የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ምዝገባ እና ቅስቀሳ ተጀመረ

0
669

የሲዳማ ዞን ክልልነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ለመለየት ሐዋሳን ጨምሮ በሲዳማ ዞን መራጮችን የመመዝገብ ሥራ ጥቅምት 27/ 2012 የተጀመረ ሲሆን የምርጫ ቅስቀሳዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ለሕዝበ ውሳኔው በተካሄደው ዝግጅትም ከስድስት ሺሕ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ወስደው ተሰማርተዋል። ከኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በክልል ደረጃ የመጀመሪያው በሆነው የራስን እድል በራስ የመወሰን ሂደት፣ በተለይም የክልልነት ውሳኔውን የሚያበረታቱ ቅስቀሳዎች ጎልተው መታየታቸውን በስፍራው የተገኘው የአዲስ ማለዳ ባልደረባ አረጋግጧል።

ኅዳር 10/ 2012 ለሚካሄደው ውሳኔ በሐዋሳ ከተማ እና በሲዳማ ዞን አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባው በስፋት እየተካሄደ ሲሆን፣ ለተከታታይ ዐስር ቀናት የሚቆይ ይሆናል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የመራጭነት ምዝገባው በተጀመረበት እለት በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ቅስቀሳ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ወጣቶች በተሽከርካሪዎች እና በሞተር ሳይክሎች በመጠቀም የሻፌታ ምልክትን በማሳይት በከተማዋ የምርጫ ቅስቀሳ በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የድርጊት መርሀ ግብር ላይ፣ ቦርዱ ኹለቱ የሕዝበ ውሳኔው አማራጭ ሐሳቦች የሚወከሉበትን አማራጭ ምልክቶች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ከሲዳማ ዞን ምክር ቤት ጋር ምክክር በማድረግ ኹለት ምርጫ መለያ ምልክቶችን መስከረም 12/ 2012 ይፋ አድርጎ ነበር።

“ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጎጆ ቤት ምልክት፣ እንዲሁም “ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለሕዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫነት እንዲያገለግል የተወሰነ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

የሻፌታውን የምርጫ ምልክትም በባነር በማሰራት በተሸከርካሪዎች ላይ በመለጠፍ ‹‹ሻፌታን ይምረጡ›› በሚል ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይም ምልክቶቹ ተሰቅለው እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በአንፃሩ ጎጆ ቤት ምልክት የያዘም ሆነ ቅስቀሳ የሚያደርግ አካል አለመመልከታቸውን እና ቅስቀሳው ወደ አንዱ ተፎካካሪ ያመዘነ አድርጎታል ሲሉ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደስታ ለዳማ በበኩላቸው በዞኑ በምርጫው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ከሚጠበቁ 1.4 ሚሊዮን መራጮች መካከል ምዝገባው በተጀመረበት ቀን ብቻ 352 ሺሕ ሕዝብ መመዝገቡን ተናግረዋል። ይህም ከአጠቃላይ ቁጥሩ 20 በመቶ ይሸፍናል ያሉ ሲሆን ሕዝቡ በሚያሳየው ከፍተኛ ተሳትፎ ምክንያት ምዝገባው ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ሊጠናቅቅ እንደሚችል ገልፀዋል።

የምዝገባ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ እና መረጋጋት የተሞላበት ሆኖ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ሕዝቡ ከማለዳ ጀምሮ ወደ ምዝገባ ጣቢያዎች በመሄድ በመሰለፍ ሲመዘገብ መመልከት ተችሏል።

የከተማውንም ጸጥታ ለመቆጣጠር ከቀድሞው በቁጥር በርከት ያለ የክልሉ ልዩ ኀይል፣ ፌዴራል ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት በሐዋሳ እና በሲዳማ ዞኖች በብዛት መክተሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተማው ውስጥም በመንገድ ላይ ፍተሻዎች የሚደረጉ ሲሆን የመራጭነት ምዝገባው ከተጀመረበት ሰዓት አንስቶ ምንም አይነት የፀጥታ ችግረ አለመስተዋሉን የአዲስ ማለዳ ዘጋቢ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here