አዲስ አበባ በጥበባት መነጽር

0
900

የሰው ልጅ ኑሮ ዛሬን አሳልፎ ትላንት በማድረግ ጉጉትና፣ ትላንትን ሰንዶ አስቀምጦ ለነገ በማቆየት መጠመድ ውስጥ የተቋጠረ ይመስላል። ለዚህም ነው ወደኋላ ታሪክ እና ትዝታ ወደ ፊት ደግሞ ተስፋ በጉልህ የሚታዩት። በዚህ መልኩ የአዲስ አበባን ገጽታ በፎቶ አስቀርቶ የዛሬን ዐይን የሚገልጥ ለነገም ሰነድ የሚያስቀምጥ መድረክ ከኹለት ሳምንት ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ጊቢ ሲካሔድ ነበር።

‹‹አዲስን እናንሳ›› (Capture Addis) የተሰኘው ይህ አውደ ርዕይ ከመከፈቱ ቀድሞ ማንኛውም ሰው ፎቶ በማንሳትና በመላክ እንዲሳተፍ ጥሩ ቀርቦ እድሉ ተከፍቷል። ይህንን ተከትሎ ከባለሙያው የተረፈውን ባለሞባይሉ፣ ባለሞባይሉ ያለፈውን ደግሞ ባለሞያው ይዘው ያቆዩትን፣ አቅርበው አዲስ አበባን በፎቶ የሚያስቃኝን አውደ ርዕይ እውን ሊያደርጉ ችለዋል። በማዘጋጃ ጊቢ በተካሔደው ይህ አውደ ርዕይ በቆየባቸው ቀናት ማምሻውን በተከናወኑ የውይይት መድረኮች ደግሞ አዲስ አበባ ከተለያዩ ጥበባት አንጻር ተቃኝታለች።

መጽሐፍት
አዲስ አበባ ለበርካታ የልብ ወለድ መጻሕፍት መቼት ሆና አገልግላለች። ታድያ ግን ሰፈሮቿ በስም ይጠሩ እንጂ መልካቸውና ገጽታቸው በጉልህ ተቀምጦ አይታይም። ይህን ያነሱት የሥነ ጽሑፍ መምህርና ሃያሲ መሠረት አበጀ፤ አንድ አንባቢ ቀድሞ ወደ ሐሳቡ የሚመጡ ልብ ወለድ መጻሕፍትን ጥራ ቢባል የአብዛኞቹ መቼት አዲስ አበባ ስለመሆኗ ይገልጻሉ።

በዓሉ ግርማ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ዘነበ ወላ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ አውግቸው ተረፈ እና ሌሎችም ደራስያን በዚህ ይጠቀሳሉ። ‹‹የደራሲ ግብ አንባቢን በመንፈስ መንጠቅ ነው›› የሚሉት መሠረት፤ መጻሕፍት ተደራሲ ሊያውቀው ከሚችለው በታች መስጠት የለባቸውም ሲሉ ይከራከራሉ። እናም መቼትን በተመለከተ ያለውን አሳድጎ ማቅረብና ፈጠራን ማከል እንዲሁም ገለጻን መጨመር ያሻል ይላሉ።

የመሠረት ሌላው ነጥብ፤ ደራስያን ገጸ ባህርያቱን ኳኩለውና አሳምረው፣ ተደራሲ የሚያወቃቸው ያህል እንዲሰማውና በዐይነ ሕሊናው እንዲስላቸው አድርገው ሳለ፣ ለመቼት ግን የዛን ያህል ሲጨነቁ አይታይም። እናም ለመቼት በተለይም ‹‹የት›› ለሚለው፣ ለስፍራው ትልቅ ዋጋ እየተሰጠ እንዳልሆነ ትዝብታቸውን ያስቀምጣሉ።
የአዲስ አበባ የድህነት፣ የመከራና የሰቆቃ ገጾች እየታዩ የመሻሻሉ ተስፋስ ወዴት አለ ሲሉም ይጠይቃሉ፤ መሠረት። ይህንንም ያሉት ከመቼት አንጻር ብቻ ነው። ‹‹ድርሰት ኃልና ጉልበት ነው። አዲስ ነገር መጨመርና ማነቃቃት ላይ ልንጠቀምበት እንችላለን፤ በዛ መልኩ የሆነ የመቼት ምልከታ ሊኖር ይገባል።›› ብለዋል፤ የሥነ ጽሑፍ መምህርና ሃያሲ መሠረት አበጀ።

