‹‹የትግል ሚዲያ የሚል የሚዲያ ፈቃድ አልሰጠንም››

0
1077

በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቡር አልጌ ከምትባል ትንሽ መንደር ነው ይህን ዓለም የተቀላቀሉት። አምስት ዓመት ሲሞላቸው በመምህርነት ሙያ ላይ የነበሩት ወላጅ አባታቸው ወደ አዲስ አበባ መዛወርን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተሙ። ዕድገታቸውም በአዲስ አበባ ከተማ ቀጠለ።
የያኔው ብላቴና በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ ጌታቸው ደንቁ (ዶክተር) አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ከጌታቸው ድንቁ (ፒ ኤች ዲ) ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል።

የግል ሚዲያ እና የግል የገንዘብ ተቋማት የተመሠረቱበት ዓመት ተመሳሳይ ቢሆንም የዕድገት ደረጃቸው ለውድድር የሚቀርብ አይደለም። ሚዲያው እያደገ ያለበትን ደረጃ እንዴት ያዩታል?
ለምን የገንዘብ ተቋማት ፈጥነው አደጉ፣ ለምን የግል ሚዲያው አላደገም የሚለውን ብናየው ጥሩ ነው። ሚዲያዎቹ እንደ መንግሥት ተገዳዳሪ ሆነው ስለሚታዩ ጫና ነበረባቸው፤ አንዴ ያዝ አንዴ ለቀቅ እየተደረጉ ስለሆነ እዚህ የደረሱት። የገንዘብ ተቋማቱ በገበያ ሕግ ብቻ የሚመሩ እንጂ በፖለቲካ ጫና የሌለባቸው ናቸው። ስለዚህ ኹለቱን ማወዳደር የማይቻለው በዛ ምክንያት ነው።

እርግጥ የፖለቲካ ጫናው ብቻ አይደለም፤ ውድድሩም አለ። ቴክኖሎጂው፤ በተለይም የዲጂታል ሚዲያው መምጣት ጋር ተያይዞ መደበኛ (ሜን ስትሪም) የሚባለው የቀደመው ሚዲያ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ከባድ ጫና እና ብርቱ ፉክክር ገጥሟቸዋል። እናም ገበያቸው ድሮም አላደገም ውስን ነው፤ ነገር ግን ይሔ ዲጂታል ሚዲያ ሲመጣ ገበያ ውስጥም ተቋቁሞ ለመቀጠል የቸገራቸው ነበሩ። ከፖለቲካውም ውጪ የሕትመት ዋጋ መናር፣ ለምሳሌ ለሕትመትና ለሚድያ ሥራ የሚረዱ መሣሪያዎችን ለማስገባት ያለው ታክስ ከፍተኛ ነው።

ለብዙ ሴክተሮች የተደረገው የታክስ ማበረታቻ ለሚዲያ ዘርፍ አልተደረገም። ይህም ብዙ ዓመት ሚዲያዎች ሲያነሱት የነበረ አሁንም መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ ነው። እኛም እየጠየቅን ያለነው ጉዳይ ነው። የፖሊሲም እይታው ስለ ሚዲያው ያለው ነገር መስተካከል አለበት፤ በተለይ የግሉን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ነገር ጥሩ ነው። ተግባራዊ የሆኑ ድጋፎችን በተመለከተ ግን ገና የሚቀሩ ነገሮች አሉ።

እንደድሮው እንደጠላት አይታዩም። የግል ሚዲያ ስለዘገበ መንግሥት ይፈርሳል ብሎ የሚሰጋ አይደለም አሁን ያለው መንግሥት። የመንግሥትን የፖለቲካ መልካም ፈቃድ ጭምር ታክሎበት ነው አሁን ከፈት ያለ አየር ያለው። እና አብሮ ከዛ ጋር መታገስንም፣ ትችትን አለመፍራቱንም መቀበል እንዳለ የሚያሳይ ነገር እንዳለ የሚሳዩ ነገሮች አሉ። ያላደገባቸው ምክንያቶች በዋናነት እነዚህ ናቸው።

