አርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለ2016 የትምህርት ዘመን ምዝገባ፤ ወላጆች የልጆቻቸውን የልደት ምስክር ወረቀት የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ምዝገባውን ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በቅንጅት እያከናወነ እንደሆነም ገልጿል።
ኤጀንሲው “የልደት ምዝገባ ለኹሉም ተማሪ” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው ንቅናቄ በትናንትናው ዕለት የተማሪዎች የልደት ምዝገባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ኹለት አሳይ አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አከናውኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በአገሪቱ ከሥነ-ህዝብ ለውጥ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው በመሆኑ የሕዝብ ብዛትና እድገትን ማወቂያ መንገድ ነው። ይህም መንግሥት ለሚያከናውናቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እቅዶችና የአስተዳደራዊ አገልግሎቶች ዝግጅት የመረጃ ምንጭ ይሆናል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መብት በመሆኑ መንግሥታት ይህን መብት ለማስፈጸም አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያዛሉ። ይህም አገራት ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአዲስ አበባ ለ2016 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ወላጆች የልጆቻቸውን የልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
“በንቅናቄው ኹለት ጉዳዮችን እያከናወነ ነው። አንደኛ ለተማሪዎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚኖረውን ጠቀሜታ ማስገንዘብ ሲሆን፤ ኹለተኛ የልደት ምዝገባ ማከናወን ነው” ያሉት ዮናስ፤ መንግሥት ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ለማሟላት የወሳኝ ኩነት መረጃ ያስፈልገዋል፤ ለዚህም ለ2016 የትምህርት ዘመን ምዝገባ የልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ አስገዳጅ ሆኗል ብለዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ በበኩላቸው፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ “የልደት ምዝገባ ለኹሉም ተማሪ” በሚል መሪ ቃል በአሳይ አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልደት ምዝገባ መጀመሩን አብስረው፤ በአሳይ ትምህርት ቤት ብቻ ለአንድ ሺሕ ኹለት መቶ ተማሪዎች የልደት ምዝገባ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን አንድም ተማሪ ያለ ልደት ካርድ ምዝገባ እንዳይካሄድ ተወስኗል ያሉት ኃላፊው፤ በትምህርት ቤቶች የልደት ምዝገባ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ በክፍለ ከተማው በሚገኙ በኹሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ ገልጸዋል። በዚህም የልደት ሰርተፍኬት የሚሰጠው ከዚህ በፊት የልደት ሰርተፍኬት ለሌላቸው ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።



