ሠላም የራቃቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት

0
799

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሰሞኑ ስማቸውና ግብራቸው ለየቅል ሆኖ ሰንብቷል። በጥቅምት 29/2012 በወልድያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት የኹለት ተማሪዎች ሕይወት ጠፍቷል። ይህን ተከትሎ ግጭቱ እና በተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከዚህም ከዛም በኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይሰማል። ተማሪዎች ይጎዳሉ፤ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲም የአንድ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል።

እንደ ሰደድ እሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ዩኒቨርስቲዎችን ያዳረሰው ግጭት እና አለመረጋጋት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከግብራቸው ውጪ ሆነው ለትምህርት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሰበሰቧቸውን ተማሪዎች በአግባቡ ለማስተማር ሲንገዳግዳቸው ታይተዋል። በተለይ ደግሞ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች የጸሐፊዎች ማንነት ባልተገለጸበት መንገድ ነገር ግን አንድን ብሔር በመጥቀስ የዛ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ጊቢውን ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ መጣሉን የሚያስነብቡ ጽሑፎችም ሲነበቡ ሰንብተዋል።

በዚህ የሰሞኑ ግጭት በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ የሐሰትና ግጭት አባባሽ የሆኑ ምስሎችን ሲያንሸራሽሩ ተስተውለው ብዙኃኑን ወደ አልሆነ መንገድ ሲመሩት ነበር።

ከዘመኑ ጋር እየዘመኑ ከመጡ የመረጃ ምንጮችም በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም እውነትነታቸው የተረጋገጠ መረጃዎችን ለሕዝብ ሲያደርሱ የሰንበቱም አሉ። በምሥራቅ ሃረርጌ የቤተ እምነት መቃጠልን፣ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ከታማኝ የዜና አውታሮች ተስተጋብቷል።

ይሁን እንጂ ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት በኹለት ጎራ ተከፍለው በርካቶች ሐሳባቸውን በማኅበራዊ ገጾች ሲሰናዘሩ አለፍ ሲሉም ከገደብ ያለፉ ጸያፍ ቃላትንም ሲወራወሩ ተስተውለዋል። በተለይ ደግሞ በቅርቡ እውን ይሆናል ተብሎ ከታሰበው የኢሕአዴግ ውህደት ጋር በማስተሳሰር ተማሪዎች በሚማሩበት ትምህርት ተቋም፣ አማኙ ኅብረተሰብ ደግሞ በቤተ ዕምነቱ ሠላሙ እየተጠበቀ ባልሆነበት ሁኔታ እንዴት ውህደቱ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል እንደሚወስን ግራ አጋቢ ነው ሲሉ አስረግጠው የሚናገሩ ነበሩ።

ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ ‹‹የለም! ውህደቱ አሁን እየታየ ላለው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት አይነተኛ ምላሽ የሚሰጥና ምናልባትም ደግሞ ብቸኛው አማራጭም ይሆናል›› ብለው ደግሞ የሚሟገቱም አልታጡም።

በኹለት ጎራ የተከፈለው ይኸው ሳምንት በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የመነጋገሪያ ርዕስ በማድረግ የወሬ መጀመሪያ እና ማሳረጊያ እስኪሆኑ ድረስ በጉንጭ አልፋ ንግግር ተነታርከውበታል። ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ግን ሦስተኛ ጎራ መፈጠሩ አልቀረም። ይኸኛው ጎራ ዩኒቨርስቲዎች ለፖለቲካ ጨዋታ ክፍት ሜዳ መሆን እንደሌለባቸው እና ‹‹ዩኒቨርስቲዎችን ተዋቸው›› መፈክር ያዘሉ ጽሑፎችን በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች ሲያስተጋቡ ሳምንቱን አገባደዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here