አሁንስ ምን እየተደረገ ነው የሚለውን ይመስለኛል በተወሰነ ደረጃ መልሼዋለሁ። ቀናነት አለ፣ መልካም ፈቃድ አለ፣ የሚዲያ ፖሊሲው እየመጣ ነው። ሚዲያ ፖሊሲው ላይ እንግዲህ ፀድቆ ሲወጣ ነው የምናውቀው። ግን አንድ የተጠቆመው ነገር ማበረታቻ የሚል ነው። እና እሱ መቼ ይሆናል የሚለውን ባላውቅም ግን ክትትል ይፈልጋል። የሚዲያው ማኅበረሰብ በራሱ ተደራጅቶ መጠየቅ ይገባዋል። መንግሥት ወዶ እና ፈቅዶ እንካችሁ ብሎ አይሰጥም።

ለምሳሌ ታክስን ብንወስድ መንግሥት ታክስ ቢሰበስብ አይጠላም፤ ደሃ አገር ነች ያለችን፤ ከሚሰበሰብ ገንዘብ ነው ብዙ መሰረተ ልማት የሚሠሩት። እና ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይ ነው። ነገር ግን ክርክሩ መሆን ያለበት፤ ከሚዲያው ማኅበረሰብና ከሌሎችም፤ ሚዲያው አንድ የልማት ዘርፍ ነው። ልማት ሲባል ኹሉንም ያቀፈ መሆን አለበት፤ የስጋ ፍለጎትን ብቻ ሳይሆን ኹለንተናን መድረስ የሚችል መሆን አለበት።

ስለዚህ ሰዎች በእሳቤያቸው ማደጋቸው፤ መብሰላቸው በዲሞክራሲም እጅግ ትልቅ ጠቃሚ ግብዓት ነው። በምክንያታዊነት እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ለባህል ማደግ ቀላል የማይባል ነው ያለው ጠቀሜታ፤ አንድ የተረጋጋ፣ ማንነቱን የሚያውቅ፣ የሚያከብር፤ በዛ ላይ ተመስርቶ ደግሞ በሰላም አብሮ ተከባብሮ የሚኖርን ማኅበረሰብ ለማፍጠር ሚድያ፣ አርት ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ከዛ አንጻር መንግሥት ሚዲያውን ቢደጉመው ሌላውን ዘርፍ እየደገፈ፣ ሌላ የልማት አቅጣጫን እየደገፈ እንጂ ካንዱ ልማት ነጥቆ ወደ ሌላ እየሰጠ እንደሆነ እንዲታሰብ አያስፈልግም።

የተለመደው እና ቀላሉ አስተሳሰብ ግን ምንድነው፤ የግል ናቸው፤ ስለዚህ በራሳቸው መሥራት አለባቸው አይነት ነገር ነው። ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥረው ግን ሁሌም መንግሥት ነው፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች አይደሉም። የፖሊሲ ተጠቃሚ ይሆናሉ ወይም አመቺ ፖሊሲ እንዲወጣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በሚዲያው ዘርፍ ነፃ ሚዲያ አለ ይባላል። ምኅዳሩን ከማስፋት አንጻር የሚዲያ ተጠያቂነቱ እስከምን ድረስ ነው? በየጊዜው የምናያቸው ሚዲያዎች ተጠያቂነታቸው በጉልህ ያለመታየት ነገር ይነሳል። በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
ነፃነትን ልንነጋገር እንችላለን። ነገር ግን ነፃ ሚዲያ አለ ወይ የሚለው ነገር ግን አከራካሪ ነው። ብዙውን ጊዜ ነጻ ከማን? ነጻ ከመንግሥት ወይም ይሄ ‹‹ኢንዲፔንደንስ›› የሚለውን ከባለቤትነት አንጻር ነው የሚያነሱት። ግን ነጻ ሚዲያ አለ ወይ ብለህ ካልከኝ የለም። አንተ የምትሠራለት ሚዲያ የሆነ የራሴ የሚለው አቋም ወይም ወገን አለው። የተነሳለትና ሊያሳካለት የሚፈልገው ነገር አለው። እንዲህ እንዲያ ሊል ይችላል እንጂ አንዳንዴ የማያምታታ እና በግልጽ የሚታይ ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ በደምብ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ነው፤ አታውቀውም። ወይም ይህን ግብ መምታት አለብኝ ብሎ ላይነሳ ይችላል።

