴራል ፖሊስ አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም የመከላከያ ሠራዊት በክልሎች ፈቃድ በክልሎች ውስጥ ሊሰማራ ይችላል በሚል መቀመጥ ነበረበት። ይሕም የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች የፈጠሩት ሥህተት ነው ማለት ይቻለል።

በተጨማሪም አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ አምስት የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ የሚያሰማራቸው ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ እንደሆኑ ይገልፃል። ነገር ግን ሕገመንግሥቱ የፌዴራል መንገስቱ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ በሚገባበት ወቅት የሚያሰማራው ኃይል የመከላከያ ሠራዊትን መሆኑን እንጂ የፌዴራል ፖሊስን መሆኑኑ አይገልፅም። ከላይ እንደተገለፀው በሕገ መንገስቱ አንቀጽ 51/14 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ የፌዴራል መንገስት በክልሎች ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ኃይሉን የሚያሰማራበትን ሁኔታ የሚፈጥር እንጂ የፌዴራል ፖሊስ በደበኛ ሥራውን ለማከናወን የክልሎች ፈቃድ ያስፈልገዋል የሚል ትርጓሜን የሚሰጥ አይደለም። ምክንያቱም ከሕገመንግሥቱ እና ከፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው የፌደራል ፖሊስ ሕገ መንግሥቱ፣ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ እና በአገር ጸጥታና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ስጋቶችን የመከላከል እና የመመርመር እንዲሁም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ትዕዛዞች የማስፈፀም ቀዳሚ ኀላፊነት ተሰጥቶታል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ቢያንስ የፌዴራል ፖሊስን በክልል ወሰኖች ውስጥ መደበኛ ሥራውን የሚሠራበት ሁኔታ እንደ ጣልቃ መግባት ተቆጥሮ በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 5 ላይ መካተቱ አግባብ አይሆንም።

በዚህ ረገድ ትክክለኛ አተረጓጎም የሚሆነው የሕገ መንግሥቱን መርህ መከተል ነው። ቀድሞውንም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51/14 ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም የአገሪቱ መከላከያ ኀይል በክልል ጥያቄ መሰረት ወደ ክልሉ መግባት እንደሚችል እንጂ ፌደራል ፖሊስ የዕለት ተዕለት ሥራውን ለማከናውን የክልሎች ይሁንታ እንደሚያስፈልገው አይገልጽም። ስለሆነም ፌዴራል ፖሊስ በክልሎች ውስጥ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የክልሎች ፈቃድ አያስፈልልውም፤ መደበኛ እንቅስቃሴውም እንደ ጣልቃ መግባት ሊቆጠር አይገባውም። የፌዴራል መንግሥት ይህንን አቋም በመያዝ ቢያንስ የተደራጀ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ ሙስና፣ አሸባሪነት እና የጸጥታ ማደፍረስ ወንጀሎችን የመከላከል (የጸጥታ ማስከበር)፣ የመመርመር፣ የመክሰስ እና የመዳኘት ተግባር በፌዴራል የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት በኩል ሊያከናውን ይገባል። የጸጥታ መደፍረሶች ባጋጠሙ ቁጥር የመከላከያ ኀይልን የማስገባት አባዜም በጊዜ ካልተገራ አላስፈላጊ ኀይል እና ሥልጣንን በመከላከያ ኀይሉ ላይ በማከማቸት ለቀነጨረው ዲሞክራሲያችን ተጨማሪ ስጋት ሊፈጥር ይችላል። የተቀሩት የወንጀል ዓይነቶች ላይም ክልሎች ሕጋዊ ሥልጣን እንዲኖራቸው የፌዴራል መንግሥቱ የፌዴራል የወንጀል ሕጉን አድማስ በመቀነስ ማሻሻያ ማድረግ አልያም በሕግ በሚሰጥ ውክልና የወንጀል ሕጎቹን አብዛኛው ክፍሎች ለክልሎች ማስረከብ ይኖርበታል።

ሚኒሊክ አሰፋ የሕግ ባለሙያና ተመራማሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው minilikassefa@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here