አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በ2014 የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስደው በልዩ ኹኔታ በሪሜዲያል ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች ፈተና ተዘጋጅቶ እንዲላክና አጠቃላይ ሂደቱ እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል።
ፈተናውም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተሰጠው ትምህርት መሠረት ከማዕከል በጋራ ተዘጋጅቶ ለተቋማት መላክ እንዳለበት አመላክቷል።
በዚህም መሰረት በሴሚስተሩ በተሰጠው ትምህርት የተቋማት የውስጥ ፈተና ውጤት 50 ከመቶ እንዲሁም በማዕከል የተዘጋጀው ፈተና ውጤት 50 ከመቶ እንደሚያዝ ተገልጿል።
ተማሪዎችም በ2016 ትምህርታቸውን ለመከታተል ብቁ ሆነው ለመገኘት የኹለቱ ድምር አማካይ 50 ከመቶና በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስቴሩ አመላክቷል።
ዩኒቨርሲቲዎችም ፈተናውን በማስተዳደርና ውጤት በመግለጽ በ2016 የፍሬሽማን ፕሮግራም ለመከታተል ብቁ የሆኑ ተማሪዎችን ለይተው እስከ ሰኔ 30/2015 እንዲያጠናቅቁ ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን ሥራ በማጠናቀቅ የ2016 የትምህርት መርሐ ግብር የተስተካከለ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።