ግን ፈተሽ ፈተሸ ስታደርግ ከባለቤትነት እሳቤ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሔዶ ሔዶ ግን ከምንም ነገር ርዕዮት ዓለም፣ አስተሳሰብ ነጻ የምትለው የለም። መጠኑ ሊለያይ ይችላል እንጂ በአንድም ሆነ በሌላ የተለያዩ ፍላጎቶች የግል ሚዲያውን ጨምሮ ሚዲያው ላይ ይንጸባረቃሉ። ስለዚህ ነጻ የሚለውን እኔ በጥንቃቄ ነው የማየው። ነጻነት ከሆነ ግን አዎ ነጻነት አልነበረም ወይም ብልጭ ድርግም ይል ነበር። ብልጭ ብሎ ረጅም ጊዜ ሳይቆይ የመጥፋት ነገር ነበረው። ነገር ግን አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥት ከመጣ በኋላ አንዱ ያሳየው ቁርጠኝነት ሚዲያውን ነጻነት መስጠት ነው።

ምኅዳሩን ማስፋት የመቻል፣ ከነችግሩም ቢሆን። እሳቸው እንዳሉት፤ እንዲያድግ እድልን መስጠት ነው። ከእነ ችግሩም ቢሆን ሲሉ ችግር ሊኖረው እንደሚችል አስበዋል። ‹‹ለምን አሰቡ?›› ብለን ስንል ታፍኖ የቆየ ብዙ ነጻነትን ያልተለማመደ፣ በነጻነት ኖሮ ተፈጥሮአዊ እድገቱን ያላደገ ስለነበረ፤ ሙያዊነት በበቂ ደረጃ አልዳበረም። ስለዚህ ሙያዊነት ባልዳበረበት እንዲህ ያለ ነጻነት በሚሰጥበት ጊዜ ያለ አግባብ መጠቀም ሊገመት የሚችል ነበር። ነገር ግን በዚህ ደረጃ ይሆናል ብሎ ያሰበ ሰው ያለ አይመስለኝም።

ከተገመተው በላይ የተስተዋሉ ችግሮች የሚጠቁሙት፤ የተገለጡት በኅብረተሰቡ ዘንድ ያሉ ስጋቶችና በሚዲያው ዘንድ ያሉት፤ በጣም የወጣ ከሙያው ሥነ ምግባር አንጻር ሲመዘኑ ሚዛን የማይደፉ ሥራዎች በሰፊው የተስተዋሉበት ስለሆነ ይመስለኛል። እርሳቸውም ከገመቱት በላይ አገርም ከነችግራቸው ብሎ ካሰበበት ደረጃ በላይ የገዘፈ ችግር ታይቷል። ኹሉም ሚዲያዎች ላይ ላይሆን ይችላል፣ መጠኑም ሊለያይ ይችላል። ወይም ደግሞ በጣም እንደዚህ ዋልታ የረገጠ አቋም ይዘው ክርር ያለ አቋም ከፖለቲካ አክቲቪዝም የማይለይ ወይም ከፕሮፖጋንዳ እጅግ የቀረበ አቋም ይዘው እሱን በተከታታይነት የሚያራምዱ ሚዲያዎች በቁጥር ብዙ አሉ።

