ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ ተፈቀደ

0
826

በገጠርም ሆነ በከተማ በሚደራጁ የአነስተኛ የፋይናንስ ሥራዎች ላይ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች እንዳይሳተፉ ከልክሎ የነበረው አዋጅ ተሻሻለ።
የሕጉን እገዳ በማንሳት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በመፍቀድ በአገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሰብ አዋጁ እንደተሻሻለ ለማወቅ ተችሏል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በባንክ ሥራ፣ በመድኅን እንዲሁም በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ድርሻ እንዳይኖራቸው ተከልክሎ የቆየ ሲሆን እነዚህን ሕጎች የማሻሻል ሥራ ባሳለፍነው ሳምንት በፀደቁ ሕጎች ተጠናቋል።

አዋጁ በተጨማሪም የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ላይ ብቻ ተገድበው እንዲቆዩና የሚሰጡት የብድር አገልግሎት ማደግ እንዳይችል አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ማሻሻያው በማንኛውም ምርታማ የሥራ መስክ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ መብት የሰጠም ነው ተበሏል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በከተማ በግብርና ሥራ እና በሌሎች ሥራዎች ላይ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ እንዲያበድሩ እና በተለይም በድህነት ቅነሳና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ የገደበ ነበረ። ከዚህም በተጨማሪ በዲጂታል ዘዴዎች የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፤ ወኪል ባንኪንግ አገልግሎት እና ከወለድ ነፃ አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አገልግሎት እንዲሰጡ ረቂቁ ይፈቅዳል።

በዘርፉ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ አካላት ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ማሻሻያ ነው ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናፈቁሽ ደሴ ናቸው።

ማሻሻያው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ውድድር የመፍጠር አቅም እንዳለው በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ባለሙያ ተኬ ዓለሙ (ዶክተር) ጠቅሰዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት አቅም እጅግ ከፍተኛና ከባንኮች ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችል በመሆኑ ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን መከፈቱ በገንዘብ አቅማቸው ላይ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም። የተነሳው እገዳ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ማደግ የሚገባውን ያህል እንዳያድግ ገድቦት የቆየውን የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር እንደሚረዳም ባለሞያው ተናግረዋል።

ብሔራዊ ባንክ የምጣኔ ሃብት ዕድገቱን የመቆጣጠር አቅሙን እያሳደገ በመምጣቱ እነዚህ ተቋማት የአገልግሎት አድማሳቸውን አስፍተው ቢንቀሳቀሱ ለቁጥጥር የማያስቸግር በመሆኑ አዋጁ የተቋማቱን አቅም ከፍ ባደረገ መልኩ እንደተዘጋጀ ለምክር ቤቱ ተገልጿል።

ዘርፉን በተወሰነ መልኩም በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊን መከፈቱ የሚያመጣው የፋይናንስ ደኅንነት ወይም ወንጀል ድርጊት ተጋላጭነት ካለም ለመከላከል የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል ቁጥጥር ማእቀፍ ስር መውደቁ ታውቋል።

በአሁኑ ሰዓት ከ 38 በላይ የሚልቁት የፋይናንስ ተቋማት ከ 15 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ከኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማኅበር አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ አንጋፋ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የፋይናንስ አቅማቸው ከብዙ አዳዲስ ባንኮች ጭምር የተሻለ እየሆነ ቢመጣም ያላቸውን ትልቅ አቅም ግን በትልልቅና የተሻለ ትርፍ ሊያመጡ በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ማፍሰስ ባለመቻላቻው የሕግ ማእቀፍ በማዘጋጀት ወደ መደበኛ የባንክ ሥራ እንዲገቡ ለመፍቀድ መታሰቡን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

በአጠቃላይም አምስት ሚሊዮን የብድር ደንበኞች ያሏቸው ሲሆን የቁጠባ ደንበኞቻቸው ግን ከተበዳሪዎቻቸው ጋር የማይመጣጠኑ ናቸው። ተቋማቱ ያበደሩት ጠቅላላ ገንዘብ በ32 በመቶ እያደገ 51.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ካፒታላቸው ግን 15.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ሆኖ ተቀማጭ 38.4 ቢሊዮን ብር እና ጠቅላላ ሀብታቸው ደግሞ 76.6 ቢሊዮን ደርሷል። የባንኩ መረጃ እንደሚያሳየው ንግድ ባንክን ጨምሮ ያሉት 17 ባንኮች ያላቸው የቁጠባ ሂሳብ ደንበኛ ግን 50 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የብድር ደንበኞቻቸው ግን 215 ሺሕ ብቻ ናቸው።

አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የሚቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገለግሉ ሲሆን ባንኩ እንደክፍተት ከለያቸው ነገሮች መካከልም የቡድን ትወውቅን እንደ ብድር ማስያዣ መጠቀም አንዱ ነው።

አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚሰጡት ብድር እድገት ከፍተኛ ሲሆን የመመለስ መጠኑ ግን እያነሰ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታውቆ ነበር። በሌላ በኩል የባንኮች ጠቅላላ ሀብት 1.1 ትሪልየን ብር የደረሰ ሲሆን ካፒታላቸውም 90 ቢሊዮን ብር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here