ኢትዮጵያዊ የሆነ የጋራ አገራዊ ማንነት እንፍጠር!

0
1505

መታሰቢያነቱ በነገው ዕለት (ኅዳር 7/2012) ከታተመ 50 ዓመት የሚሞላውን እና አነጋጋሪውን ‹‹የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ›› የተሰኘ ርዕስ ያለውን ጽሑፍ በድፍረት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለጻፈልን ዋለልኝ መኮንን ይሁንልኝ ብለው የሚጀምሩት ኢያስፔድ ተስፋዬ፤ የኢትዮጰያ ታሪክ እና የአገር ግንባታ ሒደት ላይ አተኩረው ከቃላት ትርጓሜ ጀምሮ የትኛው መንገድ ይሻለናል ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ቁልፍ ቃላቶች እና የወከሉት ሐሳብ
ብሔር (Nation) የሚለው ቃል ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን ሀሳቦች አጣምሮ የያዘ ነው። በሰዎች ምናብ ውስጥ የተፈጠረ የማህበረሰብ ስሪት/መዋቅር አይነት፣ የሚያመሳስላቸው የጋራ ነገር እንዳለ የሚያምኑ፣ በራሳቸው አስታዳደር ውስጥ ለመተዳደር የሚሹ፣ ራሳቸውን በተመሳሳይ ማንነት የሚገልጽ ማህበረሰብ ስብስብ፣ የጋራ ታሪክ ያለው፣ በኩታ ገጠም መሬት ላይ የሚኖር፣ የራሱ ቋንቋ እና ባህል ያለው ማህበረሰብ ነው።

አገረ መንግሥት (State) የሚለው ቃል በዋናነት የአንድን ሉአላዊ አገር የድንበር ወሰን የሚገልፅ ቃል ነው። ሀብታሙ አለባቸው (2009) አገረ መንግሥት እነዚህን አራት አለባውያንን አጣምሮ የያዘ ነገር ነው ሲል ይገልፀዋል። እነዚህም በዓለም አቀፍ ውሎች እውቅና ያለው የአየርና የመሬት (ውሀ) ግዛት፣ መንግሥታዊ ተቋማት እና አገረ መንግሥቱን የሚመሩ ገዢዎች ስብስብ፣ ቡድን፣ መንግሥት። ሦስተኛ ከማንኛውም የውጭ ኀይል ቁጥጥርና ተጠሪነት ነፃ የሆነ እንዲሁም ከሦስቱ ነጥቦች ጋር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የተሳሰረ ሕዝብ ሲኖር የሚሉ ናቸው።

‹‹ኔሽን ስቴት›› – በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ አንድ ብሔር ብቻ ሲገኝ፣ የዚያ አንድ ብሔር መገለጫዎች፣ ቋንቋ፣ ባህል ወዘተ የአገረ መንግሥቱ መገለጫ ሲሆን ‹‹ኔሽን ስቴት›› ብለን እንጠራዋለን።

‹‹መልቲ ኔሽናል ስቴት›› – በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ ከአንድ በላይ የሆኑ የተለያዩ ብሔሮች፣ ቋንቋ፣ ባህል ወዘተ ሲገኙ እንዲህ ያለውን አገረ መንግሥት መጠሪያ ነው።

የብሔር ግንባታ/አገራዊ ማንነት ግምባታ (nation building) ‹‹የብሔር ግምባታ በፖለቲካ መስፈርት በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ የሚኖር ሕዝብ የጋራ ማንነት የሚፈጥርበትና የሚያዳብርበት የተራዘመ ተግባር ነው።›› (ሀብታሙ አለባቸው 2009) የብሔር ግንባታ ሙከራዎች በኹለት አይነት መንገዶች ሊከናወኑ ይችላሉ። እነዚህም ብዙ ብሔሮች በሚገኙበት አንድ አገረ መንግሥት ውስጥ በአገረ መንግሥቱ የራስን ውክልና አግኝቶ ራስን በራስ በፌደራላዊ መንገድ ለማስተዳደር እና የራስን ማንነት ለማስከበር የሚደረግ ሙከራ ሊሆን ይችላል። ኹለተኛ ደግሞ ከአገረ መንግሥቱ በመገንጠል የራስን ኔሽን ስቴት ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ሊሆን ይችላል።
የብሔር/አገር ግንባታ ከአገረ መንግሥት ምስረታ ቀጥሎ የሚመጣ ነው። አገረ መንግሥት ምስረታ ከተለያዩ የዓለም አገራት ተሞክሮዎች እንደምንረዳው፣ በጉልበት ሊከናወን የሚችል ተግባር ነው። አገር ግንባታ እንደ አገረ መንግሥት ግንባታ በጉልበት የመሳካት እድሉ እጅጉን የጠበበ ነው። ምናልባትም በዓለም ላይ ከአንድ ወይም ከኹለት በላይ አገር ግንባታን በጉልበት ያሳኩ አገራትን መጥቀስ አይቻልም።
ከአገረ መንግሥት ምስረታ እስከ አገር ግንባታ ሙከራ
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዘመናቸው ወደ ደቡቡ እና ደቡብ ምስራቅ ያደረጉትን ‹‹ዘመቻ›› ምን ብለን እንሰይመው የሚለው ሙግት እንዲሁም በዘመቻው ወቅት የተፈፀሙ እኩይ እና መልካም ተግባራት ላይ ያሉትን ክርክሮች ለጊዜው በይደር እናስቀምጥ። (የምኒልክን ዘመቻ ከቅኝ ግዛት አንስቶ እስከ አገርን አንድ ማድረግ የሚል ስያሜ የሚሰጡ ክርክሮች እንዳሉ ልብ ይሏል) አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት አሁን ባለው ቅርፁ በመሰረቱበት ወቅት በአገረ ግዛቱ ውስጥ ያጠቃለሉት እነማንን ነው፣ በምን ሁኔታ ውስጥስ ነበሩ የሚለውን ግን እንመልከት።