ይጮሃሉ፤ ስለሚጮኹ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አላቸው፤ ሰዎች ይከተሏቸዋል። ምክንያቱም እንደዛ የተጋነነ መረጃን የሚያደርግን ነገር የመውደድ ነገር አለ። ኹለት አይነት አከፋፈልም አለ፤ ወይ የመንግሥት ደጋፊ ነህ ወይ ደግሞ ተቃዋሚ ነህ። ከተቃወምክ ደግሞ ደፍረህ መንግሥትን ግፋው ትላለህ፤ የዛኔ ነው ድፍረትህ የሚታየው አይነት እሳቤ ስለነበር። በዛ መስመር ላይ የመሰለፍ ነገርም ይታያል። ነገር ግን ሙያው የሚያዘው ነው ወይ ካልከኝ እንደዛ አይልም።

በዋነኛነት ኹለት ናቸው ምክንያቶቹ፤ አንዱ የሙያዊነት ማነስ ነው። በቅጡ ያላዳበርነው፣ ባህሉን ያልገነባነው፣ በቅጡ ያልተማርነው ሙያችን ነው ብለን የያዝነው ዘርፍ ነው። ኹለተኛ ደግሞ የፖለቲካ ፍላጎቶች ናቸው፤ መሬቱ ላይ ያለው ሽኩቻ ራሱን ወደ ሚዲያው ማዞሩ። የፖለቲካው ሽኩቻ ራሱን ወደ ሚዲያው አዞረ፤ አድራሻውን ወደ ሚዲያው ሲያመጣው ሚዲያው መፍቀድ አልነበረበትም፤ ‹‹ፕፌሽናል›› ሚዲያ ቢኖረን ኖሮ። ግን ፈቀደለት፤ ራሱም ፍላጎት አለው። ሙያዊነት የለም። ስለዚህ ያስተናግደዋል፤ አንዳንዴም የገንዘብ ምንጭ ይሆናል።

‹‹ጎ ፈንድ ሚ›› ላይ ይሔድና ይህን ጉዳይ ነው የማቀነቅነው፣ የዚህን የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት ነው የምነካካው፣ እኔ የእናንተ መዋጊያ መሣሪያ ነኝ ብሎ ራሱን ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር ይገልጣል። ስለዚህ በስሜታዊነት የሚቀሰቅሰው ያ ማኅበረሰብ በቀጣይ ሊረዳው የሚችለው ግልጽ በሆነ መልኩ ወገንተኝነቱን ለዛ ማኅበረሰብ እያስመሰከረ የሔደ እንደሆነ ነው። ካልሆነ የገቢ ምንጩ ይደርቃል፤ ሚዲያው መቀጠል አይችልም። በትክክል በገበያ ስርዓቱ ተመርቶ በማስታወቂያ ገቢ ላይ ተመስርቶ ነጻነቱን ጠብቆ በፖለቲካ ሳይጠመዘዙ ለመሔድ በኢኮኖሚ ጠንካራ መሆን አለበት።

አለበለዚያ የጠራውን፣ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገለትን ሁሉ ‹‹አሜን፤ እሺ›› እያለ ይቀጥላል። ከድጋፉ ጋር ደግሞ አብሮ የሚመጣ ፍላጎት አለ። እሱንም ማስተናገድ አለበት። ድሮም በካፒታሊስት አገሮች በሚዲያዎች ላይ ጫና ነበር። እኛ ጋር ደግሞ አሁን ሚድያው ላይ ጫና እየፈጠረ ያለው ፖለቲካ ነው እንጂ የገበያ እና የተጠቃሚነት ጉዳይ አይደለም።

