ሴታዊት ከኢዜማ ጋር መደበኛ የሆነ ቁርኝት የላትም

0
1201

በማንም ላይ የሚደርስን ጥቃት የሚጠየፍ ስብዕና ከልጅነት ጀምሮ አብሯቸው የነበረ በተፈጥሮም የታደሉት ነው። “ፌሚኒስት ሆኜ ነው ራሴን ያገኘሁት” ይላሉ፤ ስሂን ተፈራ (ዶክተር)። ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ ነው። እኩልነትንና የሴት ልጅን ክብር እያዩ ባደጉበት ቤተሰብ፤ የአባታቸው መልካም ተግባራት በአረዓያነት ደጋግመው የሚያነሱት ነው።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ ሰብዕ (ሶሽዮሎጂ) ሲያገኙ፤ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ከክላርክ ዩኒቨርስቲ በዓለም ዐቀፍ ልማት በተለይ ስርዓተ ጾታ ላይ መሠረት አድርገው ተቀብለዋል። ሦስተኛና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከእንግሊዝ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን ያገኙት የትምህርት ዕድል በጀመሩት የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ላይ እንዲያጸኑ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ይህም በቀላል ያገኙት ካለመሆኑ ሌላ ብዙ የተፈተኑበት መሆኑን ያወሳሉ።

የአንዲት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት የሆኑት ስሂን፤ ዛሬ ላይ የደረሱበት መንገድና ጉዟቸው ቀላል አልነበረም። የራሳቸውን የሕይወት ትግል ከመወጣት አልፈው ለጾታ እኩልነት የቆመች ሴታዊት የተሰኘችው ማኅበር ላይ አሻራቸው ይገኛል። ማኅበሯን ከጥንስሱ ያውቋታል፤ ከመሥራቾቹ ተጠቃሽ ናቸው። አሁንም በማኅበሯ የአመራር አባል ሆነው ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

አዲስ አበባ በተለምዶ ሃያ ኹለት አካባቢ አክሱም ሆቴል አጠገብ ከሚገኘው ኮሜት ሕንጻ ሦስተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የሴታዊት ቢሮ፤ ከሴቶች እንዲሁም ከወንዶችም የተለያዩ ትችቶች የሚገጥመው ነገረ ፌሚኒዝም በሥፋት ይነሳል። ወንዶችም ሴቶችም የዚህ አካል ሆነው ስለሴቶች መብትና እኩልነት ይሟገታሉ፤ ይሠራሉ።

በቅርቡ ደግሞ የሴታዊት ሥም በፖለቲካ ጉዳዮች እየተነሳ ይገኛል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህንን እና የሴታዊትን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲሁም ስለ ግል ሕይወት ገጠመኞቻቸው ከስሂን ተፈራ (ዶክተር) ጋር ሰፊ ቆይታ አድርጋለች።

አዲስ ማለዳ፡ በኢትዮጵያ አቅምና ችሎታ ያላቸው ስኬታማ የሆኑ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች አሉን፤ መድረክ ላይ ወጥቶ መናገር ላይ ሲሆን ግን ያንን አናይም። ይሔ ለምን የሆነ ይመስልዎታል?
ስሂን ተፈራ (ዶክተር)፡ እውነት ነው ስኬታማ ሴቶች አሉን፤ ነገር ግን አንደኛ ከወንዶች ሲወዳደር እንዲሁም ከሌላ አገር ስኬታማ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ውስጥ ስኬታማ የምንላቸው ሴቶች፤ ለምሳሌ በኢኮኖሚው ካነሳን፣ ቁጥራቸው አነስተኛ ነው። ምን ያህል ተዓማኒ እንደሆነ ባላውቅም አንድ የወጣ ዘገባ ከአምስት ከፍተኛ ሀብታም ሰዎች መካከል አንዷ ሴት ናት ይላል።

ከዛ ውጪ ግን በብዙ ቦታ ከፍተኛ ድርጅቶችን የሚመሩ ሴቶች ቁጥር ይህን ያህል ብዙ የሚባል አይደለም። በትምህርትም ካየን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሃምሳ ዓመት ዕድሜው አምስት ሴት ፕሮፌሰሮችን ብቻ ነው ያፈራው። ከሌላም አገር ሲወዳደር ወንዶች ከሚደርሱበት ደረጃ የደረሱ ሴቶች ቁጥር ይህን ያህል አይደለም። እንደዛም ሆኖ መድረክ ላይ ወጥተው ራሳቸውን መግለጽ የሚችሉ ሴቶችም አሉ።

እኔ ግን ይበልጥ የሚያሳስበኝ ብዙ ጊዜ ስኬታማ የምንላቸው ሴቶች ለሌላ ሴቶች ሲቆሙ አናይም። ቶሎ ብለው ይህን ስኬት ወደ ሌላ ሴቶች ከማድረስ ይልቅ በእንግሊዝኛ “ላይከቢሊቲ” የምንለው መጠላትን መፍራት ይታይባቸዋል። ቶሎ ብሎ የባሎች ተገዢ መሆናቸውን፤ ከኅብረተሰብ አፈንግጠው እንዳልሆነ እዚህ ስኬት ላይ የደረሱት ለማሳየት ይሞክራሉ። ምክንያቱም እዛ ቦታ መድረስ ብቸኝነት ይፈጥራል። ሴቱም ወንዱም፤ ሁሉም ሰው ሲመለከታቸው ብቸኝነት ይፈጥራል፤ እንዲሁም “ሴት ነኝ፤ ከማንም ተሸዬ አይደለም” የሚል ራስን ዝቅ የማድረግ ነገር እናያለን።

