‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› የተባለ አገር በቀል ድርጅት ባደረገው ጥናት በሳምንት ከ9000 በላይ አህዮች ከኢትዮጵያ እየወጡ ኬኒያ ለሚገኙ ቄራዎች በሕገወጥ መንገድ እንደሚቀርቡ ገለጸ።
በተለይም ‹ስታር ብርሊየት› የተባለ የቻይና ድርጅት አህዮቹን ያቤሎ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኪናማ ገበያ እንደሚገዛ ባለፈው አንድ ወር የተደረገውን ጥናት በማስረጃ አስደግፎ ‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› አቅርቧል።
በሳምንት ለሦስት ቀናት ክፍት የሆነው ገበያው በአንድ ጊዜ ከ3000 በላይ አህዮች ለኬኒያ ቄራዎች እንደሚቀርቡና ይዘታቸውም ጠንካራ ፣ ጤነኛና ዋጋቸውም ከፍ ያለ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ችላለች።
የ‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› ጥናት እንደሚያሣየው አህዮቹ እንዳሉበት ሁኔታ ከብር 1600 እስከ 3000 ይሸጣሉ። በሌላ በኩል በኬኒያ የቄራዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ፥ የአህያ ዋጋ በሁለት እጥፍ በመጨመር ከብር 2300 እስከ 3380 ይደርሳል።
የኬኒያ መንግሥት ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ለሚገቡት አህዮች፣ በእያንዳንዱ ከብር 50 እስከ 60 ቀረጥ እንደሚያስከፍልም ከ‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› ጥናት መረዳት ተችሏል። በኬኒያ ከኪናማ የገበያ ማዕከል እንዲሁም ከናይሮቢ 92 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ስታር ብርሊየንት የተባለው የአህያ ቄራ በኬኒያ ባጋጠመው የአህዮች ቁጥር መመናመን ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን ማዞሩን መረጃዎች ያሳያሉ።
በዶንኪ ሳንክቿሪ ጥናት መሠረት ግብይቱ በጉጂ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በኬኒያ በሚኖሩት የቡርጂ ነጋዴዎች መካከል እንደሚደረግ አሣይቷል። ይህንን የተረዱት ባለፈው ዓመት የተዘጋው የሻንግ ዶንግ በደብረዘይት የሚገኘው የአህያ ቄራ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዛሀሁአ ሊዩ ንግዱ በቅርብ ጊዜያት እየተጠናከረ መምጣቱን ያስረዳሉ። “የመንግሥት ቁጥጥር በመላላቱ ምክንያት የተበራከተው የሕገ ወጥ ንግድ ድርጅታቸውንም ሆነ አገሪቷን በጣም እየጎዳ” መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህንን ያመኑት የጥናት ባለሙያው ፍፁም አለማየሁ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በአህያ ቁጥር ቀዳሚ መሆኗ፣ የኬኒያም ሆነ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የሞያሌ ድንበርን በቀላሉ ለማቋረጥ የሚችሉ መሆናቸውና በቻይና ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ለሕገወጥ ንግዱ መስፋፋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ ጥናቱ በአንድ ገበያ ሽያጭ ብቻ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ፍፁም በሌላ አገርም ሆነ በኬኒያ በኩል በጥናቱ ከተጠቀሰው በላይ አህያ ኬኒያ ላሉ ድርጀቶች እንደሚሸጡ ጠቁመዋል።
ከ1.8 ሚሊየን በላይ አህዮች ባሏት ኬኒያ ውስጥ ሦስት የአህያ ቄራዎች የሚገኙ ሲሆን አገሪቷ በዓመት 44 ሚሊየን ዶላር ከእንስሳው ቆዳና ሥጋ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ታገኛለች። በቀን ከ400 እስከ 600 የሚያስፈልጋቸው ቄራዎቹ እያረቡ ማረዱ በቂ ስላልሆነ ከጎረቤት አገራት ማለትም 8 ሚለየን የሚጠጉ አህዮች ካሏት ኢትዮጵያ እስከ ታንዛኒያ የዘለቀ የአህያ አቅራቢዎችን መሥመር ዘርግተዋል።