አፄ ምኒልክ ደቡቡን ክፍል በማስገበር ያጠቃለሏቸው የራሳቸው ቋንቋ እና ባህል ያላቸው፣ የራሳቸው ታሪክ ያላቸው፣ የራሳቸው መንግሥት/አስተዳደር ያላቸው ህዝቦች ነበሩ። ለአንዳንዶች ይህን ሀቅ መቀበል የሚያመጣባቸው መዘዝ ስላለ ‹‹ኢትዮጵያ ስትሰፋ ስትጠብ ኖረች እንጂ ምኒልክ አዲስ ብሔር ወደ ግዛታቸው አላጠቃለሉም›› የሚል መከራከሪያን ሲያነሱ ይደመጣሉ።

ይህ ሙግት ኹለት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት። አንደኛ የዛሬ 1000 ዓመት የኢትዮጵያ ግዛት እስክ የመን ይደርስ ነበርና ዛሬ እስከ የመን ያሉ ሕዝቦች ወደ ኢትዮጵያ አገረ ግዛት ቢጠቃለሉ አዲስ ብሔር አልተጨመረም ብሎ እንደመከራከር ነው። ኹለተኛ ደግሞ ምኒልክ ባስገበሩበት ወቅት ያስገበሯቸው ሕዝቦች በወቅቱ ስለ ራሳቸው የነበራቸውን መረዳት የሚቃረንና የሚክድ መሆኑ ነው።

በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የበለጠ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፤ አህመዲን ጀበል (2008) እንደሚነግረን፤ አፄ ምኒልክ ሀረርን ለማስገበር ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በወቅቱ የሀረር ገዢ ለነበሩት ኢምር አብዱላሂ ‹‹አገሩን በሰላም አስረክበኝ›› በሚል ደብዳቤ ጽፈው ነበር። ለዚህ ደብዳቤ ኢምር አብዱላሂ የሰጡት ምላሽ በወቅቱ የነበረውን ነገር ቁልጭ አድረጎ የሚያሳይ ይመስለኛል።

ኢምር አብዱላሂ እንደሚከተለው ነበር ያሉት፤ ‹‹እውን አንተ ከቱርክ ትበልጣለህን፣ ሀረርን ከያዝክ ደግሞ ሙስሊም ሆነህ ስትመጣ ብቻ መሆን አለበት››
ከዚህ የኢምሩ መልስ እንደምንረዳው ለኢምሩ የአፄ ምኒልክ ኢምፓየርም ሆነ የቱርክ ኢምፓየር ኹለት የውጭ አካላት ናቸው። በእምነትም በቦታም በታሪክም የተለዩ የውጭ አካላት። ሀረር ቢያንስ የ800 ዓመት ታሪክ፤ የራሷ መገበያያ ፍራንክ እንዲሁም የራሷ ቋንቋ እና ባህል ያላት ነበረች።

በእርግጥ በወቀቱ ሀረር ብቻም ሳትሆን ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ከፋ፣ ጅማ፣ ባሌ፣ ወለጋ… የየራሳቸው አስተዳደር፣ የየራሳቸው ባህል እና ቋንቋ ያላቸው አካባቢዎች ነበሩ። ምኒልክ በማስገበር ወደ ግዛቱ የጠቀለለው የራሳቸው መገለጫ የነበራቸውን ብሔሮችን እንጂ ባዶ ሜዳ፣ ጫካ እና ደን አልነበረም።
የምኒልክን የማስገበር ሒደት ጥቁር እና ነጮች፤ እኩይ እና በጎ ጎኖች ማንሳቱን ለጊዜው እንተወውና በአንድ ጥሬ ሀቅ ላይ ግን መስማማት አለብን። በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነት እና ታሪክ ያላቸው ብሔሮች ተጠቃለዋል። ኢትዮጵያ በምትባለው አገረ መንግሥት ውስጥ ልዩ ልዩ ብሔሮች ይገኛሉ።

አገረ መንግሥት ምስረታ ከተለያዩ አገራት ምስረታ ታሪክም እንደምንረዳው በጉልበት ሊከናወን ይችላል። ከአገረ መንግሥት ምስረታ በኋላ የሚመጣው የአገር ግንባታ ሒደትን ግን በጉልበት ማከናወን አይቻልም። በዓለማችን ላይ አንድ ወይም ኹለት አገራት ይህንን ሒደት በጉልበት ያሳኩ ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ግን በልዩ ሁኔታ የሚታይ እንጂ በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችል አይደለም።

ሀብታሙ አለባቸው (2009)፣ አገር ግንባታን በጉልበት ያሳኩ አገሮችንም ቀረብ ብለን ያየን እንደሆነ በአገረ መንግሥቱ ውስጥ የነበረው የቋንቋ፣ የባህል እና የብሔሮች ልዩነት እጅግ አናሳ የነበረበት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኁልቆ መሳፍርት ልዩነት ያላቸው ሕዝቦች ባሉባቸው አገሮች ውስጥ አገር ግንባታን በጉልበት ለማካሄድ መሞከር አገረ መንግሥቱን ለማፍረስ እንደመሞከር ይቆጠራል። አገር ግንባታ ማለት በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ ተጠቃለው የሚኖሩ ሕዝቦች በአገረ መንግሥቱ ውስጥ የመካተት/የመወከል/የመገለፅ ስሜት እንዲሰማቸው የማስቻል እና አንድ የጋራ ማንነትን የመቅረፅ ሒደት እስከሆነ ድረስ፣ ጉልበት እና አስገዳጅነት የጋራ ማንነትን መገንቢያ አማራጮች ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም።

ከዓለም አገራት ታሪክ እንደምንረዳውም፣ ለአገረ መንግሥት/ግዛት መሰነጣጠቅ እና መከፋፈል ዋናው መንስኤ የተሳካ የብሔር ግንባታ ማከናወን አለመቻል ነው።
አፄ ምኒልክ አገረ መንግሥቱን አሁን በምናውቀው ቅርፅ ከመሰረቱ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሥልጣን ላይ ከቆየው እና የብሔር ግንባታውን ለማካሄድ ጊዜ ካልነበረው ልጅ ኢያሱ በመቀጠል ረጅም ዘመን በሥልጣን ላይ የቆዩት አፄ ኃይለሥላሴ የተከተሏቸው ፖሊሲዎች እና አካሄዶች የጋራ አገራዊ ማንነትን ከመገንባት ይልቅ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮችን ወደ ተከላካይነት የገፋ – ከአገረ መንግሥቱ ተገንጥለው የራሳቸውን ኔሽን ስቴት ለመመስረት እንዲታገሉ መሰረት ያኖረ እና የአገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ነበር።