ይህ ግን ብዙ ጊዜ አይጠቅመንም፤ ለሌላ ሴቶች አርዓያ መሆን የምንችለው ምን ያህል ገፍተን እንደወጣን ስናሳይ ነው። እና እንደዛ ባይሆን ደስ ይለኛል።
እንዲሁም ሴቶችን ወደ እኩልነት ዓላማ የማምጣት፣ ሌሎች ሴቶችን የመደገፍ ነገር ብዙ ጊዜ አይታይም። እንደውም ሥማቸውን የማልጠቅሰው ትላልቅ ቦታ የደረሱ ሴቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ሲያወሩ ሁልጊዜ ምን ያህል ሴቶች በዛ ውስጥ እንዳሉ እንዲናገሩ እጠብቃለሁ። ግን አይናገሩም/አያውቁትም። ኹለትና ሦስት ሺሕ ሰው ያስተዳድራሉ፤ ያ ቀላል አይደለም፤ ከዛ ውጪ ይህን ያህል ሴቶች ቀጥሬያለሁ የሚለውን መግለጽና ማወቅ ከሴት መሪዎች የሚጠበቅ ነበር፤ በሒደት የሚስተካከል ሊሆን ይችላል።

በፖለቲካው ጉዳይስ የሴቶችን ተሳትፎና ድርሻ በምን ደረጃ ላይ ነው ይላሉ?
በጣም ዝቅ ያለ ነው። የሚያሳስበው ደግሞ በለውጥ ሒደቱ ብዙ ነገር ተስፋ አድርገን ብዙ ለውጥ ጠብቀን ነበር። መንግሥትም ብዙ ቃል የገባልን ነገር አለ። ግን ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ አይደለም። እንደውም የሚያሳስበኝ በፊት ከነበረውም ያነሰ ተሳትፎ እንደሚኖር ነው።

ይህ ደግሞ የሚሆንበት አንድ ምክንያት ለእኛ ያዘንበት አጋጣሚ አለ። በቅርብ የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሕግ ላይ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድም ብዙ ግፊት ተደርጎ ትንሽ እንኳን ለሴቶች ኮታ እንዲኖር ተጠይቆ ነበር። በሕገ መንግሥት የሚፈቀድ ነው፤ የተፈቀደም ብቻ ሳይሆን የተደነገገ ነው። ግን ያለምንም ኮታ ነው ያለፈው፤ ምንም አስገዳጅ ነገር የለም። ማለትም ፖለቲካ ፓርቲዎች አንዲትንም ሴት ማካተት አይጠበቅባቸውም።

ስለዚህ በቅንነት ካደረጉትና ሴቶችም ደፍረው ከመጡ እንጂ ያለምንም ሴት ተሳትፎ ሊሆን የሚችል ምርጫ ነው አሁን እያስፈራን ያለው። እና ትንሽ አዳጋች ሆኖብናል፤ እያሳሰበንም ነው።

በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ አራት ፓርቲች ውስጥ ሴት መሪዎች አሉ። ከተቃዋሚ ግን ሴት መሪዎች የሉም። ባለፈው ተመዘገቡ ከተባሉ 137 ውስጥ አንዲትም ሴት መሪ የለችም። ብዙ ጊዜም አመራር ላይም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ ሴቶችን አናይም። ኢትዮጵያ ሴት ያላት አትመስልም፤ አልተወከልን።

እና ሴቶችም ደፍረን ልንሔድ፤ ቦታውም ሊከፈትልን ይገባል። ክፍተት ያለው ኹለቱም ጋር ነው፤ አሁን ግን የፖለቲካ ተሳትፎ አዳጋች ሁኔታ ላይ ይገኛል። ያለ ፖለቲካ ደግሞ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አደጋ ያለው ስለሆነ ከፖለቲካ እንድርቅ ተደርገን ነው የተቀረጽነው። ወላጆቻችንም ፖለቲካ ውስጥ እንዳትገቡ ሲሉን ነው የኖሩት፤ ብዙዎቻችን ርቀነው ነው የኖርነው። ግን እውነቱን ለመናገር መጨረሻ ላይ ምንም ዓይነት መፍትሔና ለውጥ የሚመጣው ከፖለቲካ ጋር በሚሠራው ነገር ነው። እናም ተሳትፈን ለውጥ ማምጣት ያስፈልገናል።

ሴታዊት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ ፓርቲ (ኢዜማ) ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?
ይሔ ሥራውን ሳንጀምር ትችት እያመጣብን ያለ ጉዳይ ነው። ሴታዊት ከኢዜማ ጋር መደበኛ የሆነ ቁርኝት የላትም። ግን ከብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት እየሞከርን ብዙዎች ስለ ስርዓተ ጾታ ምንም መስማት በማይፈልጉበት ሁኔታ ኢዜማዎች ፈልገውን መጥተው ነው። ዶክተር ብርሃኑ ቢሯችን ድረስ መጥተው አብረን መሥራት እንፈልጋለን፤ በዚህ በዚህ መልክ እናንት የምትሠሩትና እኛ የምንሠራው አብሮ ይሔዳል ስላሉን፤ ቴክኒካል የሆነ ሥራ ነው የምንሠራላቸው። የጾታ እኩልነት ፖሊሲ መቅረጽ ላይ እናግዛቸዋለን። መጨረሻ ላይ እነሱ ናቸው ባለቤቶቹ፤ እኛ ቴክኒካል እገዛ ነው የምናደርገው።

ይህን ሥራ ለማንም ፖለቲካ ፓርቲ ብናደርገው ደስ ይለናል፤ እናሰፋዋለንም። ኢዜማ ቀድሞ መምጣቱ እንደውም በጣም ቶሎ ቶሎ እንድንሠራ እየገፉን ነው፤ ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ። [የትኛውም] የፖለቲካ ፓርቲ ከሴቶች ጋር ለመሥራት እንፈልጋለን ብለው ቢመጡ፤ ቢመጡም ብቻ ሳይሆን እኛም ስንቀርብ ፈቃደኛ ቢሆኑ ደስ ይለናል።

