የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከደረቅ ወደቦች ዕቃ ለማንሳት የሚያስችሉ 13 ማሽኖችን በ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዩሮ ግዢ ፈፀመ። ከነዚሁ ማሽኖች መካከል ሰባቱ ከጅቡቱ ተጭነው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው። ስድስቱ ደግሞ ወደ ጅቡቲ ጉዞ ላይ ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ የሆኑት አሸብር በደረቅ ወደቦች ከፍተኛ የእቃ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል። በደረቅ ወደቦች የእቃ ክምችት መብዛት በወደቡ ውስጥ መጨናነቅ ከመፍጠሩም በተጨማሪ ወደ አገር ውስጥ የገቡት እቃዎች በወቅቱ ወደ ገበያ ባለመግባታቸው የገበያ አለመረጋጋትን ይፈጥራሉ ብለዋል። ለተራዘመ ጊዜ የእቃዎች በደረቅ ወደብ መቆየት በውጪ ግዢ የገቡ ዕቃዎች ከጅቡቲ የባሕር ወደብ በጊዜ ተነስተው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ቦታ ይይዛሉ። ኃላፊው አክለውም “ይህም ለጅቡቲ የባሕር ወደብ ተጨማሪ ክፍያዎችን እንድንከፍል በማድረግ የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ያባብሳል” ብለዋል።
አዲስ የተገዙት ማሽኖች በደረቅ ወደብ ያሉ ዕቃዎች ቶሎ እንዲነሱ ያግዛሉ። ከዐሥራ ሦስቱ ማሽኖች አምስቱ በሞጆ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በቃሊቲ፣ ገላን፣ ሰመራ፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬዳዋና መቀሌ ደረቅ ወደቦች የሚተከሉ ይሆናል።