አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ተመራቂውን ዲግሪ ውድቅ አደረገ

0
562

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ኅዳር 1/ 2012 ባካሔደው መደበኛ ጉባኤው በሳይንስ ዘርፍ የባቡር ምህንድስና ማስተርስ ተመራቂውን ዲግሪ ውድቅ አድርጓል።
ውሳኔውን ያስተላለፈው የአስፈጻሚ ማኔጅመንት ምክር ቤት ሲሆን አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን ውድቅ ለማድረግ የቻልኩት ተርን ኪይ የተባለው ሶፍት ዌር በመጠቀም ባደረኩት ማጣራት የስርቆት ወንጀል ሆኖ በመገኘቱ ነው በሏል።

ተርን ኪይ የተባለው ሶፍት ዌር ምኁራን የሚሰሯቸውን የጥናት ምርምር መመረቂያ ጽሑፎችና ጥናቶች ተመሳሳይ የሆኑትን በማሳየት ጥናቶች የማን እንደነበሩ መለየት የሚያስችል ነው።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አደረኩት ባለው ማጣሪያ 76 በመቶ የሚሆነውን የመመረቂያ ጥናት ሥራዎቹ በኩረጃ ስርቆት የተገኘ፣ 67 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ የጥናት ምንጭ ማጣቀሻው ከአንድ ስፍራ በመጠቀሙ ዲግሪው ውድቅ እንደተደረገ ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል። ዩኒቨርሰቲው ውሳኔውን በሁሉም አቅጣጫው ከመረመርኩኝ በኋላ የወሰንኩት ነው ሲል ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው የወሰነው ውሳኔ ተማሪው የሠራው ጥናት የእኔ ነው የሚል አካል ማመልክቱን ተከትሎ በተደረገ ማጣራት መሆኑን የዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት፤ ትብብር እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደመቀ አንጭሶ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የሚያካሒዳቸውን የምርምርና ጥናት ሥራዎች ጥራት ለመጠበቅም በቅርቡ በሁሉም ኮሌጆቹ ሶፍትዌሩን እንደሚያስተዋውቅ ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ተመካሪዎች ብቻ ሳይሆን አማካሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ደንብ እየተዘጋጀ ነው ያሉት ደመቀ፤ እርምጃ በግለሰብ ደረጃ ቢሆንም በመማር ላይ ላሉ በቀጣይም ለሚመጣው ትውልድ ከስርቆት ነጻ የሆነ ተቋም ለመፍጠር የመጀመሪያው እርምጃ ስለመሆኑ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

ተፈጻሚነቱም ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት በሆነው ሴኔት በሚመራ ቡድን ለግለሰቡ ውጤት ከዩኒቨርሲቲው ለተላከላቸው አካላት መነሳቱን በማሳወቅ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። በአፍሪካ ከሚገኙ 10 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here