ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ግንቦት 1/2015 ሌሊት ከትግራይ ክልል እና ከአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አካባቢ ተነስተው፤ በአፋር በኩል ወደ ጅቡቲ በሕገወጥ መንገድ በሲኖትራክ ሲጓዙ የነበሩ ወጣቶች አደጋ እንዳጋጠማቸው ተሰምቷል።
ወጣቶቹ በአፋር አድርገው ወደ ጅቡቲ ሲወጡ፤ ጅቡቲ መግቢያ አካባቢ በሚገኘው ዲቸል ተብሎ ከሚጠራ ሥፍራ ግንቦት 1 ሌሊት መኪናው ተገልብጦ የኹለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።
ሌሊት ሲጓዙ የነበሩት ወጣቶች ድንበር ጥሰው በሕገወጥ መንገድ ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ በመጓዝ ላይ እያሉ ከዲችኦቶን 45 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ዲቸል ከምትባል አካባቢ ሲደርሱ፤ ሲኖትራኩ ተገልብጦ የኹለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ20 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል አደጋ አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሰማችው፤ በሕጋዊ መንገድ ፓስፖርት አውጥቶ ወደ አረብ አገራት መሄድ እየተቻለ በሕገወጥ መንገድ ለመሄድ ሲሞክሩ ሕይወታቸውን እያጡ ወጣቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ተጎጅዎቹ ጅብቲ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በጊዜያዊ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጉም ተገልጿል፡፡
ሰዎች በደላላና በውሸት ፕሮፖጋንዳ እየተነሱ በሕገወጥ መንገድ እየሄዱ የብዙሃን ዜጎች ሕይወት እያለፈ እንደሚገኝ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ አፋር ኮሪደር በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ ሄደው ከየመን እና ከጅቡቲ የሚመለሱ በርካቶች መሆናቸውንም አመላክቷል።