ሌላ ኹለት ሦስት ያሰብናቸው ፕሮግራሞች አሉ፤ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር። ሴታዊት ትንሽ ናት፣ በአቅምም በገንዘብም። ግን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመድረስ እየሞከርን ነው። ከእኛ የሚገዝፉ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመድረስ እየሞከርን ነው። ስለዚህ ከኢዜማ ጋር ብቻ ያለን ግንኙነት አይደለም።

ሴታዊት ሲቪክ ማኅበር መሆኗ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንዳታደርግ አይገድባትም?
አሁን ባለው ሕግ ተፈቅዷል። ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ በተሻሻለው ሕግ ይፈቀዳል። ፖለቲካ ውስጥ ማለት ፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመን ወይም አባሎቻችንን ይህን ፖለቲካ ፓርቲ ምረጡ ዓይነት ሥራ አይደለም የምንሠራው። ለምሳሌ እኛ የምንቀርባቸው ድርጅቶች ሔዳችሁ ምረጡ የሚል ዓይነት ትምህርት ይሰጣሉ። ይህ ደግሞ ለሲቪክ ማኅበራት የተፈቀደ ነው፤ ዴሞክራሲን ማስፋፊያ አንዱ መንገድም ነው።

ወደኋላ መለስ እንበልና ስለ ሴታዊት ምሥረታ እናንሳ፤ እንዴት ነበር የተመሠረተችው?
ሴታዊት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ነው የተመሠረተችው። ሴታዊ (‘ፌሚኒስት’) ማንነት ያለን፣ በተለያዩ ተቋማት በሥርዓተ ጾታ እና ጾታ እኩልት ላይ የምንሠራ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ ግን አንድ የሚሰበስበን ነገር እንደሌለ ስናስብ፤ እኔና በጊዜው የማውቃቸው በአካባቢው ያሉ ጓደኞቼ ለምን መገናኘት አንጀምርም በሚል ነው በወር አንዴ በመገናኘት የጀመርነው። ምንም ቦታ ስላልነበረን በየሆቴሉ ነበር የምንገናኘው። እንደ ንባብ ክበብ እናነብ፣ ስለኢትዮጵያ የተጻፉ በተለይም ከስርዓተ ጾታ አንጻር እያነሳን እንወያይ ብለን ጀመርን።

ከዛ ሳናስበውና ዝግጁ ሳንሆን ነው ድንገት ሐና ላሎንጎ ላይ የደረሰው ጥቃት ከ5 ዓመት በፊት ተከሰተ። እሱ ወደፊት ለመምጣትና ለመናገር፤ ከሚድያ ጋር ለመገናኘት ገፋን። ከዛ በኋላ ነው ወደ ማኅበርነት ያደገው። ለአንድ ዓመት ያህል ቢሮ ስላልነበረን አንድ ጓደኛችን ቢሮውን በወር አንዴ እየከፈተልን እዛ ነበር የምንሰበሰበው።

ከመጀመሪያው ታድያ ጥናት ላይ በተመሠረቱ ሥራዎች ነበር የምንወያየው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ጾታ ላይ የሚያጠኑ ሴቶች ይመጣሉ፤ ወንዶችም። ከዛ ትንሽ እየተቀየረ የመጣው ወንዶች መሳተፍ በመፈለጋቸው ነው። ስለ ስርዓተ ጾታ ያገባኛል የሚሉ ወንዶች መግባት ጀመሩ። በሴቶች ብቻ የተጀመረውን የማክሰኞ ማታ ስብሰባን መቀየር አልፈለግንም። ስለዚህ ሰፋ ያለ በሦስት ወር አንዴ ለሁሉም ክፍት የሆነ የውይይት መድረክ ፈጠርን። አንድ ጊዜ ወንድ፤ ሌላ ጊዜ ሴት አወያይ እያደረግን ውይይት እናደርጋለን። የውይይት መነሻዎችም በዓመት መወሰን ጀመርን። ስለዚህ ትንሽ የሆነ ቅርጽ እየያዘ መጣ።

ለምሳሌ አንዱን ዓመት ስለ ሃይማኖት ነበር ያደረግነው። ሃይማኖትን መንካት ብዙ ባንፈልግም ገፍቶ ይመጣል፤ ምንም ነገር ስንሠራ ሃይማኖተኛ አገር ስለሆንን ጥያቄው ስለመጣ እሱን አንድ ዓመት አደረግን። ለምሳሌ እስልምና እና የሴቶች የእኩልነት ንቅናቄ እንዴት አብሮ ይሔዳል፤ ከዛ ደግሞ በክርስትናው የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የእኩልነት ምሳሌ በሚል አደረግን። በዚህ ዓመት ፖለቲካ ላይ ትንሽ ንቅናቄ ማድረግም ስለተፈቀደ የዚህ ዓመት ጉዳያችን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ነው።

ሴታዊት አሁን የምትታወቅባቸው ውይይቶች በወር አንዴ ያለው እና ይኸው በሦስት ወር አንዴ ለሕዝብ ክፍት በሚሆነው ውይይት ነው። ከዛ ደግሞ የበለጠ ጾታዊ ጥቃት ላይ አተኩረን ነው የሠራነው። ብዙ ጊዜ የሠራነው በዘመቻ መልክ ነው። ለምሳሌ አሲድ መድፋት ላይ ኹለትና ሦስት ጊዜ ዘመቻ አድርገናል። “ጫልቱ ለምን ሞተች” የሚል የዛሬ ኹለት ዓመት ተደፍራና አሲድ ተደፍቶባት የሞተች የ13 ዓመት ልጅ ነበረች፤ (ክሱ እስከአሁን አላለቀም) በእርሷ ሥም የሠየምነው ዘመቻ ነው።
በዚህ ዘመቻ እኛ ማድረግ የፈለግነው ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ ስለ አሲድ መድፋት ምንም አይጠቅስም። ምክንያም ሕጉ በወጣ ጊዜ አሲድ መድፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልታወቀ ስለሆነ። እና ፊርማ አሰባሰብን። ዐሥር ሺሕ ለመሰብሰብ አስበን ሃያ ሺሕ አግኝተን ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ወሰድን። ሕጉ እየታየ ስለሆነ ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ ብታዩት ብለን አቀረብን። እሱ አሁን ፓርላማ ለቋሚ ኮሚቴ ቀርቧል።

