በመጪዎቹ ሳምንታት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተገለፀ

0
732

በመጪው ኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሌ እና አማራ ክልሎች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ እና በጥቂት ቦታዎችም ላይ ከመደበኛው በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ሲል የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የገለፀ ሲሆን፣ በዓለማቀፍ ተቋማት የጎርፍ አደጋ ሊኖር ይችላል በሚል የሚወጡ መረጃዎችን አስተባበለ።

ዓለማቀፉ የስደተኞች ተቆጣጣሪ ተቋም ባወጣው መረጃ፣ በመጪዎቹ ሳምንታት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ እንዲሁም ከ አምስት መቶ ሺሕ በላይ ዜጎችን ካፈናቀለው የጥቅምት ወር አደጋ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ተተንብይዋል። በታሪክ ከፍተኛ ሆኖ በተመዘገበ ሙቀት ምክንያት በህንድ ውቂያኖስ ላይ ያጋጠሙ ለውጦች ከፍተኛ የዝናም መጠን እና መጥለቅለቅ ለአደጋው መከሰት እንደ ምክንያትነት አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በበኩሉ ግን የአገሪቱ አብዛኛው ከፍሎች የበጋው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ላይ ሆነው እንደሚቆዩ ይጠበቃል ያለ ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ዞኖች በተለይም ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢለአባቦራ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌን ጨምሮ የቦረና እና የጉጂ ዞኖች መደበኛ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል ሲል አስታውቋል።

ከድሬዳዋና ሀረሪ በተጨማሪም የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉሙዝ አንዳንድ የዝናብ ስርጭት ያገኛሉ። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የከፋ፣ የቤንች ማጂ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዲኦ እና የሰገን አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ያገኛቸዋል። በሶማሌ ክልል ደጋሀቡር፣ ፊቅ፣ ቀብሪዳሃር፣ አፍዴር፣ ሉበን እና ጎዴ ይገኙበታል ሲል ኤጀንሲው ገልጿል።

ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ፣ የሸዋ ዞኖች፣ ጥቂት የምሥራቅ ጎጃም ዞኖች እንዲሁም በትግራይ ክልል የምሥራቅና የደቡብ ትግራይ ዞኖች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን የተቀሩት የሀገሪቱ ሥፍራዎች ደረቅ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።
‹‹የዝናብ ስርጭቱ ዓለማቀፉ የስደተኞች ተቆጣጣሪ ተቋም ባወጣው መረጃ ልክ ሰዎችን የሚያፈናቅል እና ለአደጋ የሚጥል ከባድ የዝናብ ስርጭት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም›› ሲል ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ የላከው መልስ ያስረዳል።

በአብዛኛው የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ጠባይ እንደሚስተዋል የሚጠበቅ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ የሰሜን፣ የምሥራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ በቀጣይ ቀናት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ገናሌዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ኦጋዴን፣ የመካከለኛው እና የታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣ የአባይ ደቡባዊው ክፍል እንዲሁም በባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ላይ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ እና በጥቂት ቦታዎችም ላይ ከመደበኛው በላይ የዝናብ መጠን ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል። በተመሳሳይም በጥቂት የምሥራቃዊ አባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በመሆኑም ዝናብ በሚያገኙ ተፋሰሶች ላይ የሚገኘውን ውሃ ማኅበረስቡና በውሃ እንቅስቃሴ ላይ የሚሠሩ ተቋማት በተቻለ መጠን በአግባቡ በመያዝ አገልግሎት ላይ ሊያውሉት ይገባል ሲል ኤጀንሲው አሳስቧል።

የብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፣ በቀጣይ ወራት በኢትዮጵያ ሰብል የሚሰበሰብበት ፀሐያማ ወቅት እንደሚሆን ይጠበቃል ያለ ሲሆን፣ በአደጋ ደረጃ የሚያሰጋ እና በተጠቀሰው መጠን ሰዎችን ሊያፈናቅል የሚችል የደመና ስርጭት ባለመኖሩ በተቋሙ የተሰጠው መረጃ የተጋነነ ነው ብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here