ሙዚቃ
‹‹ሙዚቃ ማህበረሰብን ለማቀራረብና አንድ ለማድረግ ያግዛል።›› ያለው አዲስ አበባን ከሙዚቃ ስፍራነት አንጻር የቃኛት ሙዚቀኛና ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ ነው። ሙዚቃ በከተማ እድገት ውስጥ የራሱ የሆነ ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው ያለው ሳሙኤል፤ ይህም እንደ አገር የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማየት ይረዳል ባይ ነው።

አዲስ አበባን በተመለከተ እስከ አሁን ሙዚቃ የነበረውን ድርሻ ለማየት የተደረገ ጥናት አለመኖሩን ሳሙኤል ያወሳል። ከተማዋ ለሙዚቃ፣ ሙዚቃው ደግሞ ለከተማዋ ያበረከቱት ነገር ባለመታወቁም፤ ሙዚቀኛውም ሆነ ከተማዋ ሳይናበቡ በየራሳቸው መስመር እንዲሔዱ አድርጓቸዋል።

ይህም ሆኖ ታድያ አዲስ አበባ የሙዚቃ ከተማ እንደሚባሉት ሁሉ በዛ ደረጃ ልትጠራ ትችላለች። የተለያዩ ፌስቲቫሎች የሚከናወንባት መሆኗ፣ መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ ከሙዚቃ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ማረፊያም ስለሆነች ነው። በሌላ አገላለጽ አዲስ አበባ የሙዚቃ ማዕከል ነች፤ የሳሙኤል ምልከታ ነው።

ነገር ግን ከሌሎች የሙዚቃ ከተሞች የምትለይበት ጉልህ መገለጫ አላት። ይህም ምንም ዓይነት የሙዚቃ ስልት ይዞ ለመጣ ሁሉ ክፍት የሆነችና ብቸኛዋ እድል ያለባት ከተማ ሆና መገኘቷ ነው። ከተለያዩ ከተሞች ሙዚቃን የሚሠሩ ሙዚቀኞች ሳይቀሩ አዲስ አበባ መጥተው ነው ተመልሰው ወደ መጡበት ከተማ ሥራቸውን ይዘው የሚያቀኑት። የሙዚቃ ገበያው በአዲስ አበባ ላይ ማዕከል አድርጓል።

ነገር ግን በዛ ልክ አውድ አልተፈጠረባትም፤ ሳሙኤል ይርጋ የሚቆጭበት ነጥብ ነው። የሙዚቃ ስፍራዎች፣ ስቱድዮዎችና ቀን ቀን ሙዚቃ የሚቀርብባቸው መድረኮች የሏትም። ‹‹ሙዚቃውን ለማሳደግ የሚያግዝና ለዛ ታስቦ የተዘጋጀ ስፍራ አይገኝባትም።›› ይላል።

በድምሩ ግን ለሙዚቃ ባልተሰጠ ትኩረት የተነሳ ሙዚቃውን ‹‹ዘርፍ›› ብሎ ለመጥራት አስቸጋሪ አድርጎታል። አዲስ አበባም ልታገኝ የሚገባውን ጥቅም ልታገኝ ያልቻለችው በዚህ ምክንያት መሆኑን ሳሙኤል ይገልጻል። ከገቢ አንጻር ሌሎች አገራት ጥቅሙን አይተው ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡትና እንደተጠቀሙበት በማንሳት ለአዲስ አበባም በተመሳሳይ እንድትጠቀም፤ እንደ አገር ሙዚቃውንም እንድትጠቅም ከባለሙያዎች ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን መወጣጥ አለበት ብሏል።