ሌላ በዘመቻ መልክ የሠራነው “ምን ለብሳ ነበር?” ዓውደ ርዕይ ነው። አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው ሴቶች በጊዜው የለበሱትን ልብስ ነው ያቀረብነው። ትልቋ ሃያ ትንሿ ሰባት ዓመት ነበሩ። በጊዜው የለበሱትን ልብስ ነው ለዕይታ ያቀረብነው። ብዙ ጊዜ ጥቃት የደረሰባቸውን ልጆች ጥፋተኛ የማድረግ አባዜ ስላለ፤ እሱንም ለመቀየር ያደረግነው ሙከራ ነው።

ይህ ዓውደ ርዕይ የዛሬ ዓመት ነው የተጀመረው፤ አሁንም እየሔደ ነው። ከአዲስ አበባ ወጥቶ አሁን ወላይታ፣ ጎንደር እየተካሔደ ይገኛል። ከዛም “አሪፍ አባት” የሚል የመልካም አባትነትን ምሳሌ ለመስጠትና ለማሳየት የተሠራ የፎቶ ውድድርና አውደ ርዕይ ነበር።

አሁን 5ኛ ዓመታችን ላይ ነን። ትንሽ አካሔዳችን ለማስተካከል እየሞከርን ነው። በዘመቻ መልክ ብዙ እንደሠራን ይሰማናል። ግን በዘመቻ ሲሠራ ሁሌ ሩጫ ነው። እውነቱን ለመናገር ለሴታዊትም የሚያዋጣ አካሔድ አይደለም። ምንም ገንዘብ አናገኝበትም፤ ራሳችንን ለማቆየትም ይከብደናል። ስለዚህ እየቀየርን ነው፤ አትኩሮታችን የሚሆነው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ሆኖ ጾታዊ ጥቃት ላይ መሥራታችን ይቀጥላል።

በአዲስ መልክ እየተዋቀርን ነው። ከፈረንጆች አዲስ ዓመት በኋላ ብዙ የምንሠራቸው ነገሮች ይቀየራሉ። የውስጣዊ መዋቅር ለውጦች ይኖራሉ፤ ሌላም በጎን የምንሠራቸው የሚቀጥሉ እንዳሉ ሆነው። ለምሳሌ አዲሴት ሁሉም መጠቀም የሚችሉት ስፍራ ነው፤ ልጆች ማምጣት ይቻላል። ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወንዶችም ሴቶችም አገልግሎት የሚያገኙበት ነጻ የስልክ መስመርም ይጀመራል። ስለዚህ ከዘመቻ ብቅ ጥልቅ፤ ትንሽ ጠለቅ ያለ ሥራ ወደ መሥራት እየገባን ነው።

ማኅበረሰቡ ፌሚኒዝምን እንዴት የተረዳው ይመስልዎታል? ከባህር ማዶ የመጣ እሳቤ ተደርጎ ስለሚወሰድም ኢትዮጵያዊ ማድረግ ያስፈልጋል ይባላል፤ እና በዚህ ላይ የሴታዊት ግብረ መልስ ምን ይመስላል?
ኅብረተሰቡ ምን ይላል የሚለውን ራሱን መጠየቅ ይሻላል፤ ብዙ ነገር በየቀኑ ይባላል። ግን ከአውሮፓ የመጣ የሚለውን እርግጠኛ አይደለሁም። ምክንያቱም ፌሚኒዝም በምንም ዓይነት ምልከታ ቢታይ የጾታ እኩልነት ንቅናቄ ማለት ነው። ወንዶችና ሴቶች እኩል እንደሆኑ ማመን፣ ከማመን አልፎ ለእኩልነት መታገል ነው። ወንዶችም ሴቶችም ፌሚኒስት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ብዙ ዓይነት ፌሚኒዝምም አለ።

የጾታ እኩልነትና የፍትሕ ጥያቄ ከአውሮፓ መምጣቱ ግን በጣም ጥያቄ ያስፈልገዋል። ማንም አውሮፓዊ ሳይጽፍ በፊት ስለ እኩልነት ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ ነበር በሐተታው የጻፈው፤ ማንም አውሮፓዊ ሳያስበው በፊት ማለት ነው።

በግሌ ፌሚኒዝምን የተማርኩት ከአያቴ ነው። እንግሊዘኛም ሆነ አማርኛ ማንበብ የማትችል አያቴ ለሴቶች መቆም፣ ሴቶችን መደገፍ፣ ራስን ማክበርና ማስከበርን ያስተማረችኝ እርሷ ናት። ከአውሮፓ መጣ የሚለው አያስማማም፤ ከዛ መጣ ከተባለም ያስፈልገን ነበር ማለት ነው። ግን ከዛ እንደመጣ አላምንም። የፍትሕን የእኩልነት ትግሎች እኛ አገር ከድሮም አሉ።

ኢትዮጵያዊ የሚያደርገው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ስለተሠራ ነው። ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ሴቶች እንወክላለን ወይ? ከተባለ አንወክልም። እኛም እንወክላለን ብለን አናውቅም።

ብዙ ዓይነት ፌሚኒዝሞች አሉ። ኬንያ ለምሳሌ ሦሰት አራት አለ፤ ናይጄሪያም እንደዛው፤ የእስላም ፌሚኒዝም፣ የክርስትና ፌሚኒዝም የሚባልም አለ። በአሜሪካ 100 ዓይነት ፌሚኒዝም ይገኛል። ሌላ አንድ ፌሚኒስት እየጨመርን ነው ነው የምንለው። እኛ ብቻ ነን ያለነው አይደለም የምንለው፤ እኛ ፈጠርነውም አንልም። ግን አሁን ባለንበት ጊዜ በፌሚኒዝም መርህ የእኩልነት ሥራ እየሠራን ነው ነው የምንለው።

