ወጥቶ መግባት ብርቅ የሆነባት አገር!

0
896

ሰው በአገሩ፣ በሰፈሩ፣ በቀየው ወጥቶ የመግባት መብቱን ሲነፈግ፣ አልፎ ተርፎም ያለ አግባብ ሕወይወቱንና ንብረቱን በጉልበተኞች መቀማት በኢትዮጵያ የዕለት ከዕለት ተግባር ሆኗል፡፡

የሰው ልጅ አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆ በነጻነት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ይህ መብት በገጠርም ይሁን በከተማ አጣብቂን ውስጥ ከገባ ውሎ አድሮ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

ይህ አይነቱ ተግባር ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በሚነቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በዚሁ ክልል ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢው በትራንስፖርት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያመላክቱ እገታዎች አሁንም ቀጥለዋል፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ላይ ጭምር ሰዎች ከቤታቸውና ከሰፈራቸው በታጣቂዎች ታግተው የሚወሰዱበት ሁኔታ መፈጠሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ አዲስ ማለዳ በቅርቡ የሰራችው ዘገባ እንደሚያመላክተው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ ከተማ ይህ አይነቱ ድርጊቱ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው ሁኔታ ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የሚፈጸም የነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በየአካባቢው አጋች ኃይሎች መፈጠራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ድርጊቱ በየአካባቢው መስፋፋቱንና የተለመደ መሆኑን ተከትሎ፣ ገንዘብ መስብሰብን አላማ ያደረጉ በየአካባቢው የተደራጁ አጋቾች መፈጠራቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡

በኦሮሚያ ክልል እገታውን የሚፈጽሙት አካላት በመንግሥት “ኦነግ-ሸኔ” ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው፣ ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል አባላት መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ በየጊዜው በሰራቻቸው ዘገባዎች ላይ የታጋች ቤተሰቦችን ስታነጋግር የምታገኘው መረጃም ይህንን ያመላክታል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ራሳቸውን በሰፈር ያደራጁ ኃይሎች ገንዘብ የመሰብሰብ ዓላማ አንግበው በየአካባቢያቸው እገታ እየፈጸሙ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያሰባሰበቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተለይ በተደጋጋሚ እጋታ በሚፈጸምበት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ጎሃዮን፣ ገርበ ጉራቻ፣ ደራ፣ ሙከ ጡሬ፣ ደብረ ጽጌ፣ ግራር ጃርሶ፣እና ደገም የመሳሰሉ አካባቢዎች በየሰፈሩ ተደራጅተው ገንዘብ ለመቀበል የሚያግቱ ኃይሎች በስፋት ተፈጥረዋል ተብሏል፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች “ገንዘብ መሰብሰብን ብቻ ዓለማ ያደረጉ አካላት ተፈጥረዋል፣ አግተው ገንዘብ ሲጠይቁ ሸኔ ይባላሉ እንጂ ዓለማቸው ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ነው” ሲሉ ስለሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ የተስፋፋው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የሚፈጽመው እገታና ከፍተኛ ገንዘብ የመሰብሰብ ልምድ የተለመደ መሆኑን ተከትሎ፣ ወጣቶች ተደራጅተው ይህንኑ ተግባር የገቢ ምንጭ የማድረግ ተግባር ውስጥ ገብተዋል ተብሏል፡፡

ይሄው ተግባር ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አዳማ ከተማ ጭምር መፈጸም የጀመረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ስዓሊ ሙሉጌታ ገብረኪዳን በከተመዋ ታግቶ አጋቾቹ የጠየቅነው ገንዘብ ሳይሰጠን ዘግይቷል በማለት እንደገሉት ተሰምቷል፡፡ ገንዘብ መሰብሰብን አላማ ባደረጉ አጋቾች የሚታገቱ ሰዎች የጠየቁትን ገንዘብ በአስቸኳይ ካልከፈሉ በጭቃኔ የሚገደሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜም ገንዘብ ከፍለውም የሚገደሉበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የሚፈጽማቸው እገታዎች መጠነ ሰፊ ሲሆኑ፣ በብዛት የትራንስፖርት ተጓዦችን መንገድ ላይ ጠብቆ ማገትና በየአንዳንዳቸው ታጋቾች ገንዘብ መሰብሰብ ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰት ነው፡፡