በአፄዎቹ ዘመን የነበረው የአገር ግንባታ ሒደት 3 መሰረታዊ ችግሮች ነበሩበት።
1 – እኛ እና እነሱ (ራስን በራስ ማስተዳደርን መከልከሉ)
ምኒልክ በይበልጥም በጉልበት ባስገበሯቸው አካባቢዎች የራሳቸውን ሰው በአስተዳዳሪነት እየሾሙ የማለፍ ልማድ ነበራቸው። ከጅማ፣ ከትግራይ እና ከወለጋ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የገበሩ አካባቢዎች የምኒልክን ቋንቋ በሚናገሩ ከሰሜን ኢትዮጵያ በመጡ ሹመኞች ነበር የሚተዳደሩት።
ይህ አይነቱ አካሄድ በገዥውም ሆነ በተገዥው ወገን ‹‹እኛ እና እነሱ›› የሚል ክፍፍል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ለአጭር ጊዜ በሥልጣን ላይ የቆዩት ልጅ ኢያሱ ከዚህ የተለመደ አካሄድ ለማፈንገጥ በጥቂቱ የሞከሩ ቢሆንም ከእሳቸው በኋላ የመጡት አፄ ኃይለስላሴ ግን የቀደመውን የራስን ወገን በሌሎች ላይ የመሾም ድርጊትን አጠናክረው ገፍተውበታል።

በኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ከነበሩት 186 ቁልፍ የውሳኔ ሰጭነት ቦታዎች ውስጥ 143ቱ በሸዋ መኳንንት እና ልሂቃን የተያዙ እንደሆኑ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በአጠቃላይ 5 ቦታዎች ብቻ ነበሩት። የተቀረው በጎንደር ጎጃም እና የትግራይ መኳንንት የተያዙ ነበሩ።
ዋለልኝ መኮንን (1961) የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ በተሰኘው ባለ 5 ገፅ ጽሑፉ ላይ አንድ ወይም ኹለት አማራ/ትግሬ ያልሆኑ፤ አንድ ወይም ኹለት የጦር ጄነራሎች አማራ/ትግሬ ያልሆኑ፤ አንድ ወይም ኹለት ገዢዎች እና ባላባቶች አማራ/ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች በስርአቱ ውስጥ ሥልጣን ላይ መሆናቸውን በማንሳት የብሔሮች ጭቆና የለም ለማለት የሚሞክሩ እንዳሉ ጠቅሶ፣ ብሪታኒያም ቅኝ የገዛቻቸውን አገሮች በጎሳ መሪዎች የእጅ አዙር ድጋፍ እንደምትገዛ ገልፆ መከራከሪያውን ፉርሽ ያደርገዋል።

በእርግጥ በስርአቱ ውስጥ የነበሩት አንድ ወይም ኹለት አማራ/ትግሬ ያልሆኑ ሹመኞችም በእጅ አዙር የሚቆጣጠራቸው አማራ/ትግሬ ምክትል ይመደብላቸው ነበር።
ለዚህ አይነተኛ ማሳያ የሚሆኑት ገረሱ ዱኪ ናቸው። ገረሱ ዱኪ እንዲቆጣጠራቸው የተላከው ምክትላቸው አላሠራ እያለ ስላስቸገራቸው አስረው በጅራፍ ያስገርፉታል። ይህን ማድረጋቸውን የሰሙት ንጉሡም ከሥልጣናቸው ተነስተው አዲስ አበባ ቁጭ እንዲሉ አድርገዋቸዋል። ስለጉዳዩ እንዲያስረዱ ቤተመንግሥት በተጠሩበት ወቅትም ‹‹እኔ እንዳስተዳድረው እንጂ እሱ እንዲያስተዳድረኝ መላኩን አላወኩም ነበር›› ሲሉ መልሰዋል (ኦላና ዞጋ፡ 1985)
ይህ የራስን ወገን በአስተዳዳሪነት በሕዝቦች ላይ መጫን ሲውል ሲያድር ያመጣው መዘዝ ቀላል አይደለም። በጉልበት ከገበሩት አካባቢዎች መካከል ሀረር አካባቢን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ገዥዎች ላይ ጣልያን በገባ ጊዜ የአካቢው ሰው ሆ ብሎ ተነስቶባቸው ጭፍጨፋ አካሂዶባቸዋል።

ጣልያን ወደ አካባቢው መጠጋቱ በተሰማ ወቅት የአካባቢው ሰው ደስተኛ ነበር። ደስተኛ የነበረውም ከሀዲ ወይም ባንዳ ስለነበር ሳይሆን ለከት ባልነበረው ብዝበዛ በጭካኔ ከሚገዛቸው በላይ ጣልያን ምንም አያደርገንም ብለው በማሰባቸው ነው። አንዳርጋቸው ፅጌ (2010) በዚህ ጭፍጨፋም አንዳርጋቸው ፅጌ የአባቱ ወንድሞች መገደላቸውን በመጽሐፉ ላይ ይነግረናል።

ዛሬ ላይ የምናያቸውን ብሔርን/ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አንዳንዶች የ27 ዓመቱ የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ውጤት አድርገው ያዩታል። ይህ ግን ከታሪክ እና ከእውነት ጋር መጋጨት ነው። በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ማዕከላዊ መንግሥት የተዳከመ በመሰለበት ጊዜ ሁሉ ከብሔር ማንነት ጋር የሚያያዙ ጥቃቶች አጋጥመዋል። ጣልያን ዳግም በመጣበት እና የንጉሡ አቅም በተዳከመበት በ1930ዎቹ እና ንጉሡ በወታደራዊ ደርግ ከዙፋናቸው በተነሱበት ወቅት እንዲሁም ደርግ ተወግዶ ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ መሰል ጥቃቶች ነበሩ። የጥቃቶቹ መንስኤም የአፄዎቹ የራስን ወገን በሌሎች ላይ በጉልበት ገዢ አድርጎ መጫን ያመጣው የእኛ እና የእነሱ ልዩነት ነው።

