አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኹሉም መሳጂዶች ከቁኑት ዱዓ ውጪ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ ባለመሆናቸው ህዝበ ሙስሊሙ የተለመደ ታዣዥነቱን በማሳየት የጁምዓ ሰላቱን ሰግዶ ብቻ መመለስ እንዳለበት ኡስታዝ አቡበክር አህመድ አሳስበዋል።
ኡስታዝ አቡበክር በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አመራሮች ሼይኽ ሁሴን ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ፣ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እንዲሁም ከኦሮሚያ መጅሊስ ሼይኽ ሚስባ እና ሌሎች አመራሮች ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚኬኤል ጋር በትናንትናው ዕለት ውጤታማ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና እና ምክትል ኮሚሽነሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና ከፍተኛ የፀጥታ ሐይሉ አመራሮች መካፈላቸውን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ በሸገር ከተማ የፈረሱ መስጂዶችን ተከትሎ በኹለት ጁምዓዎች በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተወሰዱት ኢ ሰብዓዊ እና ከልክ ያለፉ የኃይል እርምጃዎች ተቀባይነት የሌላቸው እና ህዝበ ሙስሊሙን እጅግ ያሳዘነ መሆኑም ተገልጿል።
አገር ወዳድ እና ሰላማዊ ለሆነው ህዝበ ሙስሊም ህጋዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረቡ በምላሹ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደው የኃይል እርምጃ በምንም መመዘኛ የሚገባው እንዳልነበር እና ጥፋት እንደሆነ ለፀጥታ አመራሮቹ ማብራሪያ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በፀጥታ ኃይሉ በኩልም የሙስሊሙን ሕጋዊ ጥያቄ ሽፋን በማድረግ የራሳቸው አጀንዳ ለማራመድ የሞከሩ ኃይሎች መኖራቸውን መረጃ እንዳላቸው በማንሳት የነበራቸውን ስጋት መግለጻቸውም ተነግሯል።
በውይይቱ መቋጫ ላይም በኹለቱ ጁምዓዎች በተወሰደው የኃይል እርምጃ በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊሞች በሙሉ ከእስር በሚፈቱበት አግባብ ላይ ከስምምነት ላይ መድረስ መቻሉንም ኡስታዝ አቡበክር በመልዕክታቸው ያስታወቁ ሲሆን፤ ከሕግ አግባብ ውጪ የኃይል እርምጃ የወሰዱ የጸጥታ ሀይሉ አባላትም በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ ኮሚቴ ተዋቅሮ የማጣራቱ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ መገለጹን ተናግረዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ያቀረባቸው ሕጋዊ ጥያቄዎቹ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኩል መፍትሄ ለመስጠት ቃል በመገባቱ እና ይህም መፍትሄ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ህዝበ ሙስሊሙ በተለመደው ጨዋነቱ በትዕግስት በመጠበቅ ከመሪ ድርጅቱ መጅሊሱ ጎን በመቆም በተቋሙ የተሰጡትን መመሪያ እና የመፍትሄ አቅጣጫ በመተግበር እና በዱዓ በማገዝ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።
ስለሆነም፤ “በቀጣይ ባሉ ጁምዓዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር እና በዱዓ በመበርታት መደበኛ የጁምዓ ሰላቱን ብቻ እንዲያከናውን ጥሪ እናቀርባለን።” ሲሉ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።



