የብዙኀን አምባገነንነት በሥመ ፌዴራሊዝም

0
1022

በግርድፉ ሙገሳና ትችት የሚነሳበት የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም፣ ስላስመዘገበው ጠንካራና ደካማ ጎን ብዙ አልተወራለትም። ስርዓቱ መፍትሔ ያመጣለታል የተባለውን የኢትዮጵያን ችግር በተለየ አቀራረብ መልሶ እንዳመጣ የሚጠቅሱት በፍቃዱ ኃይሉ፤ ያደረገው አስተዋጽኦ ቢኖርም የተለያዩ ግጭቶች እንዲነሱ መንስዔ ሆኗልም ይላሉ። የቡድን መብቶችም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖች ለመጠበቅ የሚከበሩ እንጂ ብዙኀን አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሕዝቦች ላይ ያላቸውን የበለጠ ተጠቃሚነት የሚጨምሩበት መሆን የለበትም ሲሉም ይሞግታሉ።

ስለኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ብዙ ተብሏል። እንደ ቅዱስ መና የሚያዩት እንዳሉ ሁሉ፣ እንደ ርኩስ ምፅዓት የሚፈርጁት አሉ። “ችግሩ በአግባቡ አለመተግበሩ ነው” የሚሉትን ያክል፣ እንዲያውም አለመተግበሩ “እስካሁን ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ አድርጓታል” የሚሉ አልጠፉም። “አውራ ነኝ” የሚል አንድ “ማዕከላዊ ዴሞክራሲን የሚተገብር” ፓርቲ፣ ፌዴራሊዝምን በስርዓቱ መተግበር አይችልም የሚሉት እንዳሉ ሁሉ፥ እንዲያውም “ያልተማከለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ቢኖር ኖሮ ብዙ ትንንሽ አገሮች እንሆን ነበር” የሚሉ ይገኛሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ከተፈተነ በኋላ ስላስመዘገበው ጠንካራ እና/ወይም ደካማ ጎን እምብዛም አይወራም።

ኢትዮጵያ ብዝኀነት የመላባት አገር ነች፤ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ የተለያዩ አኗኗር ዘዬዎች (አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወዘተ.) የተለያዩ ማኅበራዊ ስርዓቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ያሏቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ነች። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን የሚረዱበት መንገድ፣ ባሕላዊ ዕሴቶቻቸው እና እምነቶቻቸው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፍላጎቶቻቸው እና አቅሞቻቸው የተለያዩ በመሆናቸው ይህንን ከግንዛቤ ያስገባ ያልተማከለ አስተዳደር ያስፈልጋቸዋል የሚለው ብዙኀንን ያስማማ ይመስላል።

በዚህ ረገድ ፌዴራሊዝም ተመራጭ ስርዓት ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ስርዓት አንዱ ጠንካራ ጎኑ ምናልባትም ፌዴራላዊ መዋቅር መፍጠሩ ነው። ነገር ግን ፌዴራላዊ መዋቅሩ በዘውግ መሥመር መሠመሩ ራሱን የቻለ ሌላ የቀውስ ምክንያት ሆኗል ለማለት በቂ ማስረጃዎች አሉ።
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከፈጠራቸው ችግሮች እምብዛም ያልተወራለት ገና ሲዋቀር “ይፈታዋል’’ ተብሎ የታሰበው ችግር በተለየ አቀራረብ መቀጠሉ ነው። የዜጎችን የራስን ዕድል በራስ መወሰን ጉዳይ በተለይ በቁጥር አናሳ ለሆኑት ሕዳጣን ‹ከድጡ ወደ ማጡ› ሆኖባቸዋል።

የክልሎች የዘውግ ብዝኀነት
ምንም እንኳን ዘውግን መሠረት ያደረጉ ክልሎች መመሥረታቸው የዘውጎቹን ባሕሎች እና ቋንቋ የማሳደግ አስተዋፅዖ ቢያሳይም የተለያዩ ግጭቶችም እንዲነሱ መንስዔ ሆኗል። ይህንንም ጆን አቢንክ ‘ጆርናል ኦፍ ኢስት አፍሪካን ስተዲስ’ ላይ እ.ኤ.አ. በ2012 ባሳተሙት ‘Ethnic-based federalism and ethnicity in Ethiopia: reassessing the experiment after 20 years’ ባሰኙት ጽሑፋቸው አትተዋል። ይሁንና ብዙ ጊዜ የዘውግ ግጭት (ethnic-conflict) እየተባለ በመጠራቱ ባይሥማሙም፥ በድንበር፣ በውሃና መሬት ሀብት ግጭቶች ፌዴራሊዝማዊ መዋቅሩ ከተዘጋ በኋላ መባባሳቸውን ተናግረዋል። ግጭቶቹን ተከትሎም “ልዩ ወረዳ” የሚባሉ አከላለሎች የተፈጠሩ መሆኑን የጠቆሙት ጆን አቢንክ፣ ለብዙዎች ነፍስ መጥፋት መንስዔ ከመሆናቸውም ባሻገር መቻቻል ጠፍቶ አግላይነት (exclusivist claim-making) መባባሱን ጠቁመዋል።