2- አቅላጫዊነት የቋንቋ እና የባህል ፖሊሲ (assimilation policy)
ዋለልኝ መኮንን (1961) የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ በተሰኘው ጽሑፉ ላይ ‹‹አንድ ሰው ‹‹እውነተኛ ኢትዮጵያዊ›› የሚባለው አማርኛ ቋንቋ ሲናገር፣ አማርኛ ሙዚቃ ሲያደምጥ… በአጭሩ ኢትዮጵያዊ የሚባለው የአማራነትን ማስክ ሲያጠልቅ ነው›› ሲል ሌሎች ማንነቶችን በማጥፋት የአንድ አካባቢ ማንነትን ኢትዮጵያዊ ማንነት ለማድረግ የሚደረገውን ሙከራ ይኮንናል። በተማሪዎች ትግል ወቅት ‹‹ማነው ኢትዮጵያዊ›› የሚለው የኢብሳ ነገዎ ግጥም ዝነኛ የነበረውም የዚሁ የአንድን ማንነት የመጫን ሙከራ የፈጠረው የተቃርኖ ኀይል ስለነበር ነው።
ይህንን የእነ ዋለልኝን ክስ የሚያጠናክርልን አንድ ታሪካዊ ማስረጃ እንመልከት።

አፄ ኃይለሥላሴ በ1959 ከኢትዮጵያ ሱማሌ የጎሳ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት በወቅቱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ታትሞ ነበር።ሀብታሙ አለባቸው (2009) ጋዜጣውን ዋቢ አድርጎ ያሰፈረውን እና አፄ ኃይለሥላሴ ከሱማሌ የጎሳ መሪዎች ለቀረበላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ (1959) እንደወረደ ላቅርበው፤ ‹‹ሆስፒታል፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት እንድንገነባላችሁ ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ አማርኛ ልመዱ። አማርኛ ሳይችሉ እንዴት ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ይቻላል?››

እንግዲህ ከዚህ የንጉሡ ንግግር እንደምንረዳው፣ በእሳቸው ስርዓት ውስጥ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመባል አማርኛ ቋንቋን መቻል አለበት። ኢትዮጵያዊ ለመባል ብቻም ሳይሆን የመሠረተ ልማት ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት አማርኛ መቻል ግዴታው ነበር። ይህ የሕዝቦችን ማንነት አክስሞ የራስን ማንነት የመጫን assimilation policy ኹለት ፊት ነበረው።

አንደኛው የሰሜን ኢትዮጵያን ማንነት በሕግ አገራዊ ማንነት አድርጎ በመደንገግ በሌሎች ሕዝቦች ላይ በጉልበት መጫን ሲሆን (ለምሳሌ- አማርኛ ቋንቋ በሕገ መንግሥቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን መወሰኑ፣ በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች አማርኛ ብቻ ይፋዊ የትምህርት ቋንቋ እንዲሆን መደንገጉ፣ የኦርቶዶክስ እምነት የመንግሥት ሀይማኖት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉ ወዘተ) ኹለተኛው ደግሞ ሌሎች ማንነቶች የሚያድጉበትን እድል በተለያዩ መንገዶች መንፈግ ነው። (ለምሳሌ – በኦሮምኛ ቋንቋ የሬዲዮ ስርጭት እንዳይኖር መከልከል፣ ከክርስትና ሃይማኖታዊ በዓላት ውጭ ሌሎች ባዕሎች ባሉበት ቀን ከሥራ ገበታ ወይም ከትምህርት የሚቀር ሰው ላይ የገንዘብ መቀጮ መጣል- ወዘተ)

ይህ የአፄ ኃይለሥላሴ የራስን ማንነት በጉልበት የማጥመቅ ፖሊሲ ውሎ ሲያድር ሪአክሽነሪ ኃይል በመፍጠሩ የአገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል። በጥቂት አገራት (ለምሳሌ በፈረንሳይ) ሲሳካ እንደታየው ፖሊሲው በኢትዮጵያ ለምን አልተሳካም? ቢያንስ ኹለት ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፤
ሀ. እንዲከስም የተፈለገው አካል በአይነትም በብዛትም ከአክሳሚው አካል ስለሚበልጥ ነው። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምስረታን ለየት የሚያደርገውም በምሥረታው ወቅት ወደ ግዛቱ የተጠቃለለው አካባቢ በቆዳ ስፋትም በሕዝብ ቁጥርም ንጉሡ ከተነሱበት የሰሜን ኢትዮጵያ መብለጡ ነው። በሌሎች አገሮች የማክሰም እና ያለመክሰም ትንቅንቆች የሚደረጉት በብዙኀኑ እና በአናሳው መካከል ነበር። በኢትዮጵያ ግን የተሞከረው የተገላቢጦሹ ነው።

ለ. የሌሎችን ማንነት በማክሰም የራስን ማንነት ለመጫን የሞከረው አካል አላማውን ለማስፈፀም የሚያስችል በቂ የኢኮኖሚ እና የኀይል አቅም አልነበረውም።

3. ኢኮኖሚያዊ ጭቆና
ክፍሉ ታደሰ (ያ ትውልድ ቅፅ1) እንደሚነግረን፣ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው የእርሻ መሬት ላይ 2/3ኛ የሚሆነው መሬት የተያዘው ከሰሜን ኢትዮጵያ በመጡ ባላባቶች ነበር። እነዚህ ከሰሜኑ ክፍል የመጡ ባላባቶችም የአካባቢውን ሰው ጭሰኛ አድርገው ጉልበቱንም መሬቱንም ምርቱንም ሲበዘብዙት ኖረዋል።
አንድን አካባቢ እና ሕዝብ በጉልበትም ይሁን በማናቸውም መንገድ ወደ አገረ መንግሥቱ ካጠቃለልከው በኋላ መሬቱን እና የመሬቱን ውጤት ከቀማኸው እንዴት ዓይነት አገራዊ ማንነት ግንባታ ነው ልታካሂድ የምትችለው?

