በደብረ ብርሃን ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ በርካታ ወጣቶች ለሕገወጥ ስደት ተዳርገዋል ተባለ

0
368

እሁድ ግንቦት 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከኦሮሚያ ክልል፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ እና ከአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ በርካታ ወጣቶች ለሕገወጥ ስደት መዳረጋቸው ተገለጸ፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች “ቁጭ ብለው አማራጭ ያጡ በርካታ ወጣቶች በዋናነት ወደ አረብ አገር በብዛት እየተሰደዱ ነው።” ሲሉ፤ በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

“ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ወጣቶች መንገድ ላይ መሞታቸውን ሰምተናል፣ ገብተናል ብለው የደወሉልንም አሉ” ያሉት ተፈናቃዮች፤ ቁጥራቸው የማይታወቅ ብዙ ወጣቶችም የደረሱበት እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ ወደ አረብ አገራት የሚሄዱት በየመን በኩል አድርገው ነው የተባለ ሲሆን፤ አሁንም ብዙ ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ ከአገር ስለመውጣት እንደሚያስቡ ተገልጿል፡፡

በከተማዋ 40 ሺሕ ገዳማ ተፈናቃዮች መኖራቸው በመጥቀስ፤ መንግሥት ከአራት ወራት አንድ ጊዜ የበቆሎ ዱቄት እና ዘይት እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሰሞኑን የበቆሎ ዱቄት እንደተሰጣቸው ገልጸው፤ “ይሁን እንጂ ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ እንጀራም ይሁን ገንፎም አድርገን ልንጠቀመው የማንችል ነው። ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች ከፍተኛ ረሃብ አለ የተባለ ሲሆን፣ ብዙ ቤተሰብ ያላቸው እናቶች እንዲሁም ሕጻናት ጎዳና ላይ ወጥተው እንደሚለምኑ ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም በቅርቡ ቻይና ካምፕ ተብሎ ወደሚጠራው መጠለያ ጣቢያ የገቡ ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎች፤ “በመንግሥት አልተመዘገባችሁም” በሚል ምንም ዓይነት እርዳታ ስለማያገኙ ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው ተገለልጿል፡፡

“መሄጃ ስለሌለን ቁጭ ብለናል።” የሚሉት ተፈናቃዮቹ፤ “ተፈናቅለን ከመጣንበት የወለጋ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሰዎች እየተገደሉ ስለሆነ ተመልሰን አንሄድም፡፡ መጨረሻችን ምን እንደሆነም የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በዞኑ ከ70 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ እንደሚገኙ እና የፌዴራል መንግሥቱ በችግሩ ልክ በቂ ድጋፍ እንደማያደርግ ጠቅሶ፤ የተፈናቃዮቹ ጉዳይ ከአቅሜ በላይ ነው ሲል ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ መግለጹ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here