በዚህም እንደ አቢንክ ጥናት “በታሪካቸው እንደዚህ ባይሆኑም ግዛቶች ዘውጋዊ-አሀድነት (mono-ethnic) አባዜ ተጠናውቷቸዋል፤ ከአንድ በላይ የሆኑ የዘውግ አባላት በጋራ ሊኖሩባቸው አልቻሉም” ሲሉ፤ “የጋራ ዜግነት የሕገ መንግሥቱ እና የዜጎች መብቶችን መሠረት አድርጎ አለመበልፀጉ” ጣጣ እንዳስከተለም አክለው ጽፈዋል። “የዘውግ ፌዴራሊዝም በተቋማዊ አደረጃጀቱ የዘውግ ማንነትን ከሌሎች ማንነቶች ሁሉ (ለምሳሌ የመደብ፣ የዜግነት፣ የሥራ፣ የሃይማኖት፣ ወይም የፆታ ማንነቶች) ያስበልጣል።

በነባራዊ ሁኔታዎች ግን ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ከዘውግ ማንነት የበለጠ አስፈላጊ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። በዚህም ምክንያት አካታች አገር ዐቀፍ ተዋስዖ ከልማት እና ኢኮኖሚያው ዕድገት ጋር ተያይዞ ካልሆነ በቀር፥ በዴሞክራሲያዊ አፈፃፀም፣ በሰብኣዊ መብቶች አከባበር፣ ወይም በሁለገብ ድህነት ቅነሳ እና የሰብኣዊ ልማት መለኪያ መሥፈርቶች ዙሪያ ማድረግ አልተቻለም።

ክርስቶፍ ቫን ደር ቤከን የተባሉ የጌንት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. በ2007 ባሳተሙት “Constitutional Protection of Ethnic Minorities at Regional Level” በተሰኘው ጥናታቸው፣ የክልሎችን የውስጥ ብዝኀነት ሲያወዳድሩ የተመለከቱት ልዩ ዞኖችን ነው። በፌዴራሉ አባል ክልሎች ውስጥ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን እስካሁን ለመፍታት የተሞከረው ልዩ ዞኖችን በመመሥረት ነው። በተለይም በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች ሕገ መንግሥት ያለው ትልቁ ልዩነት የአማራ ክልል ሕገ መንግሥት በውስጡ ላሉ ቡድኖች የራስን ዕድል የመወሰን ሥልጣን ሲሰጥ፥ የኦሮሚያ ክልል ግን እንደነፈገ ያስረዳሉ። በኦሮሚያ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ነዋሪዎች ልዩ ዞን እንዳይኖራቸው ተበታትነው የሚኖሩ መሆናቸው ይጠቀሳል። ይህም የልዩ ዞን መፍትሔነት በክልሎች ውስጥ ብዝኀነትን ለማቀፍ ሁነኛው ዘዴ/መፍትሔ አለመሆኑን ማሣያ ነው።

አስተሳሳሪ ወይስ ሰባባሪ?
የፌዴራል ስርዓት [ብዙዎቹ] ቀድሞ ሉዓላዊ በነበሩ አገራት በጎ ፈቃድ የሚፈፀም አስተዳደራዊ ጋብቻ በመሆኑ “ወደ አንድ መምጣት” (coming together) የሚለው ይገልጻቸዋል። የኢትዮጵያው ግን “ልዩነታቸውን ለማስታረቅ” የተፈጠረ ነው በሚል፥ ምሁራን “አስተሳሳሪ” (holding together) በሚል መግለጫ ይጠቅሱታል። ሆኖም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም መዋቅር ክልሎችን ቀስ በቀስ ለመገነጣጠል የሚዘጋጁ የፌዴሬሽን አባላት አድርጓቸዋል በሚል፥ “ሰባባሪ” (splitting apart) ነው የሚሉትም አልታጡም።

የቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ማሪዬኬ ፍራንክ “Effects of Ethnic Federalism in Ethiopia. Holding Together or Splitting Apart?” የሚል ጥናት እ.ኤ.አ. በ2009 አሳትመዋል። በዚህም ስርዓቱ ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት እንደሚችል ጠቁመው፣ ለዚህም እንደምክንያት የዘረዘሯቸው አንደኛ ቃል የተገባው ራስን የማስተዳደር መብት እና ተግባሩ መካከል ክፍተት መኖሩን ነው። ኹለተኛ ተቋማዊ ተአማኒነትን በመገንባት ፈንታ ቤተ ዘመዳዊ ትስስር የሥልጣን መወጣጫ ዘዴ በመሆኑ የተፈጠረ ክፍተት መኖሩን ሲጠቅሱ፣ ሦስተኛ የፖለቲካ አሠራሩ ከላይ ወደታች በመጫን ላይ የተመሠረተ እንጂ የዜጎችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አለመሆኑን፣ አራተኛ ክልሎቹ በስፋት ረገድ እርስ በርስ ያልተመጣጠኑ መሆናቸውን፣ አምስተኛ የዘውግ አረዳዱ ደረቅ (static) መሆኑን እና ስድስተኛ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተአማኒነት ያለው ዐቃፊ አገር ዐቀፍ ማንነት መገንባት አለመቻሉን ነው።

ማሪዬኬ ፍራንክ በተለይ በክልሎቹ መካከል ያለውን አለመመጣጠን (asymmetry) ሲገልጹት በምሳሌ እያስረዱ ነው። “ኦሮሞዎች ለምሳሌ እንደ ብሔር መቆጠርን የበለጠ ይመርጣሉ። ሆኖም በቁጥር አነስተኛ ሕዝብ ያላቸው የዘውግ ቡድኖች በግለሰባዊ ጥበቃ የበለጠ ያምናሉ። ሁሉንም ብሔሮች እንደ እኩል መቁጠር ለአዳዲስ ኢ-ፍትሐዊነት ዕድል ይሰጣል” ይላሉ። ሕወሓትም የፌዴራል ስርዓቱን ምሥረታ በፊታውራሪነት ሲመራ ያላስተዋለው ይህንኑ ችግር ነው። አሁን ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከሁሉም የበለጡ ብዙ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው በመሆናቸው ፖለቲካው በኹለቱ በጎ ፍቃድ ብቻ እንዲዘወር አስገዳጅ ሆኗል።

ባለፉት ኹለት ዓመታት እንደተመለከትነውም ሕወሓትን በኢሕአዴግ መሠረታዊ ውሳኔዎች የዳር ተመልካች እንዲሆን ያስገደደው የኹለቱ ክልሎች ፖለቲከኞች ከተባበሩ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየርም ቢሆን ጥቂት ተጨማሪ ድምፅ ብቻ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ነው።

ፍራንክ የዛሬ ዐሥር ዓመት ገደማ በጻፉት በዚህ ጽሑፋቸው፣ ኢትዮጵያን ያስተሳስራታል የተባለው ፌዴራሊዝም ሊሰባብራት እንደሚችል ሲናገሩ የሚጎድላትን የጠቆሙት “ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች የሆነ አገር ዐቀፍ እና ዘላቂ ማንነት መገንባት አለባት” የሚለውን በማስመር ነበር። ይህም ከጆን አቤንክ ጥናት ላይ የተመሠረተ ምክር ጋር ያመሣሥለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ምንም እንኳን ከ80 በላይ የሆኑትን ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል እንዲወስኑ በሚል ዕሳቤ የተፈጠረ ቢሆንም ቅሉ፣ ከሦስት ዓመታት ተሞክሮ በኋላ አንዳንድ ብሔሮች/ብሔረሰቦች ከሌሎቹ የበለጠ ተጠቃሚ እና ላዕላይ የሚሆኑበት ስርዓት ሆኖ ወጥቷል። በዚህም ሳቢያ ብዙ ነዋሪዎች ያሏቸው ክልሎች ከሌሎቹ ክልሎች የበለጠ ተፅዕኖ ያላቸው በመሆኑ በፌዴራል አባላት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ ወይም ያልተመጣጠነ እና የአለቃ እና ምንዝር ግንኙት የመሠለ ነው። በአንድ ክልል ውስጥም ቢሆን ብዙ ሕዝብ ያላቸው ብሔሮች የሕዳጣንን መብቶቻቸውን ያለምንም ተጠያቂነት የሚረግጡበት አሠራር ተዘርግቷል።

የቡድን መብቶች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖች ለመጠበቅ የሚከበሩ እንጂ ብዙኀን አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሕዝቦች ላይ ያላቸውን የበለጠ ተጠቃሚነት የሚጨምሩበት መሆን የለበትም። ስለሆነም የብዙኀን አምባገነንነትን (majority dictatorship) ለመከላከል ያልተሞከረው መፍትሔ ቡድኖችን ሳይሆን ግለሰቦችን ማዕከል ያደረገ እና የቡድን መብቶችንም በተገቢው መጠን የሚያከብር ሕገ መንግሥታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here