በ1960ዎቹ የተማሪዎች ትግል ወቅት አከራካሪ ከነበሩት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የመደብ/ኢኮኖሚ ጭቆናውን መልስ ብንሰጠው የብሔር ጥያቄ መልስ ያገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመደብ ልዩነት ማቴሪያላይዝ የሚደረግ እና አንድ ኹለት ብሎ ለመቁጠር አዳጋች ነው። ጨቋኙም ተጨቋኙም መሬትን እና የመሬትን ውጤት የሚጠብቁ እንጂ እንደ አውሮፓውያኑ ሰፊ የመደብ ልዩነት አልነበረም። የነበረውንም ልዩነት የፈጠረው የተወሰነን ቡድን ማንነቱን መሰረት አድርጎ በመሬት ላይ ባለቤት እንዲሆን እድል የሰጠ ስርአት ነው የልዩነቱ መነሾ።

ከላይ የተዘረዘሩት 3 ነጥቦች የኢትዮጵያን የአገር ግንባታ ሒደት የጋራ አገራዊ ማንነትን ከመፍጠር ይልቅ ወደ ኋላ በመጎተት አገረ መንግሥቱ ላይ የመፍረስ አደጋ ጋረጡበት። የዘውዳዊው ስርአት ከአማራ ማንነት ጋር መቆራኘቱ አማራ ባልሆኑ ሕዝቦች ጭንቅላት ወስጥ የነበረ ስዕል ብቻ አልነበረም። ‹‹ጊዮናዊነት የአማራ መነሻ እና መዳረሻ›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ምስጋናው አንዱአለም (2010) ብርሀኑ አስረስን ዋቢ አድርጎ፤
‹‹የዘመናት የአማራ ምሰሶ የሆነው የዘውድ ስርአት እያዘመመ፣ ካዘመመበትም ምስጥ እየበላው ለመጠገን አልቻል ብሎ እየፈራረሰ ነበር…የዘውዳዊው ስርአት ወደ ማብቂያው መዳረሱን በማየት ብዙዎች ለየት ያለ የስጋት አየር ይሸታቸው ጀመር። ነገሩ ከመንግሥት ውድቀት ባሻገር የአማራ ውድቀት መሆኑን የተረዱ መሳፍንት በበኩላቸው የተለየ ጭንቀት ውስጥ ገብተው ነበር።…››

በ1965 ቀጨኔ በሚገኘው የደጃዝማች እንቁሥላሴ ቤት ተሰብስበውም እንዲህ መክረው ነበር፤ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ቢመጣ ተነሳሁ የሚለው አማራው ሕዝብ ላይ እንጂ ለይቶ የሸዋ፣ የጎንደር፣ የጎጃም አይልም። እኛም ወደድንም ጠላንም የአማራው አንገት አንድ መሆኑን ማወቅ አለብን። ስለዚህ አማራው መተባበር አለበት።›› ምስጋናው አንዱአለም (2010)

ይህ ታሪካዊ መረጃ የአፄው ስርአት እና ሲገነባ የኖረው ማንነት የአንድ ወገን ብቻ እንደነበር በኹለቱም በኩል የሚታወቅ ያፈጠጠ እና ያገጠጠ የዘመኑ ሀቅ እንደነበር ያሳየናል።

በተማሪዎች አመፅ እየተንገዳገደ የነበረውን ስርአት ተክቶ ዙፋን ላይ የወጣው ደርግም የመደብ ጥያቄን ለመመለስ ያስችለኛል ያለውን የመሬት ለአራሹ አዋጅ ቢያውጅም የብሔሮችን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ አገረ መንግሥቱ በየቦታው በሚደረጉ ትግሎች መናጡን ያዘ።

ወታደራዊ ደርግ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለውን አዋጅ ሲያውጅ በወቅቱ በወጣቱ ዘንድ ሰፊ መሰረት የነበረው ኢህአፓ በልሳኑ ዴሞክራሲያ ላይ የሰጠው ምላሽ በወቅቱ የነበረውን የመስመር ልዩነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ኢህአፓ ለደርግ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሰጠው መልስ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይቅደሙ›› የሚል ነበር።

ደርግ ሥልጣኑን እና ግዛታዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ሲታገል፣ የግዛታዊ አንድነት ምሰሶ የሆነውን የጋራ አገራዊ ማንነት ግንባታን ዘነጋው። ደርግ በመጨረሻዎቹ የሥልጣኑ ዓመታት ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩትን›› በማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ካረፈደ ሆነና 1983 መጣ።
የጋራ አገራዊ ማንነት ግንባታ ድኅረ 1983
ንጉሡ ተመልሰው መጡ?!

‹‹ለብሔሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን ትግል እውቅና በመስጠት እና በብሔሮች መካከል የነበረውን የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት በማረም የግለሰብ እና የቡድን መብቶች የሚከበሩበትን አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ይህን ውል ገብተናል›› (የሕገመንግሥቱ መግቢያ 1985) በሚል መርህ የሥልጣን ዘመኑን የጀመረው ኢህአዴግ በአገር ግንባታ ሂደቱ ላይ ሦስት መሰረታዊ ጥፋቶች ፈፅሟል።

1- የቋንቋ ፖሊሲው
የጋራ አገራዊ ማንነትን ለመቅረፅ የቋንቋ ፖሊሲ እጅግ ቁልፍ ነው። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት በኢትዮጵያ የነበረውን የቋንቋ እና የተናጋሪዎቹን አሃዝ ስንመለከት፤ ‹‹14 ሚሊዮን ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ 12 ሚሊዮን አማርኛ ተናጋሪ፣…. ነበር›› (የ1985ቱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ) አማርኛ ቋንቋ ባለፉት ስርአቶች በሕግ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ከመዝለቁ አንፃር፣ በሥነ ጽሑፍ ዘርፉ የዳበረ ቦታ እንደነበረው እሙን ነው። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ከአማርኛ ጋር ኦሮምኛን የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ያላደረገው ለምን ይሆን?

