“ከአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች ሕጋዊዎቹ ሰባቱ ብቻ ናቸው”

0
567

በአሁኑ ወቅት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ የሚያስቀምጣቸውን ግዴታዎች አሟልተው የሚገኙት ሰባት ብቻ መሆናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። የተቀሩት ፓርቲዎች ሕጉ ከዓመታዊ የሥራ እና የሒሳብ አያያዝ እንዲሁም ከሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ጋር በተየያዘ ጉድለት ያለባቸው መሆኑን አስታውቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/1999 ላይ እንደተደነገገው ፓርቲዎች የሥም፣ የመለያ፣ የአመራር፣ የኦዲተር እና የዋና ጽሕፈት ቤት ለውጥ ሲያደርጉ ለቦርዱ ያላሳወቁ እንደሆነ እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ እና የሒሳብ ሪፖርቶችን ካላቀረቡ ቦርዱ ፓርቲዎችን ከምዝገባ ሊሰርዛቸው ይችላል። ቦርዱ ይህን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሲሆን፥ በማስጠንቀቂያው መሠረት ማስተካከያ እርምጃ ያልወሰደ ፓርቲ ሊሰረዝ እንደሚችል በሕጉ ተቀምጧል።
የኦሮሞ ፌደራሊት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር እና የመድረክ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እንደሚሉት ብዙ ‹የፖለቲካ ፓርቲዎች› የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳልሆኑ መንግሥት ራሱ ያውቃል። “እርምጃ ለምን እንደማይወሰድባቸው ግን አናውቅም፤ ነገር ግን ትንሽ ጠንከር የሚሉት ላይ ሆነ ብለው ጫና ከመፍጠር ባሻገር ለራሳቸው [ለመንግሥት] አገልግሎት የተፈጠሩትን ግን በዝምታ የሚያልፋቸው እንደሆነ እንውቃለን” ይላሉ። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋም በዚህ ሐሳብ በመስማማት “ገዢው ፓርቲ ከምርመራዎችና ቁጥጥሮች ነጻ ሆኖ ሳለ የተወሰኑ ፓርቲዎች ግን ጫና ይበዛባቸዋል” ብለዋል።
መረራ ጉዲና እንደሚሉት ከዚህ በፊትም በነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ ድርድሮች ላይ ሕጋዊ ግዴታቸውን ያልተወጡና የፓርቲነት አቋም የሌላቸው ፓርቲዎች መገኘታቸው ድርድሩን ውጤት አልባ እንደሚያደርገው በማመን ፓርቲያቸው ከድርድሮች ራሱን አግልሏል አሁንም እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ድርድር ማድረጉን ከባድ ያደርገዋል። “የሚመሩትን ፓርቲ በተለመከተ ሕጋዊ ግዴታችሁን ተወጥታችኋል ወይ?” ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ “የእኛን ዓይነት ፓርቲዎች ላይማ ስለሚጨክኑ አያልፉንም፤ የመንግሥት ልጆች የሆኑት ላይ ነው የማይበረቱት” ብለዋል።
የሺዋስ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በሕጉም ሆነ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች እያሟላ ሰባተኛ ዓመቱን ቀጣይ ወር ላይ የሚደፍን እና አራተኛውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሒድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህ ረገድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለሚታየው ክፍተት ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦችን ያቀርባሉ። የመጀመሪያው አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕግ መሠረት ቦርዱ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መጀመር የሚኖርበት መሆኑ ሲሆን “አገር እንመራለን የሚሉ ፓርቲዎች ላይ ከተራ የመንደር ሱቅ ያነሰ ቁጥጥር እና አስተዳደር ሲደረግባቸው መቆየቱ ትልቅ ችግር ነው” ብለዋል። ከዚህ አንፃር እንኳን የተሟላ ሒሳብ አያያዝ ሊኖራቸው ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው የማያውቁና በይፋ ፕሮግራም እንደሌላቸው ያመኑ ፓርቲዎም እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ሁለተኛው መፍትሔ ሐሳብ ደግሞ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ከፍ ያለ የመመዘኛ ደረጃን አካቶ መሻሻል ይኖርበታል የሚል ነው። አንድ ፓርቲ ለመመሥረት መሟላት ያለባቸው የመሥራች አባላት ቁጥርን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች የአገራችንን የፖለቲካ ደረጃ በሚመጥን መልኩ መስተካከል ወይም ከፍ ማለት ይገባቸዋል ሲሉ ያሳስባሉ።
የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ግዴታቸውን ያልተወጡትና በሕጉ መሠረት ከምዝገባ ሊሰረዙ የሚገባቸው ፓርቲዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለመግለጽ እንዳልወሰነ ያስታወቀ ሲሆን በቀጣይ አዲስ የተሰየመው አመራር በጉዳዩ ላይ አቅጣጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here