ከሌሎች በሴቶች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ የሙያ ማኅበራት ጋር ሴታዊት ያላት ግንኙነት እንዴት ነው?
በሴቶች ጉዳይ የሚሠሩ የሙያ ማኅበራት ጋር፣ ለምሳሌ ከሴት ጋዜጠኞች ማኅበር ጋር በሆነ ፎረም ተገናኝተናል። ነገር ግን መደበኛ አይደለም። በማንዴት ደረጃ ሴቶችን ከሚወክሉ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ሴት ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር፤ የኢትዮጵያ ሴት ማኅበራት ቅንጅት ጋር ጥሩ እንሠራለን ብለን እናምናልን። “የሎው ሙቭመንት” አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለ ከእኛ ቀደም የሚል ፌሚኒስት ንቅናቄ ነው፤ ከእነርሱም ጋር ጥሩ እንሠራለን።

ከወንዶችም ጋር እንደዛው። ተራማጅ ብለን የምናያቸው ትምህርት ቤቶችም አሉ፤ አብረናቸው የምንሠራ፤ ድርጅቶችም በተመሳሳይ። ስላለን ቅርበትና ግንኙነት ነው እንጂ አብሮ መሥራት የግድ ነው።

የሴታዊት እንቅስቃሴ ለምን በከተማ ብቻ ታጠረ?
አዲስ አበባ ላይ በብዛት መሥራታችን ጥያቄ የለውም። አዲስ አበባ ነው ያለነው፤ አብዛኛው የበጎ አድራጎት ማኅበር እዚህ [አዲስ አበባ] ነው የሚጀምረው። ከአዲስ አበባ ውጪ የጀመሩ እንደውም ጥቂት ናቸው። ግን መሥራት እንዳለብን እኛም እናምናለን። ቅስቀሳዎች በሙሉ ከአዲስ አበባ ወጥተዋል። “አሪፍ አባት” አዲስ አበባም መቀሌ ሠርተናል። “ምን ለብሳ ነበር?” ም ከአዲስ አበባ ወጥቶ እየዞረ ነው።

ከዛ ውጪ ብዙ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ የሴቶች የትምህርት ዕድል መርሃ ግብር አለ። ሴት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ጥናታዊ ሥራዎችን አይሠሩም፤ አይጽፉምም። በሥራቸውም ሲገፉ አናይም። እና ከእንግሊዝ አገር ካለ “ዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን” ጋር በመተባበር የሴቶች ትምህርት ዕድል መርሃ ግብር (ስኮላርሺፕ ፕሮግራም) አለን። በእኛ በኩል የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ፤ በሌላም መልኩ ይደገፋሉ። አሁን ያቀድነው የሴቶች ኮንፈረንስ አለ፤ የዚህ ወር መጨረሻ ላይ ይሳተፋሉ። እነዚህን የምንሠራው ከአምስት የክልል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው።

የተጠቀሱት ሁሉ አሁንም ከተማ ላይ ነው። መቀሌ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር ወይም ሀሮማያ፤ አብረናቸው የምንሠራው ከተሞች ናቸው፤ ከዛ አልፎ ወደ ገጠር ለመሔድ እየሞከርን ነው። የውስጣዊ መዋቅር ለውጥ አድርገን አዲስ ፕሮጀክት ስንሠራ ንቅናቄን የማስፋት ነገር አንዱ ነው። አዲስ አበባ ጥቂት ሴቶች ተቀምጠን በቂ ለውጥ እያመጣን እንዳልሆነ እናምናለን። ብዙዎች ይተቹናል፤ ስለተቹንም ብቻ ሳይሆን እኛም የበለጠ ነገር ማድረግ ስለምንፈልግ ወደ ገጠር የማንቃት ሥራዎችን እየሠራን ነው።

ሴታዊት ላይ ሴቶች ሰብሰብ ብለው የሚነጋገሩበት ክበብ አለ። በማኅበራዊ ኑሯችን ደግሞ ሴቶች እርስበርስ አይስማሙም የሚል ነገር እንሰማለን። ይህን የሴታዊት ክበብ ወደታች ለማድረስ የተሠራ ነገር ይኖር ይሆን?
ሴቶች ቁጭ ብለው መወያየታቸው የሴታዊት የልብ ትርታ ነው። ብዙ መፍትሔ ይመጣል። ሴቶች ብዙ አይስማሙም የሚለውን ነገር እኛ በሕይወታችን አላየነውም፤ በግሌ አላየሁትም። እውነት ለመናገር ሥም ማጥፋት ነው የሚመስለኝ። በሕይወት ማንም ሰው ከሰው ጋር ሊጣላ ይችላል፤ ሴቶች የበለጠ ከሴቶች ጋር ይጣላሉ የሚለውን በግሌ አልቀበልም፤ በሴታዊትም እንደዛ አላየንም።

ክበቡን ማስፋት የሚለውን ከትምህርት ቤቶች ጋር የምንሠራው ፕሮጀክት ነበር። ኹለት ሺሕ ተማሪዎች አዲስ አበባ ላይ ደርሰናል። ወላይታና ጎንደር ትምህርት ቤቶች ላይም የሚሠራ አለ። እሱ ላይ አንድ ጠንካራ የትምህርቱ አካል እህትማማችነት ማጎልበት ነው። የምንሰጣቸው መልመጃዎች አሉ፤ ደራሲት ሕይወት እምሻው የጻፈችው አንድ ተረት አለ፤ እና እሱን አንብቦ እሱ ላይ የመወያየት ነገር አለ።