በ1990 የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የትምህርት ቢሮ በክልሉ ለሚገኙ ተማሪዎች ከአማርኛ በተጨማሪ አንድ ተጨማሪ አገር በቀል ቋንቋ እንዲማሩ የሚያስችል ጥናት አስጠናቶ ነበር። በዚህ ጥናት መሰረት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ በአማራ ክልል እንደ ኹለተኛ ቋንቋ ሆኖ ትምህርት እንዲሰጥበት ተቀባይነት ያገኘው ኦሮምኛ ነበር። በዚህም መሰረት ወደ ተግባር ሊገባ ሲል ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በተላለፈ ቀጭን ትዕዛዝ እንደቀረ ‹‹ጠርዝ ላይ ያለች አገር›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ (2011) ይነግረናል።

ህወሓት መሩ ኢሕአዴግ ብሔሮች የራሳቸውን ቋንቋ በክልላቸው እንዲያበለፅጉ ፍቃድ ሲሰጥ የብሔሮች ቋንቋ የኢትዮጵያ ቋንቋ ሆኖ እንዳይወጣ ግን ግልፅ እና ስውር ደባዎችን ሲፈፅም ቆይቷል። ይህም የጋራ አገራዊ ማንነት ግንባታ ሂደቱን ያደናቀፈ ተግባር ነበር።

2- ራስን በራስ ማስተዳደርን አለመፍቀዱ
የሕገ መንግሥቱ አእማድ እና ሕገ መንግሥቱን የወለደው ትግል ምሰሶ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ቢሆንም ኢሕአዴግ ለይስሙላ ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው ይበል እንጂ በእጅ አዙር ራሱ በሾማቸው ጭቃሹሞች በኩል ብሔሮችን ሲገዛ ኖሯል።

አፄ ኃይለሥላሴ ጥቂት አማርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ሰዎችን በየአካባቢው ከሾሙ በኋላ የሚቆጣጠራቸው አማራ/ትግሬ ምክትል ይመድቡባቸው እንደነበረው ሁሉ፣ ህወሓት ኢሕአዴግም ብሔሮችን በሞግዚትነት የሚያስተዳድሩ የራሱን ሰዎች በየቦታው ሹሞ በይስሙላ ፌደራሊዝም እጅግ በጣም የተማከለ አሃዳዊ አመራር ይሰጥ ነበር።

ይህም ሌላ የጋራ አገራዊ ማንነት ግንባታ ሂደቱን ያደናቀፈ የኢህአዴግ ተግባር ነው።

3- የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ብያኔ ሳይከልስ ማስቀጠሉ
ብዙዎች የብሔሮች ጥያቄ በ1983 ተመልሷል- የቀረው ጥቂት ነገር ብቻ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ግን አንድም ፈፅሞ ከእውነታው የራቀ ነው። እንዲሁም የብሔሮችን ጥያቄ ምንነት በትክክል ካለመገንዘብ የሚሰጥ አስተያየት ነው። በራስ ቋንቋ የመናገር፣ የመማር የማስተማር፣ የራስን ባህል የመጠበቅ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች አዎን የብሐየር ጥያቄዎች ናቸው። ጥያቄዎቹ እነዚህ ብቻ ቢሆኑ ኖሮ በመገንጠል እና የራስን ኔሽን ስቴት በመመስረት በቀላሉ ምላሽ ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ጥያቄዎቹ በ1983 መልስ አግኝተዋል ቢባል እንኳን (መልስ አላገኙም) ብሔሮች በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ስር እስካሉ ድረስ ጥያቄዎቻቸው እነዚህ ብቻ አይደሉም።

ብሔሮች በኢትዮጵያ አገረመንግሥት ስር እስካሉ ድረስ ዋናው ጥያቄያቸው ኢትዮጵያን በፍሬ ነገር ዳግም መበየንና ሁሉንም የሚመስል እና የሚወክል አገራዊ ማንነት መሥራት ነው።

ዋለልኝ መኮንን fake nationalism (የቁጩ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት) ሲል የሚጠራው የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት ብያኔ እስካልተቀየረ ድረስ የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ውስጥ መልስ አግኝቷል ሊባል አይችልም። ህወሓት/ኢሕአዴግ በአፍ የዋለልኝ ዘካሪ ሆኖ ቢቆይም በግብር ግን የአፄዎቹን የኢትዮጵያዊነት ብያኔ አስቀጥሏል። በዚህም ምክንያት ከደርጉ 17 ዓመታት በተጨማሪ ሌላ 27 ዓመታት የጋራ አገራዊ ማንነት ሳንገነባ አልፎብናል።
ምን ይሻለናል? ምን እናድርግ?

1- የዜግነት ፖለቲካ እንደ አማራጭ?
ዜጋ በሌለበት የዜግነት ፖለቲካ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ?! በቅርቡ የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናትናኤል ፈለቀ በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ላይ ቀርበው ስለ ዜግነት ፖለቲካ ምንነት ሲስረዱ፤ ‹‹በዜግነት ፖለቲካ እና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መካከል የልዩነት ቦታ አለው። ሰዎች ማንነታቸውን በዘውጌም ሊገልፁ ይችላሉ…ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ነው ሊሉም ይችላሉ። የዜግነት ፖለቲካ ከማንነት ጋር የተያያዘ አይደለም። ሁላችንም የዚች አገር ዜጎች በመሆናችን በዜግነት የምናራምደው ፖለቲካ ነው›› ብለዋል
የዜግነት ፖለቲካው በዙሪያው የሰበሰባቸው ደጋፊዎች እና ተከታዮች ይህንን በዜግነት ፖለቲካ እና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መካከል ያለውን የልዩነት መስመር ቢያውቁ ጓዛቸውን ጠቅልለው ይህንን ካምፕ መሰናበታቸው አይቀርም። ለብዙ ደጋፊዎቹ የዜግነት ፖለቲካ ሲባል የሚመስላቸው በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጥላ ስር ተሰብስቦ የሚደረግ ትግል ነው። የደጋፊዎቹን ነገር ለጊዜው በይደር ይዘን የዜግነት ፖለቲካን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁናቴ አማራጭ መፍትሄ አድርገን እንዳንወስደው የሚያደርጉንን ኹለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ።

