ሐሙስ ሰኔ 1 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ 25 ሚሊዮን 385 ሺሕ 666 ብር የንግድ ትርፍ ፍሬ ግብርን አሳውቃ ባልከፈለችው ግለሰብ ላይ ክስ አቅርቦ በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ40 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ቅጣቱ የተላላፈባት እመቤት መላኩ የተባለች ተከሳሽ ጠቅሶ፤ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116/2/ እና 125/1/ን በመተላለፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 01 በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ተመዝግባ የንግድ ሥራ ስትሰራ መቆየቷን ገልጿል።
በዚህም በግብር ስወራ ወንጀል ከ2004 እስከ 2010 በተደረገው የምርመራ ኦዲት፤ ግለሰቧ ግብር ለመሰወር በማሰብ ግዥ ያልተፈጸመባቸውን 72 ሀሰተኛ ደረሰኞች ግዢ እንደተፈጸመባቸው በማስመሰል፣ በሂሳብ መዝገብ ውስጥ በማካተት ለግብር ሰብሳቢው ተቋም በማሳወቅ፤ የሚፈለግባትን አጠቃላይ የንግድ ትርፍ ግብር ፍሬ ግብር 25 ሚሊዮን 385 ሺሕ 666 ብር አሳውቃ ባለመክፈሏ በፈጸመችው የንግድ ትርፍ ግብር ስወራ ወንጀል ክስ እንደመሰረተባት ተገልጿል፡፡
ተከሳሿ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት ”የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም“ ያለች ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግም 2 የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሿ በቀረበባት ክስ መሰረት እንድትከላከል ብይን ተሰጥቷል።
በሰጠው ቀጠሮ መሰረትም ተከሳሿ 1 የመከላከያ ምስክር አቅርባ ብታሰማም የአቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻሏ፤ ትከላከል በተባለችበት ድንጋጌ ሥር የጥፋተኛ ፍርድ በመስጠት ፍርድ ቤቱ በ2 ዓመት ጽኑ እስራትና በ40 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ውሳኔ ማስተላለፉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።