እህትማማችነት ማጎልበት ከሴታዊት የሥራ መርሆዎችም አንዱ ነው። አዶዬ እንለዋለን፤ አዶዬ የአፋን ኦሮሞ ቃል ነው። ያላገቡ ሴቶች ወጣቶች እርስ በእርስ በጣም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት እና ጓደኝነታቸው አዶዬ ይባላል፤ እርስ በእርስም አዶዬ ይባባላሉ። እሱን ወደ እኛ አምጥተን አዶዬ አንደኛው መርሃችን ሆኗል፤ ሴቶች መደጋገፍ አለባቸው የሚለው። ሰለዚህ ይህን ሥራ ወደ ገጠር ለመውሰድ ስንሞክር አንድ የምንሠራበት መንገድ እሱን ይመስለኛል።

ሴቶች ተገናኝተው መወያየታቸው አልቀረም። ቡና ሲጠጡ፣ በእቁብ፣ በእድርና በማኅበር ይገናኛሉ። ግን ይህን ወደ ሰፋ ነገር እንዴት ነው የምናመጣው፤ ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር እንዴት ነው የምናገናኘው ነው። ተሰብስበው የሚያወሩት ቁምነገር አይደለም ማለት ሳይሆን እንዴት ነው ወደ ሌላ ነገር ልንወስደው የምንችለው የሚለውን ገና እየፈተሸነው ነው። በኤች አይቪ ብዙ ነገር በእድርና በእቁብ ተሠርቶ ስኬታማ ነበር፤ ስለዚህ ተመሳሳይ ነገር ብንሠራ ደስ ይለናል። ግን ገና እየፈተሽን ያለው ነገር ነው።

በስሂን ሕይወት አጋጣሚ ትዳር፣ ልጅ እና የትምህርት ዕድል እኩል መጥተዋል። ያ ጊዜ እንዴት ነበር?
ከባድ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ክረምት ነው የሆነው። በአንድ ወር ውስጥ በጣም የምፈልገውና በየዓመቱ የምመኘው የትምህርት ዕድል ነበር። በቀላል አይደለም ያንን ዕድል ያገኘሁት፤ በጣም ውድድር የሚጠይቅ ነው። ያኔ ለኹለት ሰው ብቻ ነበር የሚሰጡት፤ አሁን እንደውም አንድ ሆኗል። በወቅቱ እጮኛዬ ነበር፤ ያን ሰሞን ነው ለመጋባት የተነጋገርነው። እርግዝናም የመጣው ያኔ ነው።

ሁሉንም እፈልጋለሁ፤ እንደ ልጅ የምፈልገው ነገር የለም። ትምህርትና ትዳሩንም እፈልገዋለሁ። እናም አብሮ ማስኬድ ከባድ ነበር።

ታድያ እንዴት አለፈ?
ያው ማለፍ ስላለበት አለፈ። እንግሊዝ አገር ለትምህርት ልሔድ ኹለት ቀን ሲቀረኝ ነው እርግዝናዬን ያወቅኩት፤ አንድ ሰው የማላውቅበት አገር ነው! የመጀመሪያ እርግዝና ደግሞ ያስፈራል፤ ምን እንደምትሆኚ አታውቂምና ሻንጣ ብሸከም ራሱ ልጄን የማጣ ይመስለኛል። ቁጭ ብዬ ነበር የማድረው፤ አንድ ነገር ብሆን ማን ይደርስልኛል ብዬ ስለምፈራ። ከባድ ወራት ነበሩ፤ ብቸኝነትም አለ። ትምህርቱንም እንደፈለግሁ ልማር አልቻልኩም። እርግዝናዬ ከባድ ስለነበር ቤተመጻሕፍት ላጠና ገብቼና መጽሐፍ ደርድሬ እተኛ ነበር፤ ተነስቼ ቤት ሔጄም እተኛለሁ።

በተለይ መጀመሪያ ወራት ከባድ ጊዜ ነበር። የምነግረው ጓደኛም አልነበረም። ወደ ፒ ኤች ዲ ለማለፍም ፈተና ነበር፤ እንዴት እንዳለፍኩ ራሱ አላውቅም። ልጄ ደግሞ ከታሰበችው ከ3 ሳምንት ቀድማ መጣች። እና በአጋጣሚ እናቴ ለንደን መጣችልኝ ልታግዘኝ። እርሷን ከተማውን ለማሳየት ዞር ዞር ስል ነው ምጥ የጀመረኝ፤ ተወለደች።
ስለዚህ ወደ ፈተና ስገባም እናቴና የባለቤቴ እናት ነበሩ ልጄን የሚይዙልኝ። ጡቴ ወተት ሞልቶ ያስቸግረኛል። ትምህርትም ስላልጨረስኩ ልጄን ክላስ ይዣት እገባ ነበር፤ በኹለተኛ ሳምንቷ። ቀላል አድርጌ ነበር የማየው፤ ቀላል ይመስለኝም ነበር። ግን ቁጭ ብለን እናድራለን ኹለታችንም።

ከዛ አዲስ አበባ ስመጣ ቀለለ። መመረቂያ ጽሑፌን ለመሥራት አዲስ አበባ ስለመጣሁ፤ እናቴም ስለምታግዘኝ፤ የልጄ አባትም ነበር። ኹለተኛ ልጄን ስወልድ ግን ትምህርቴን ለጊዜው አቆምኩ። ደግሞ ሞግዚት ኖሮኝ አያውቅም፤ ራሴ ነኝ የማሳድጋቸው።

ትንሹ ልጄ ትምህርት ቤት ሲገባ ነው ሴታዊት የተጀመረችው። ስለዚህ የሴታዊት እኩያ ነው። እዚሁ ነው ልጆቼም ያደጉት፤ ከትምህርት ቤት በኋላ ይመጣሉ። ሴታዊት ውስጥ ከሚገኙ ልጆቼን የቤት ሥራ ያላሠራ የለም፤ ሁሉም አክስት አጎት ናቸው፤ ያግዙኛል። በሴታዊት ያደጉ ልጆች ናቸው። ልጆች እያደጉ ሲሔዱ ደግሞ ይቀላል።