እንደ ማሳያነት የቅርብ መሰል ድርጊቶችን ብንመለከት እንኳን፣ ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል በሚወስድዉ መንገድ ላይ ሰኔ 10/2015 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አሊደሮ በተባለ ቦታ በርካታ የጭነት መኪና አሽከርካሪ ሾፉሮችና ረዳቶች በዚሁ ታጣቂ ኃይል መታገታቸው ይታወሳል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ባደረገችው መጣራት ያገኘችው መረጃ እንደሚሚላክተው፣ 50 የሚደርሱ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው የእገታው ሰላባ ሆነዋል፡፡ ሹፌሮቹና ረዳቶቻቸው መንገድ ላይ ቀድመው በጠበቋቸው ተጣቂዎች ሲታገቱ፣ በቅርብ እርቀት የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አካላት መረጃ ቢደርሳቸውም “ከበላይ አካል ትዕዛዝ አልተሰጠንም” በማለት የታገቱ ዜጎችን ሊታደጉ አለመቻላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡  

የታጋች ቤተሰቦች በአጋቾች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የተጠየቁ ሲሆን፣ የተጠየቀው ግንዘብም በአንድ ግለሰብ አንድ ሚሊዮን ብር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡  አጋቾቹ የጠየቁትን ከፍተኛ ገንዘብ የመክፈል አቅም የሌላቸው የታጋች ቤተሰቦች፣ ሕዝብ እንዲያግዛቸው አደባባይ መውጣታቸው እና እናቶች ነጠላ አንጥፈው ጭምር እየለመኑ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡ ገንዘቡን የመክፈል አቅም ያላቸው ሰዎች የተየቁትን ገንዘብ ከፍለው ከእገታ ነጻ የወጡ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ታጋች ሹፌሮች ያሉበት ሁነታ በግልጽ አይታወቅም፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን፣ በተደጋጋሚ እገታ ከሚፈጸምባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ደራ ወረዳ ግንቦት 26/2015 ከ30 በላይ ሰዎች በዚህ ታጣቂ ቡድን መታገታቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡

ታጋቾቹ ሳላይሽ ከምትባል ከተማ ወደ ደራ ጉንዶ መስቀል ከተማ በመካከለኛ የሕዝብ ማጓጓዛ ባስ ተሳፍረው የነበሩ ከ30 በላይ ሰዎች ካታገቱ በኋላ፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው የሚገኝ ሲሆን፣ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጠንካራ ክትትል አላደረገም ያሉ የታጋች ቤተሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን ለማስለቀቅ ከአጋቾች የቀረበላቸው 200 ሺሕ ብር መደራደሪያ ገንዘብ ለመክፈል ጥረት እያደረጉ እንደነበር እገታው በተፈጸመበት ሰሞን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

አቅም ያላቸው የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው በዚያው ሰሞን የተለቀቁ ቢሆንም፣ አቅም የሌላቸው ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በውል አልታወቀም፡፡ በአካባቢው በተደጋጋሚ በታጠቁ ኃይሎች ንጹሃን የሚታገቱ ሲሆን፣ የተጠየቁትን ብር የማይክፍሉ ታጋቾች እንደሚገደሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ያሰባሰብነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ የሚፈጸመው እገታ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና የውጭ አገር ዜጎችን ጭምር ሰላበ ያደረገ ሲሆን፣ ገንዘብ የመከለፈል አቅም አላቸው ተብሎ የሚታሰቡ ሰዎች ትኩረት ተደርጎባቸው እንደሚታገቱም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት በክልሉ ከፍተኛ የመንቀሳቀስ ስጋት የፈጠረ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥትም ይሁን የፌደራሉ መንግሥት ትኩረት አልሰጡትም የሚል ብርቱ ትችት ይቀርባል፡፡

የመንግሥት “ጆሮ ዳባ ልበስ”!

ይህ የእገታ ተግባር በየጊዜው እየተባበሰ መሄዱን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች በተደጋጋሚ መንግሥት ድርጊቱን እንዳስቆምና የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት እንያረጋግጥ በተደጋጋሚ ተጠይቋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በሰላማዊ ሰልፍ የታገዘ ጥያቄም ቀርቦለታል፡፡

ከተለያዩ አካላት ግዴታውን እንዲወጣ በተደጋጋሚ ጥሪ የቀረበለት መንግሥት ግን በአንጻሩ በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ መረጃ የሰጠበት ሁኔታ እንኳን በውል አልታየም፡፡ በታጣቂዎች የተጋቱ ሰዎችም ይሁኑ በተደራጀ የከተማ አካባቢ ዘረፋና እጋታ ሰላባ የሆኑ ዜጎች፣ የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው በሕይወት ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስ ዕድላቸው በቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የመከፈል አቅም የተንጠለጠለ ነው፡፡

