በፋኖና በመከላከያ መካከል በተደረገ ውጊያ በትንሹ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

0
851

አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ዙሪያ ራሳ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ ረቡዕ ግንቦት 92015 በፋኖ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በትንሹ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በሸዋሮቢት ዙሪያ እና አካባቢዋ በተደረገው በዚህ ውጊያ ንፁሃን ዜጎች የሞት ሰለባ ሁነዋል የተባለ ሲሆን፤ ሰላማዊ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው መሄዳቸው ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ በአገር መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ መካከል በተከፈተው ጦርነት ሌሎች የሸኔ አባላት እና የአካባቢው ነዋሪዎችም ተሳትፈዋል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን መካከል በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን ተናግረዋል።

በአካባቢው ሲካሄድ በነበረው የተኩስ ልውውጥ የከባድ መሳሪያ ድምፅ ይሰማ እንደነበርም ነው ለማወቅ የተቻለው፡፡

በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በየወቅቱ የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ቤት እየተቃጠለ፣ ሃብት ንብረት እየወደመ የቀጠለ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥቱ በዘላቂነት ሊያስቆመው ባልመቻሉ በርካታ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እንዳስገደዳቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ከሦስት ጊዜ በላይ በአካባቢው ጦርነት ተካሂዶበታል የሚሉት የራሳ እና ግድም ነዋሪዎች፤ በአካባቢው ሰላም ያስከብራሉ ተብለው የተመደቡ የአገር መከላከያ ሰራዊት የንፁሃንን ሕይወት ከመጥፋት አልታደጉም ብለዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here