የወንዶችን አጋርነት በትዳር ሕይወት ውስጥ እንዴት ያዩታል?
ስለ አባቴ ልንገርሽ። ሁሉም ወንድ እንደ አባቴ ይመስለኝ ነበር። ያደኩት እሱን እያየሁ ነው። እናቴ በሦስት ዓመቴ ነው ሕክምና ትምህርት የጀመረችው። ሕክምና ደግሞ ረጅም ዓመት ይፈጃልና እስከ 13 ዓመቴ ተማሪ ነበረች። እና አባቴ ነው ቀጥ አድርጎ ያሳደገን። ሁሉም አባት እንደ እሱ ሚስትን የሚደግፍ፣ ተምራ ከእሱ የበለጠ እንድትሆን የሚፈልግ ይመስለኛል። እናቴ እንደተመረቀች ደግሞ ስፔሻላይዝ ማድረግ አለብሽ ብሎ ገፋፍቶ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻላይዝ አደረገች።

ለእኔ እንደ መሠረትና መለኪያ የማየው እንደ እሱ ዓይነት ወንድን ነው። የሴትን ከፍታ የሚያደንቅ፤ እንደፈተና የማያየው። ወንድሜም እንደሱ ነው። ስለ እሱ ከምትነግሪው ስለሚስቱ ብታመሰግኚለት ደስ ይለዋል። በጣም አርዓያ የሆኑ ወንዶች አሉ አካበቢዬ። ለዛም መሰለኝ ወንዶችን ከፍ አድርጌ የማየው። ሴቶችን ሲንቁና ሲያንቋሽሹ የበታች ሲያደርጉ የሚታዩ ወንዶች አካባቢዬ የሉም። በቢሮም የሥራ አጋሮቼ የሆኑ ወንዶች የገባቸው ፌሚኒስት ናቸው።

አሁን ለምሳሌ በፍቃዱ ኃይሉ [ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ቤተሰብ አንዱ] እኔ ከእርሱ ስለፌሚኒዝም እማራለሁ። እኔ ያላየሁትን ነገር ያያል። ይህ ትግል የሴቶች ብቻ ነው የሚለውን አንቀበልም። በሴቶች መመራት እንዳለበት እናምናለን። የሴቶችን መብት እኩልነትን የተቀበሉትም በሴት መመራት አለበት የሚለውን ይቀበላሉ።

ወደ ስርዓተ ጾታ እንዲቀርቡ ያደረገው ይህ አስተዳደግ ይሆን?
ያደግኩት ሁሉ ተሟልቶልኝ በፍቅር ነው። ግን ምንም ነገር ላይ ፍትሕ ሲጓደል፣ ውሻና ድመት ሲመታም ጭምር ይቆረቁረኛል። መፍትሔ ፈላጊም ነኝ። የሆነ ነገር አይቼ አላሳልፍም፤ በዛ ይመስለኛል። እናቴ ግን አራት አምስት ዓመቴ ሆኖ ፌሚኒስት ናት ትል ነበር። ምክንያቱም ለምሳሌ ወንድሜን “አታልቅስ ወንድ ልጅ አያለቅስም” ካለች ቀሚሴን ጎትተሸ ወንድ ካላለቀሰ ሴትም አታለቅስም ብለሻል ትለኛለች። 9 ዓመቴ አካባቢ አያቴ [የእናቴ እናት] ባለሙያ ነበረችና ሙያ ታስተምረኝ ተባለ፤ ምግብ መሥራት። ወንድሜ ካልተማረ እኔም አልማርም ብዬ ነበር።

ወላጆቼ ተራማጅ የሆኑና በእኩልነት የሚያምኑ በጣም የተማሩ ሰዎች ሆነው፤ ለእነርሱም ራሱ ግራ እየገባቸው ነበር። እና አባቴን “አንተ ግን የሴት መብት አታከብም” ብዬ ተናግሬው፤ በሰባት ወይም በስምንት ዓመቴ በጣም ሲስቁ አስታውሳለሁ።

እንግዲህ ፌሚኒስት ሆኜ ነው ራሴን ያገኘሁት ማለት ነው። እንጂ ለየት ያለ የጾታ እኩልነት ንቅናቄ ውስጥ አድጌ አይደለም።

የሴቶች ቀን በየዓመቱ ይከበራል፤ እንዴት ነው መከበር ያለበት?
እኔ ባይከበር ደስ ይለኛል። በሴታዊት አናከብረውም። ምክንያቱም እስከመቼ ነው አንድ ቀን መሰጠቱን የምናመሰግናው። አንድ ቀን የሚሰጠው ጥቂት ለሆነ የኅብረተሰብ አካል ብንሆን ነው፤ ለየት ያለ በሽታ ሲኖር ለዛን ቀን ግንዛቤ ስለሚያስፈልግ ያ ቀን ይከበራል። እና አስፈላጊነቱን ብዙ ፌሚኒስቶች ይከራከራሉ። ለምን ያስፈልጋል እንደሚሉም ይገባኛል። አንዱን ቀንም መጠቀምና ምን ያህል እንደሚቀረንና ምን ያህል እንደመጣን በማየት የማክበር ነገር ነው።
ግን ሥራ ነው የሚሆንብን። በየቀኑ እኩልነት ሥራ ስለምንሠራ ያንን ቀን ለይተን አናከብረውም።

አሁን ባለው አገራዊ ጉዳይ ላይ ሴቶች ምን ድርሻ መውሰድ ይችላሉ?
ይሔ ከባድ ጥያቄ ነው። ሴቶች ሲጀመር ፖለቲካ ላይ ሳይተሳተፉ ችግር ላይ መፍትሔ ስጡ ማለት ከባድ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የማይመቸኝ አንዱ ነገር ሴቶች አስታራቂ ናቸው የሚሉት ነው። የኅብረሰተብ አካል ነን’ኮ። ሲጣሉ ማስታረቅ የእኛ ኀላፊነት ከሆነ ከባድ ነው። ሴቶች ምን ያድርጉ ከሚለው ለሴቶች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ይደረግ ነው መጀመሪያ።