በዚህም በአጋቾች የሚጠየቁትን ገንዘብ የመከፈል አቅም የሌላቸውና ከተሰጣቸው ጊዜ የዘገዩ ዜጎችን እጣ ፈንታ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይታቸውን መነጠቅ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አይነቱ ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ ቀን በቀን ለዚያውም በተመሳሳይ ቦታ ላይ ጭምር ለዓመታት እየተፈጸመ መንግሥት አለሁ በሚልበት አገር ላይ ስለመኖራችን ጥርጣሬ ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡

እገታውን የሚፈጽሙ አካላት የሚጠይቁትን ገንዘብ የሚቀበሉት በባንክ በኩል መሆኑን አዲስ ማለዳ በተለያዩ ጊዜ ካነጋገረቻቸው የታገች ቤተሰቦች ተረድታለች፡፡ መንግሥት አለሁ በሚልበት አገር ላይ በአደባባይ እገታ እየፈጸሙ፣ እንደ ሕጋዊ ሰው በባንክ ብር ሲቀበሉና ሲያንቀሳቅሱ መንግሥት ዝም ማለቱ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡

መንግሥት እንደሚለው ቢያንስ ሁሉንም እገታ ወንጀል ማስቆም ባይችል እንኳን፣ ታጋቾች በባንክ የከፈሉተን ገንዘብ ማስመለስና የአጋቾቹን የገንዘብ እንቅስቃሴ የመገደብ ሥልጣን አለው፡፡ ይሁን እንጂ እሰካሁን ይህን መሰል እርምጃዎች በመንግሥት በኩል ስለመወሰዳቸው በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡ እውነትም ይህ አይነቱ ድርጊት “መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ነው ወይ የምንኖረው?” የሚል ጥያቄ ቢያስነሳ የሚገርም አይሆንም፡፡

ይባስ ብሎ መንግሥት የየዕለት ተግባር እየሆነ ስለመጣው እጋታ በመረጃ ደረጃ እንኳን ምን እየሰራ እንደሆነ ለሕዝብ የሚገልጽበት ሁኔታ የለም፡፡ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ በተለያየ ሁኔታ ለመንግሥት ጥያቄ እየቀረበ ቢሆንም፣ መንግሥት ችግሩን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ያለው ይመስላል፡፡

ከሰሞኑ 50 የሚደርሱ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው በታገቱበት ማግስት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጠው የመንግሥት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት፣ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፈረንሳይ ጉዞና ስለ ችግኝ ተከላ ለሕዝብ መረጃ ሲሰጥ ሕዝብን ስላሳሰበው እገታና ሌሎች የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትንፍሽ አላላም፡፡

የሹፌሮቹን መታገት ተከትሎ በጎጃም ደ/ማርቆስ፣ አማኑዔልና ደንበጫ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች የሚፈጸሙ እገታዎችን በመቃወም መንገድ በመዝጋት ተቃውሟቸዉን ለማወሰማት አደባባይ መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ድርጊቱን በመቃወም አደበባይ የወጣው ሕዝብ የሚጠብቀው ድርጊቱን ማስቆም ቢሆንም፣ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ የሞትና የአካል ጉዳት ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም አንድ ሰው ሲገደል ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቋል፡፡

ችግሩ ያሳሰባቸው አካላት ይህ ድርጊት ከዚህ በላይ ተባብሶ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለመግታት መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት በማንሳት፣ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ በተለይ በየጊዜው መልኩን እየቀረና በየአካባቢው እየተስፋፋ መምጣቱ ሊያስከትል የሚችለውን በነጻነት የመንቀሳቀስ ገደብ ከግምት ያስገባና ድርጊቱን ሊገታ የሚችል መፍትሔ እንደሚያስፈልግም እየተጠቆመ ይገኛል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ መረጃዎችን አሰባስባ ይህንን ጥንቅር ስታዘጋጅ በተለይ ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸምበት ከኦሮሚያ ክልልና የፌደራል መንግሥት መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሊሳካለት አልቻልም፡፡ ከኦሮሚያ ክልል በኩል ለጉዳዩ ቅርበት ያለውን የክልሉን አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም፣ ከፌደራል መንግሥት በኩል ከኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል መረጃ ለማግኘትና ከጉዳዩ ላይ የተያየዙ ጥያቄዎችን ለማንሳት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጋችንን ውድ ቤተሰቦቻችን እንድተገነዘቡን እንወዳለን፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here