አንደኛው ‹ዜግነት› በኢትዮጵያ አለ ወይ? ነው። በኢትዮጵያ አገረመንግሥት ታሪክ ውስጥ የዜግነትን ፅንሰ ሀሳብ እና ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ ደረጃ ያስተዋወቀው ደርግ ነው። ከደርግ በፊት በነበሩት ኹለቱ የኃይለስላሴ ሕገመንግሥቶች ላይ ዜጎች የሚል ቃልም ሐሳብም የለም። ከዚህ ይልቅ ‹‹ሕዝብ›› እና ‹‹ነዋሪዎች›› የሚል ቃል ነበር በሕገመንግሥቶቹ ላይ የምናገኘው። (ቃልአብ ታደሰ ስጋቱ 2011) ነዋሪዎቹ/ሕዝቡም እንደ ንጉሠ ነገሥቱ ተገዥዎች ተደርገው ነበር የሚቆጠሩት። ይህ በማንኛውም አምባገነን ኢምፓየር ውስጥ የተለመደ አካሄድ ስለነበር የሚያስደንቅ አይደለም።

ዜግነት ምንድነው? ሀብታሙ አለባቸው (2009) ብሩተር ኤምን ዋቢ አድርጎ እነዚህ 4 ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ዜግነት ትርጉምም ሆነ ህልውና የለውም ሲል ይሞግታል። እነዚህም ካፒታሊዝም ወይም ካፒታሊስታዊ የፖለቲካ ስርአት፣ በምርጫ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ፣ የሕዝብ ሉአላዊነት እና በኢኮኖሚ ራሱን የቻለ ወይም የመቻል እድል ያለው ግለሰብ የሚሉ ናቸው።

በዚህ የዘመናዊ ዜግነት ፅንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁናቴ ስንተነትን፣ የዜግነት ፖለቲካ ቀርቶ ዜግነት ራሱ ፅንሰ ሐሳባዊ ትርጓሜው ተሟልቶ በኢትዮጵያ መገኘቱ አጠያያቂ ነው። ዜግነት በሌለበት የዜግነት ፖለቲካ ደግሞ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው የሚሆነው።

ኹለተኛው ከማንነት ውጭ በጋራ ሊያቆመን የሚችል መሰባሰቢያ ምህዋር የለም። ቅድመ ካፒታሊስታዊ በሆነች እና ዘመናዊ የዜግነት ፅንሰ ሐሳብ ባላዳበረባት ኢትዮጵያ ሕዝብን በጋራ ለማስተባበር እና ለማቆም የተሻለው አማራጭ ማንነት ነው።

የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች (ከላይ ከቀረበው በቀር) ውጭ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት/ማንነት እና በዜግነት ፖለቲካ መካከል የልዩነት መስመር ሲያሰምሩ የማናየው እና ልዩነቱን ሲያድበሰብሱ የምናየው ከማንነት ውጭ (ንዑስም ሆነ አገራዊ) ሕዝብን ማሰባሰብ ከባድ ስለሆነ ነው።
አሜሪካንም ሆነ ሌሎች አገራት ከማንነት ውጭ በጋራ ያቆማቸው ሌላው ዋናው ነገር ሕገመንግሥታዊ አርበኝነት (constitutional patriotism) የሚባል ፅንሰ ሐሳብ ነው። አንዳንድ ምኁራን ይህንን አማራጭ ደግፈው ብዙ ጽፈዋል። ይህ አማራጭ ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁናቴ ለአገራችን እንደ አማራጭ የሚቀርብ አይደለም። ምክንያቱም እንኳን በአርበኝነት መንፈስ የምንገዛለት ሕገመንግሥት ሊኖረን ቀርቶ በቅጡ የምንስማማበት ሕገመንግሥት እንኳ የለንም። በሕገመንግሥቱ አልተወከልኩም ከሚለው አንስቶ ሕገመንግሥቱ ዜግነቴን ክዶታል እስከሚለው ድረስ ከፍተኛ ተቃርኖ ያስተናገደ ሕገመንግሥት ነው ያለን።

ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ የዜግነት ፖለቲካው (ህልውና ካለው) ከማንነት ተፋትቶ ሕዝቦችን በጋራ የሚያሰባስብበት መሠረተ ሐሳብ የለውም። ራሱን ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር አጣምሮ ካቀረበ ደግሞ የትኛው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት? መቼ እና እንዴት የተፈጠረው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት? የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት መገለጫዎች ምንድን ናቸው? አለ የምትለው ብሔርተኝነት ውስጥ እኔን እስቲ አሳየኝ? ከሚሉ መልስ ከሌላቸው ጥያቄዎች ጋር ይጋፈጣል።

2- ብሔርን ከፖለቲካው ማግለል እንደ አማራጭ
ይህ አማራጭ መጀመሪያ ላይ ካየነው የዜግነት ፖለቲካ አማራጭ በጥቂቱ ለየት ይላል። ብዙውን ጊዜም የሚቀነቀነው በይፋ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነን ብለው በገለጹ ሰዎች ነው። አለ ብለው የሚያስቡትን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ማስቀጠልም ትልቁ መሻታቸው ነው።

ብሔር እና ፖለቲካው ሲጣመር በአገር እና በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳመጣ የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችን ዋቢ በማድረግ ይከራከራሉ። (ሰማኸኝ ጋሹ 2014) የዚህ አመለካከት አራማጆች ብሔርን መሰረት አድርጓል ብለው የሚያስቡትን የፌደራሊዝም ስርአትንም አጥብቀው የሚኮንኑ እና በአብዛኛው የመልከዐ ምድራዊ ፌደራሊዝምን የሚደግፉ ናቸው።

ይህ አማራጭ ኹለት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት። ቀዳሚው ብዙ ብሔሮች ባሉባት አገር ከብሔርተኝነት ነፃ የሆነ መንግሥት ሊኖር አይችልም። ኢትዮጵያ ተወደደም ተጠላም የበርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ የበርካታ ባህሎች እና የራሳቸው ታሪክ ያላቸው ብሐየሮች የተጠቃለሉባት አገረ መንግሥት ናት። በርካታ ብሔሮች ባሉበት አገረ መንግሥት ውስጥ ደግሞ መንግሥት ብሔር አልቦ ሊሆን አይችልም።