ኪነ ህንጻ
በ‹‹አዲስን እናንሳ›› የፎቶ አውደ ርዕይ ክዋኔ ላይ ከቀናት በአንዱ የአዲስ አበባን ትዝታዎች ከኪነ ህንጻ (Architecture) ጋር የሚያያይዝ ውይይት ተደርጓል። በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ያጋሩት የኪነ ህንጻ ባለሙያ ማህደር ገብረመድኅን፤ ኪነ ህንጻ የትላንት ትዝታን የሚያቆይ፣ የዛሬን በራሱ መንገድ የሚቀርጽ፣ የነገም ትዝታ ላይ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችል ዐቢይ የኪነጥበብ ዘርፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኪነ ህንጻ ለውጥም ከማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ጋር ይያያዛልአ አሉ። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ክስተቶች እንዴት ነገሮችን እንዳይመለሱ አድርገው እንደሚቀይሩ ማህደር በማሳያ አስቀምጠዋል። ይህም ለምሳሌ ከ1966 ቀደም ብሎ ታቅዶ የነበረው የከተማ ፕላን ነው። በዚህም ከዓድዋ አደባባይ በቸርችል ጎዳና እስከ ፒያሳ ሊሠራ የታሰበ ሥራ ነበር። ነገር ግን በ1966 የፈነዳው አብዩት እቅዱን አስቀርቶት አካባቢው አሁን ያለውን ገጽ እንዲይዝ አድርጓል። ማህደርም ‹‹በአንድ አብዩት አርክቴክቸሩም ተቀይሯል፤ ትዝታችንንም አብሮ ቀይሮታል።›› ሲሉ ይገልጹታል።

ማህበራዊ ኑሮም ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ሳይጠቅሱ አላለፉም፤ ይህም በአዲስ አበባ በጉልህ ይታያል። ማህደር እዚህ ላይ በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ ኪነ ህንጻ መገለጫ እየሆነ ያለውን ኮንዶሚንየም ቤት ጠቅሰዋል። ኪነ ህንጻ የማህበረሰቡን አኗኗር ከግንዛቤ ያላስገባ ሲሆን ችግሮች እንደሚፈጠሩም ጠቅሰዋል።

‹‹ኪነ ህንጻው ለምንፈልገው የኑሮ ሒደት ቦታ ካልሰጠ ማህበረሰቡ የራሱን እርምጃ ይወስድና ግንባታው የታሰበለትን ዓላማ ይቀይሩበታል።›› ይላሉ። እናም ኪነ ህንጻ ለተሠራለት ዓላማ ማገልገል እንዲችል ትውልድና አስተሳሰብን ማግኘት መቻል አለበት። ካልሆነ አገልግሎት ላይ አይውልም፤ የማህደር ገለጻ ነው።

ታድያ በዚሁ አንድ ስጋታቸውን አጋርተዋል፤ ይህም ወደፊቱ እንደ ከተማ አዲስ አበባውያን የሚጋሩት ትዝታ ሊቀንስ ይችላል የሚል ነው። በቀደመው ጊዜ የተወሰነ ጋዜጣ፣ ከአንድ ያልዘለለ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና ራድዮ እየሰማ የኖረና ያደገው የማህበረሰብ ክፍል፣ የኑሮ ደረጃው ቢለያይ እንኳ ተመሳሳይ ትዝታን የመጋራት እድል ነበረው። አሁን ግን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ብዙ አማራጭ በሰጠበት ወቅት ይህ ነገር እንደሚቀንስ ነው ያነሱት።

ፊልሞች
አዲስ አበባን የሚወዱ፣ የሚሳሱላትና የሚኖሩባት እንዲሁም በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ ታዳሚ በሆኑበት በዚህ መድረክ፤ የሚሰጠው አስተያየትም ብዙና ሰፊ ነበር። በውይይት ሰዓት በኪነጥበቡ ዘርፍ ፊልም ለብቻው ከአዲስ አበባ ጋር በተገናኘ በውይይት ርዕስነት አልተጠቀሰም። ሆኖም አስተያየት ከሰጡ የተለያዩ ባለሙያዎች መካከል የመቅረጸ ምስልን ነገር ከአዲስ አበባ ጋር አቆራኝተው ያነሱ አልጠፉም።

