ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋሳናትን ድንበር መዝጋቷ ተገለጸ

0
808

አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኤርትራ ከኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ጋር የሚያዋሳናትን ድንበር መዝጋቷን የእንግሊዝ መንግሥት አስታውቋል።

የእንግሊዝ መንግሥት ኤርትራ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ድንበሯን የዘጋችበትን ምክንያት ያልገለጸ ሲሆን፤ በኤርትራ ግን የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት እንደሌለዉ ገልጿል።

የእንግሊዝ የውጭ የጋራ ደህንነትና እድገት ቢሮ፤ የብሪታኒያ ዜጎች ከኤርትራ ድንበር 25 ኪሎ ሜትር እርቀት ባላቸዉ ማንኛውም አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ፣ በኤርትራ የሚገኙ የእንግሊዝ ዲፕሎማቶችና ዜጎች አገሪቱን በቶሎ ለቅቀዉ እንዲወጡ እንዲሁም ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ያሰቡ ጉዟቸዉን እንዲሰርዙ አሳስቧል።

በተጫማሪም በኤርትራ የሚገኙ የእንግሊዝ ዜጎች ከታሰሩ፣ ጥቃት ከደረሰባቸው ወይም ከተገደሉ በአስመራ ለሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ደውለው እንዲያሳውቁ አስገንዝቧል።

በኤርትራ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ያሳሰባቸው የእንግሊዝ ዜጎችም ለመንግሥት እንዲያሳውቁ ተነግሯቸዋል።

በአንጻሩ ኤርትራ ከሱዳን ጋር የሚያዋስናት ድንበር ክፍት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የሱዳን ግጭት ከመጀመሩ አስቀድሞ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሸ ሃይሎች መሪ ጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ድንበር ዘግተው የኖሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸው መሻሻል አሳይቷል።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም የኤርትራ ጦር አባላት ከኢትዮጵያ መከላካያ ሰራዊት ጋር በመሆኑ በትግራይ ክልል ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር ሲዋጉ እንደነበር ሲነገር ቆይቷል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የኤርትራ ሃይሎች ከኢትዮጵያ ትግራራይ ክልል ሙሉ በሙሉ መውጣት ያለባቸው ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አሁንም ብዙ አካባቢዎች በኤርትራ ሃይሎች መያዛቸውን ይገልጻል።

ከቀናት በፊት የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት ለማበላሸት የሚጥሩ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ “ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።

ከሰሜኑ ጦርነት ማብቃት ወዲህ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት መሻሻል ማሳየቱ የሚገለጽ ሲሆን፤ ኤርትራም ከቻይናና ሩስያ ጋር ያላትን ግንኙንት ማጣናክሯ ይጠቀሳል።

በሌላ በኩል፤ በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው ከሚገኙ 130 ሺሕ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች “ታግተን ወደ ኤርትራ እንወሰዳለን” የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህም ብዙዎቹ ከዚህ ስጋት ለማምለጥ እንዲሁም በሱዳን ያለውን ቀውስ ሸሽተው በጎንደር በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here