አንድ የጋራ አገራዊ ማንነት የመገንቢያ መንገዶች የሚባሉት ዋና ዋና መሣሪያዎች (የትምህርት ፖሊሲ፣ የቋንቋ ፖሊሲ፣ መሰረተ ልማት) በመንግሥት እጅ ነው የሚገኙት። መንግሥት ከሁሉም ብሔሮች የተውጣጣ አገራዊ ማንነት የሚገነባበትን መንገድ ይዘረጋል ወይም ደግሞ አንዱን ማንነት አጉልቶ የሚያወጣ ፖሊሲ ይከተላል። በዚህም ምክንያት ብሔር አልቦ መንግሥት ሊኖር አይችልም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አንድ መቶ ዓመታት ውስጥ እንዳየነው መንግሥት የአንድ አካባቢ ማንነትን (የአቢሲኒያ ማንነት) በፖሊሲ ድጋፍ ከሌሎች ማንነቶች ገንኖ እንዲወጣ ለማድረግ ሞክሯል። ብሔርን ከፖለቲካ እንነጥለው የሚለውን ሀሳብ የሚያራምዱ ወገኖች ዋነኛው ችግር ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ማንነት / የጋራ አገራዊ ማንነት ባልተገነባባት እና ዳግም ባልተበየነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን ከፖለቲካው መነጠል ማለት በሌላ አማርኛ አሁን ያለው የኢትዮጵያዊነት ብያኔ ይቀጥል እንደማለት መሆኑ ነው።

ኹለተኛው ችግር ክልልን እና ብሔርን የመነጠል አካሄድ አላማ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብሔሮች ኩታ ገጠም በሆነ መሬት ላይ ተጠጋግተው ሰፍረው ሲገኙ እና በክልሉ ብዙኀን ሆነው እንዳይወጡ ሲፈለግ ፖለቲከኞች የሚከተሉት አካሔድ አለ። ይህም ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ሰዎች ተጠጋግተው ሰፍረው የሚገኙትን ቦታ በመከፋፈል እና ከሌሎች ጋር በመከለል በአገረ መንግሥቱ ግዛት ውስጥ ያሉ ክልሎች ውስጥ ብዙኀን የሚባል ማንነት እንዳይኖር የማድረግ ስትራቴጂ ነው። ማንነት እና ክልል ይነጠል የሚሉ የአገራችን ፖለቲከኞችም በዚሁ መነፅር የሚታዩ ናቸው። ይህ አይነቱ ፍላጎትን በሌሎች ላይ በግድ የመጫን አካሄድ የበለጠ አገሪቷን ወዳለመረጋጋት የሚወስድ ነው።

3- ኢትዮጵያን ዳግም በመበየን የጋራ አገራዊ ማንነትን መገንባት ብቸኛው አማራጭ
ኢትዮጵያን ዳግም መበየን ስንል ምን ማለታችን ነው? አሁን ያለው የኢትዮጵያዊነት ብያኔ ምን ይመስላል? ሰፊ ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። በአጭሩ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በፍሬ ነገር ሰሜኑን ኢትዮጵያ ብቻ የምትወክል ናት።

እንደ መውጫ አንባቢዬን አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ከስር ያለውን ጽሑፍ ከማንበብዎ በፊት ይህን ጥያቄ ይመልሱ፤ በ 17ኛው መቶ ክፈለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ ማን ነበር? መልስዎ አፄ ልብነ ድንግል የሚል ከሆነ በእርስዎ አእምሮ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ብያኔ ምን እንደሚመስል ላሳይ።

ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ አህመድ) አሁን ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት አገረመንግሥት ግዛት ውስጥ ከኢትዮጵያውያን የተወለደ ሰው ነበር። ግራኝ አሕመድ አፄ ቴዎድሮስ በዘመናቸው አንድ አድርገው ከገዙት ቦታ በላይ የሚሆንን ግዛት (እስከ ጅቡቲ ድረስ) አንድ አድርጎ ገዝቷል። በአንፃሩ ግን አፄ ልብነ ድንግል በሰሜኑ ኢትዮጵያ ያውም ከሰሜኑ ኢትዮጵያም እጅግ በጣም የተወሰነ ቦታ ይዘው የገዙ ንጉሥ ናቸው።

ነገር ግን ሰፊውን የኢትዮጵያን ክፍል ይገዛ የነበረውን ግራኝ አህመድን እንደወራሪ የአንድ መንደርን መስፍን እንደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ለምን ተቆጠረ? የኢትዮጵያ ብያኔ ደቡቡን የኢትዮጵያ ክፍል ያላካተተ የሰሜኑ ኢትዮጵያ የማንነት መገለጫ በመሆኑ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አረቡን ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት መግለፅ የተለመደ ነው። አረቦች ግራኝ አህመድን እና የሀረር ኢምሮችን ማስታጠቃቸው እንደ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ካስቆጠራቸው ፖርቹጋሎች ጎንደር እና ነገሥታቱን መደገፋቸው ለምን እንደ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት አላስቆጠራቸውም?

ምክንያቱም አሁን ያለው የኢትዮጵያዊነት ብያኔ እስልምናን ያገለለ እና ክርስትናን እና ኢትዮጵያዊነት ቀላቅሎ የሰፋ በመሆኑ ነው። እንዲህ ያሉ አንድ ሺህ አንድ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። በአጭሩ አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት እና የኢትዮጵያዊነት ብያኔ ሁሉንም ወገን የሚገልፅ እና የሚወክል ባለመሆኑ በድጋሚ መከለስ ይኖርበታል። ከብያኔው መከለስ በኋላም አንድ የጋራ አገራዊ ማንነት ለመገንባት የልሂቃኖች ድርድር አንዲሁም የመንግሥት የቋንቋ፣ የትምህርት እና የመሠረተ ልማት ፖሊሲዎች ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
አንድ የጋራ አገራዊ ማንነት መገንባት ካልቻልን ግን ከአዙሪቱ ውስጥ መውጣት ፈፅሞ አይቻለንም።

 

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here