የፊልም ባለሙያው ሰውመሆን ይስማው (ሶሚክ) አዲስ አባባ ለፊልም ሥራ ምን ያህል አስቸጋሪና ከባድ እንደሆነች ጠቅሷል። አሁን ላይ ይሄ ነው የሚባል የራሷ የሆነ ቀለም የሌላት በመሆኑም የፊልም ባለሙያዎች በመቼት ደረጃ የአሁኗን ሳይሆን የቀደመችውን አዲስ አበባን ከምናብ ጓዳ ፈልፍሎ አውጥቶ በካሜራ ዐይን ማሳየትን ለመምረጥ ይገደዳሉ/ እንገደዳለን ይላል።

አንዳች ባህሪ ያለው የከተማ ቀለም፣ አዲስ የሆነ እይታን ማውጣት ይስበኛል የሚለው ሰውመሆን፣ አዲስ አበባ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ብዙ እንዳላዘጋጀ ይጠቅሳል። ካሜራውን ዝግጁ አድርጎ ለቀረጻ ሲነሳና ‹‹ምን የተለየ ነገር አለ?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ አዲስ አበባ ለዚህ አጥጋቢ ምላሽ ሰጥታው እንደማታውቅና መልስ ማግኘት አዳጋች ሆኖበት እንደሚያውቅ ከልምዱ ያለውን ጠቅሷል። ‹‹ስለዚህ አዲስ አበባን በተመለከተ መጻፍ ካለብኝ 1960ዎቹ ነው የምለው። በዛ ዘመን ላይ ሊሆን የሚችለውን በምስል እያሰብኩ ነው የምሠራው።›› ሲል ያክላል።

ከዚህ በተጨማሪ ለእይታ አዲስ ነገርን ያመጣሉ የተባሉ አካባቢዎችንና ህንጻዎችን ፈልጎ ማግኘትም አስቸጋሪ ነው። ለዚህም ነው በርከት ያሉ ፊልሞች ትዕይንቶቻቸው ከቤት ውስጥ የሚሆኑት። እንደ ሰው መሆን ገለጻ እንደውም ውጪው ተበላሽቷል፤ ለቀረጻ አስቸጋሪና ምቹ ያልሆነ ነው። ጉራማይሌ መሆኑም ለዚህ ዳርጎታል ባይ ነው።

በተመሳሳይ የፊልም ባለሙያ የሆነችው መዓዛ ወርቁ ሐሳቧን ያካፈለችው ከአንድ ገጠመኟ በመነሳት ነው። አንዲት ኡጋንዳዊት ደራሲ አዲስ አበባ ተገኝታ ዙሪያ ገባውን ማየት ፈለገች፤ አንዳች አዲስ ነገር ለማየት በመጓጓት። መዓዛም አዲስ አበባን አስጎበኘቻት፤ ነገር ግን እንግዳዋ ኡጋንዳዊት አልተደነቀችም፤ አዲስ ነገር እንዳላየች ሆነች።
‹‹ለእኔ አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ናት፤ ለምን አላየቻትም/አልታየቻትም ብዬ አሰብኩ።›› ትላለች መዓዛ። እናም ያቺ ኡጋንዳዊት እንድታይላት የምትፈልጋቸውን ስፍራዎች አሁን ላይ የፊልሞቿ መቼት አንድ አካል አድርጋ ታስቀራቸው ጀመረች። ‹‹በዚህ ትንሽ እርካታ ላገኝ እሞክራለሁ።›› ስትል በአስተያየቷ መካከል ተናግራለች።

በተጓዳኝ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚታዩ ፊልሞቸ ላይ አዲስ አበባን በምስል ሰንዶ የማስቀመጥ ሩጫ እንደሚታይ ነው የጠቀሰችው። የአዲስ አበባ መልክ እያደር እየተቀየረና እየተለወጠ ስለሚሔድ።

