በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ እና ያያ ጉለሌ ወረዳዎች ያለው የጸጥታ ችግር ከሌሎች ወረዳዎች የተለየ እና የከፋ በመሆኑ፤ የግብርና ሥራችንን መከወን አልቻልንም ያሉ አርሶ አደሮች ለከፋ ድህነት ተጋልጠናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአካባቢው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ በመባል በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በሚያደርገው ዝርፊያ እና አፈና እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት አለመቻሉን ነው አርሶ አደሮቹ የጠቆሙት፡፡
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በያያ ጉለሌ ወረዳ ዳለቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለአዲስ ማለዳ እንደተናሩት፤ በአካባቢው ታጣቂ ቡድኑ በሚያደርገው ሰፊ እንቅስቃሴ የተነሳ የግብርና ሥራቸውን መከወን አለመቻላቸውን በመጠቆም፣ አብዛኛው የእርሻ መሬታቸው ሳይታረስ የዘር ወቅት ማለፉን ገልጸዋል።
“የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በመኖሩ በወቅቱ አለማግኘታችን ሳያንስ፤ ያለውን ውስን ማዳበሪያ ለመውሰድ እንኳን ባለው የጸጥታ ችግር የተነሳ የሚሰጥበት ቦታ ድረስ ሄደን ማምጣት አለመቻላችን ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎብናል፡፡” ሲሉም አክለዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በወረዳዎች በሚፈጽመው ተደጋጋሚ ዝርፊያ እና አፈና የተማረሩት አቅም ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሻለ ሰላም ወዳለበት ቦታ መሸሻቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች ባሉበት ሆነው የሰቆቃ ሕይወት እየገፉ ነው ተብሏል።
በተለይ በያያ ጉለሌ ወረዳ ሥር ካሉ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከዚሁ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከተዘጉ ወራት በማስቆጠራቸው በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ታጣቂ ቡድኑ በደራ ወረዳ ተደጋጋሚ ዝርፊያ እና እገታ የሚፈጽመ መሆኑን በመጥቀስ፤ የቡድኑ አባላት በቀን ጭምር የፈለጉትን ድርጊት እንደሚፈጽሙ ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡
ለአብነት ታጣቂ ቡድኑ ከወራት በፊት ለቅሶ ሄደው ሲመለሱ የነበሩ ሰዎችን በማገት መውሰዱን ጠቅሰው፤ የተወሰኑ ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ከመለቀቃቸው ውጪ ቀሪዎቹ እስካሁን ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቀ ጠቅሰዋል፡፡
ማህበረሰቡ ካለበት የጎላ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞም እንደለቅሶ፣ ሰርግ እና የመሳሰሉ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማድረግ ካቆመ ቆይቷል ነው የተባለው።
በዞኑ ሥር ባሉ ከሰባት ባላይ ወረዳዎች ከፍተኛ የጸጥታ ችግር መኖሩን አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆቷ ይታወሳል፡፡
የደራ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደመቀ ክፍለው፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለው በሚል ጭምብል መልሶ የኦሮሞን ሕዝብ የሚያሰቃይ እጅግ አሳፋሪ ተግባር እየፈፀመ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፤ “ዓላማው ከተራ ዝርፊያ እና ውንብድና ያለፈ አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “ከዞን የጸጥታ መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን በታጣቂ ቡድኑ ለይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ በመሆኑ አሁን ላይ የተሻለ ሰላም አለ፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።