የ‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› ጥናት እንደሚለው ከሆነ፣ ቻይና በየዓመቱ 5 ሺሕ ቶን “ኢጂኣኦ” የምታመርት ሲሆን ለዚህም 4 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ ያስፈልጋታል። በዚህም የተነሳ ይህንን በራሷ ማሳካት የማትችለው ቻይና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ የአህያ ሀብት ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ቄራ መክፈቱ እንደ አማራጭ ወስዳለች። ይህንንም ዕድል ለመጠቀም ከ10 ዓመት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት ድርጅቶች ቄራ እንዲገነቡ ፍቃድ ሰጥቶ ነበር። በወቅቱም አገሪቷ ፈቃዱን ስትሰጥ ጠለቅ ያለ ጥናትም ሆነ ለመቆጣጠር ሕግ አልነበራትም።
ነገር ግን ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ተጨማሪ ፈቃድ መንግሥት መስጠት ቢያቆምም፣ ሁለቱም ድርጅቶች ግንባታቸው ቀጥለው ከዚያም ሻንግ ዶንግ የተባለው ድርጅት በ2009 ሥራ ጀምሮ እንዲያቋርጥ ትዕዛዝ ከመሰጠቱ በፊት ወደ 2000 አህዮችን አርዶ ሥጋውን ወደ ቬትናምና ቆዳውን ደግሞ ወደ ቻይና ልኮ ነበር።
ድርጅቶቹ ቄራዎቹን በጠቅላላው ወደ 140 ሚሊየን ብር በሚያወጣ ገንዘብ ቢያቋቁሙም ሁለቱም ፋብሪካዎቹ የሚገኙበት የኦሮሚያ ክልል ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ለጉዳዩ እልባት እስካሁን መስጠት አልቻሉም። ጉዳዩም በዚህ ሁኔታ እያለ ነበር በሞያሌ በኩል ገበያው የተጧጧፈው።
ቄራዎቹ ይዘጉ ወይስ ይቀጥሉ የሚለው ጥያቄ ላይ ውሳኔ መስጠት ያቃተው መንግሥት አቋሙን በግልጽና በፍጥነት አለማሳወቁ የአገሪቷን የአህያ ሀብት እየጎዳ መሆኑን የጥናት ባለሙያው ፍፁም ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ 850 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጣ ከዚህ ቀደም የተደረገ ጥናት ጠቀሰው የተናገሩት ፍፁም በመንግሥት ቁጥጥር፣ ጥናት፣ ፖሊሲ ቀረፃ፣ ከሕግ አንፃር ሲታይ ለአህያ ንግድና እርባታ የሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ እንደሆነና አገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት እንደሆን ያስረዳሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ሳሕሉ ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን የአህያ ሀብት በመገንዘብና የተበራከተውን የሕገወጥ ንግድ ለመቅረፍ ፖሊሲ እየቀረፀ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። “የአህያ ቆዳና ሥጋ ለአገሪቷ ሊያመጣ የሚችለውን ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሬ ከግምት ውስጥ ቢያስገባም ያለውን የመቆጣጠር ብቃት፣ እርባታው እንዴት ይደረጋል በሚለው ዙሪያና የሕዝቡ ተቀባይነት ምን ይመስላል በሚሉት ጉዳዮች ጠንካራ ሥራዎች ከተሠሩና ወይይቶች ከተደረጉ በኋላ የሁለቱ ቄራዎች ዕጣ ፈንታ ይወሰናል” ብለዋል።
በዓለም አህያን ለመድኃኒት መጠቀም እንደሚቻል ከምዕተ ዓመታት በፊት ያበሰረችው ቻይና ከዛሬ ሀያ ዓመታት በፊት 11 ሚሊየን በላይ አህዮች የነበሯት መሆኑን መረጃዎች ቢያሳዩም ቁጥሩ በአሁኑ ወቅት ወደ ስድስት ሚሊየን አሽቆልቁላል። ዋነኛ ትኩረታቸው ቆዳው ላይ ያደረገችው ቻይና የአህያ ቆዳ በመቀቀል “ኢጂኣኦ” የተባለ “ጄላቲን” ትሠራለች። ይህንንም የተለያዩ ጥናቶች አንደሚያሳዩት ለደም ዝውውር፣ ሰውነትን ከበሽታ ለመከላከል፣ የራስ ማዞር፣ የእንቅልፍ ዕጦትን፣ ሳል፣ የወር አበባ አለመስተካከልን ለመከላከልና ለማከም ቻይኖች ይጠቀሙበታል።
‹ዶንኪ ሳንክቿሪ› በአገሪቷ የሚገኙ ሕዝቦችን ይወክላሉ ባላቸው ከተለያዩ አካባቢዎች 257 ሰዎች ላይ ባጠናው ጥናት 91 በመቶ ዜጎች እንደማይቀበሉት ከወር በፊት ባለቀው ጥናቱ አስነብቧል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከፊሎቹ ባሕልንና ሃይማኖትን ላለመቀበላቸው እንደ ዋነኛ ምክንያት ሲያነሱት ሎሎቹ ደግሞ የአህያ ቁጥር መቀነስን ፣ አህያ ለማኅበረሰቦች ያለውን ጥቅም ፣ ለእንስሳቱ ደኅንነት አስጊ መሆኑንና ሌሎች ምክንያቶችን አንስተዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011