የእይታ ጥበባት
የሥነ ጥበብ ባለሙያና በሥነ ጥበብ ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ‹‹አዲስ አበባ፤ ምናብና ምስል›› በሚል ርዕስ መወያያ ሐሳብ አቅርበው ታዳሚን አነጋግረዋል። ባቀረቡት ሐሳብ ከሚታየው ይልቅ ስፍራን ለመረዳት የምናብን ጥንካሬ አንስተዋል። ለማሳያነት ከአዲስ አበባ ሰፈሮች መካከል የተወሰኑትን እያነጻጸሩ ጠቀሱ።
‹‹ጨርቆስን በቦሌ ፊት ደረቷን ነፍታ እንድትቆም ያደረጋት ምናብ ነው›› የሚለው ካነሱት ማሳያ መካከል ነው። ለምን ሲባል ስለ ጨርቆስ የሚያነሱ ሰዎች ጨርቆስን በቁሟ (በሚታይ መልኳ) አያይዋትም። ይልቁንም በነዋሪዎቿና በውስጧ ባለ ሙቀትና የሕይወት መስተጋብር ነው የሚመለከቷት። ይህም ስፍራንና አካባቢን በቁሙ እንደማንፈርጅና ይልቁንም ምናብ የላቀውን ስፍራ እንደሚይዝ ያሳዩበት ነጥብ ነው።

ይህ ታድያ በጎ ጎን አለውም ብለዋል። ‹‹ድህነታችንን ከወንጀል አርቆ ያቆየው ይህ ምናብ ይመስለኛል።›› ያሉት በቀለ፤ እነዚህ ምናቦች በማህበራዊ ጉዳይም ማህበረሰቡን አቻችለው ያቆዩ ናቸው ሲሉ ምልከታቸውን ገልጸዋል። ይህም ምናባዊነት የሚሰጠው ጠቀሜታ ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል።
በፎቶና በምስል ሲታይ ግን ስፍራን በቁም ማየት ግድ እንደሚል ያነሳሉ። ታድያ አካባቢን በመረዳት ምናባዊነት የጠቀመው ነገር መኖሩ እንዳለ ሆኖ፣ በአንጻሩ ግን ሊሞላ የሚገባ ክፍተት እንዳለና አካባቢን በቁሙ አይቶ ማሻሻል ላይም ትኩረት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

አዘጋጆቹ ምን አሉ?
ከተከናወነ ከአንድ ሳምንት የዘለለው ይህን የፎቶ አውደ ርዕይ ስናነሳ አንዴ ታይቶ የሚጠፋ ክዋኔ እንደማይሆን በማመን የተነሱ ሐሳቦችም ለብዙዎች ቢደርሱ እይታን ሊያሰፉ ይችላሉ ከሚል እይታ አንጻር ነው። ታድያ የ‹‹አዲስን እናንሳ›› የፎቶ አውደ ርዕይ አዘጋጆች መካከል ሐሳቡን ለአዲስ ማለዳ ያካፈለው አክሊሉ ገብረመድኅን፤ በቀጣይም ይህ ክዋኔ እንደሚኖርና ዓመታዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በዚህ የመጀመሪያ በሆነው ክዋኔ ጥሩ ግብረ መልስ ማግኘታቸውን ያነሳው አክሊሉ፤ በቀጣይ ፎቶ ግራፍ በማንሳት የሚሳተፈውን ባለሙያ እና ባለሙያ ያልሆኑም ሆነው ፍላጎት ያላቸውን ተሳታፊዎች፣ የዳኞች ቁጥር ከፍ እንዲል እቅድ እንደተያዘ፤ እንዲሁም የተሰጠውን የወርክሾፕ ጊዜ ለማፋት እንደታሰበም ጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለአውደ ርዕዩ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ መንገድ ዝግጅቱን ደግፏል። ‹‹ቃል የተገባልን ነገር ተፈጽሞ አይተናል›› ያለው አክሊሉ በቀጣይም የከተማ መስተዳደሩ ድግፍ እንደሚኖር ተስፋ እንዳለ ጠቅሷል። በተያያዘም በዚህ ክዋኔ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግና አዲስ አበባን ሰንዶ በማቆየትና በማክበር በኩል መሳተፍ ለሚፈልጉ ሁሉ በራችን ክፍት ነው ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here