በቅርቡ በነበረው ብጥብጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 86 ተብሎ ሲጠቀስ፤ ከዛ ውስጥ 4 ሴቶች ናቸው። አራቱስ እንዴት ሞቱ ብለን ስንነጋገር ነበር። የትም አገር በጦርነትም ተገድለው የሚሞቱ ብዙ ጊዜ መጀመሪያ ወንዶች ናቸው፤ ወታደርም ስለሚሆኑና ፊት ለፊት ስለሚገኙ። ግን ሴቶች ላይ የሚደርሰው ደግሞ የከፋ ነው። አስገድዶ መድፈር ሰምተን በማናውቀው መንገድ ነው። በዚህ ግጭት ላይ ባንሰማም ጌዴኦ እና ጉጂ እንዲሁም ቡራዩ በጣም የሚሰቅ፣ ለማስማት የሚከብድ በቡድን መድፈር፣ ሕፃጻናትን ዕድሜያቸው 5 እና 9 የሆኑ ልጆችን አስገድዶ መድፈር እያየን ነው።

እና ሴቶች ባልተሳተፍንበት እርቅ አምጡ ብሎ መጠየቅ በምን ክፈተት ነው ያቺ ሴት አስታራቂ የምትሆነው። በተቻለ መጠን ከብሔርተኝነት እና ብጥብጥን ከመደገፍ መቆጠብ ሁላችንም ማድረግ ያለብን ነገር ነው። ግን እርቅ አምጪዎች አድርጎ ሴቶችን ማየት አደጋ ያለው ይመስለኛል፤ ትክክልም አይደለም። ያልተሰጠን ፖለቲካ ዓውድ ውስጥ አንድ ቀን አስታውሶ ኑ ሳይሉ ደጋግሞ ሴቶች ማስታረቅ አለባቸው የሚለው ነገር መፈተሽ ያለበት ትርክት ይመስለኛል።

እንደ አገር አጣብቂኝ ውስጥ በገባንበት ወቅትስ ምን ዓይነት ድምጽ ነው ማሰማት የሚቻለው?
እንደዛ ዓይነት አስተያየት ደርሶን ነበር። ከኢዜማ ጋር ባደረግነው ስብሰባ፤ “እናንተ ስለሴቶች ተሳትፎ ታስባላችሁ፤ አገር እንዲህ እየሆነች” ይላሉ። ግን የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ያሳየንን ሁኔታ ነው ያየነው። በፖለቲካው ሴቶች ቢበዙ እንደዛ ዓይነት ነገር አናይም ነበር። ሴቶች ወጥተው ሲደበድቡ፣ ድንጋይ ሲወረውሩ አናይም። መፍትሔው ላይ እየሠራን እንደሆነ ነው የምናምነው። መፍትሔው ነገ የሚመጣ አይደለም። ሴቶች ለመማር ዕድል ሲኖራቸው፣ የራቸውን መብት መጠየቅ ሲጀምሩ፣ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ ሲኖራቸው ይህም ብሔርን ወክሎ ሳይሆን ለራስ መሳተፍ ሲጀምሩ እኛ የምሠራው በሙሉ ወደዛ የሚያመጣ ይመስለኛል።

አሁን ባለው ሁኔታ ማናችንም ምንም መሥራት አንችልም። አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ናቸው ጥፋተኞች፤ አብዛኛው ኅብረተሰብ ተጠቂና ተጎጂ ወይም ዝም ብሎ የሚያይ ነው። እናም ከሴቶች የሚጠበቀው እንደሌላው ማኅበረሰብ ማውገዝ፣ ብሔርተኝነትን መፈተሽሽ ወንድነትን መፈተሸ ነው። ፌስቡክ ላይ ለምሳሌ የለሁም፤ መርዛማ ቦታ ሆኖ ስላገኘሁት። ሌሎች ማኅበራዊ ገጾች ላይ ግን ሴቶች እኩል ብሔርተኛነትን ሲያቀነቅኑ ይታያል። ወይም ወንዳዊ በሆነና ወደ ጥቃት ሲወስድ በሚታይ መንገድ አብረው እየሔዱ፤ ግደለው ተደራጅ ሲሉ ይታያል። እነዚህ ሴቶች እኩል መጠየቅ አለባቸው ማለት ነው፤ ራስን የመፈተሸ ነገር ነው በአብዛኛው።

በመጨረሻ የሚተላለፍ መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥ፤ አሁን ላይ የአገር ሁኔታ ሴቶችን ሲያንገበግባቸው፣ ሴቶች ለሃይማኖታቸው እና ለብሔራቸውም ሲቆረቆሩ እናያለን። ከሁሉ በፊት ግን ማንነት ሴቶች እንደሆኑ ቢያስተውሱ ደስ ይለኛል። ስንጠቃም እንደ ሴቶች ነው፣ መንገድ ላይ ስትለከፊም እንደዛው። መጀመሪያ ማንነት ጾታ መሆኑን ቢያውቁና ቢያስታውሱ። እና ለራስ ለእኩልነትና ለፍትሕ መሥራት እንደዚህ ሊያሰጋ አይገባም። ብዙ አክቲቪስቶችን ለማናገር እንሞክራለን፤ ስለ ብሔር ይጽፋሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይተቻሉ፤ ግን ስለ ስርዓተ ጾታ ጻፉ ሲባሉ ይፈራሉ። ከምንም ማንነት በፊት ይህ ማንነት እንዳለ እንድናስታወስ የሚለው ነው የእኛ መልዕክት። ብዙ ትችት የሚደርሰን ከሴቶች ነው፤ እሱን መፈተሸ ያስፈልጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here