ዘርን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ አካሔድ ወደ ሚዲያውም ገብቶ በስፋት ይታያል። ግን እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ብሮድካስት ባለሥልጣንስ ይህን መቆጣጠር የሚቻልበትን መንገድ እንዴት ነው ብሎ ያስባል?
ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ከበድም ይላል። እንግዲህ ሚዲያ ላይ የበዛ ወገንተኝትን ያመጣል የሚባለው የማንነት ፖለቲካ ነው። ሚዲያ የመጀመሪያ ወይም ጋዜጠኝነት ማንነት መሆን ሲገባው እሱን የሚያሸንፉ ሌሎች ማንነቶች ከእምነት፣ ከብሔር፣ ከአካባቢ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱ ካሸነፉት በጋዜጠኝነት ሙያ ማንነት እዛ ጋር የምታገኘው መረጃ አይነት ያንን ማንነት የሚያንፀባርቅ ነው። አንድ ትርክት ይገነባና ያንን የሚደግፍ ነገር ሁሌም ትክክል፣ ሁሌም ሽፋን የሚሰጠው ይሆናል።
ግን በተቃራኒው ያለ ነገር ደግሞ ውድቅ ይደረጋል ወይም በአሉታዊነት ተተችቶ ነው የሚቀርበው። ምክንያቱም አንድ እውነት አለው የማይነቀነቅ፣ ከብሔር ጋር የተያያዘ፣ ከእምንት ጋር የተያያዘ፤ ትክክል ነው የሚልና የዛን ወገን የሚያንጸባርቅ ነገር። ከዛ በተጻጻራሪው ያለው ነገር ደግሞ ሁሌም ትክክል አይደለም። እንዴት ታዲያ ሚዛናዊ የሆነ ሪፖርት ይጠበቃል? እዚህ ላይ በጣም ከባድ ያደረገው ነገር በግልጽ መልኩ ከማንነት ጋር ተጣብቀዋል። የመንግሥትም፣ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችም።
የመንግሥት አወቃቀራቸው ድሮውንም የክልል መንግሥታትን ተመርኩዞ ስለነበር የክልል ካቢኔዎች ፈንድ የሚያደርጓቸው፣ የሚያዟቸው፣ ኃላፊዎቻቸውን የሚሾሙላቸው የሚሽሩላቸው ሆኑ። ይሔ በአንድ በኩል ቸግር አልነበረውም፤ በቅጡ ተይዞ ቢሆን ኖሮ። የሚዲያው ወደ ኅብረተሰብ መቅረብ እኛ በጣም የምንፈልገው እና የምናበረታታው ነው። ምክንያቱም ተደራሽት አስፈላጊ ነው። የመብትም ጉዳይ ነው። ማዕከል ላይ ያሉት የተለያየ ሐሳብና ሚዲያ እያገኙ፤ ዳር አገር ያሉት አንድም ኹለትም አያግኙ ማለት ይቸግራል።

የግሉ ዘርፍ ደግሞ አያዋጣኝም በሚል አሁን እንኳን ያወጣናቸውን የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ በአምስት ከተሞች ላይ በቂ አመልካቾችን እያገኘን አይደለም። ይሔው መዝጊያው ቀን እየደረሰ ነው። ለምን ካልክ የግሉ ዘርፍ አያዋጣኝም፣ የሚዲያ ገበያ ያለው አዲስ አበባ ነው ብሎ ያስባል። ስለዚህ ማን ይድረሰው? ልክ እንደ ቴሌ እና መብራት ኀይል የሚሰጡት መከራከሪያ የተወሰነ እውነት አለው። መንግሥት ነው አሁን ሔዶ ከፍትኀዊነት አንጻር፣ ከመሰረተ ልማት አንጻር፣ ታክስ ከፋዮችም ስለሆኑ ወደ እነሱ መቅርብ ወይም የሚቀርብ ሚዲያ ማቋቋም አቅም የነበረው። እሱንም ማቋቋሙ ላይ ተቃውሞ የለኝም።

ነገር ግን እንዲቋቋም የተደረገበት ምክንያት እና ሚዲያው ራሱን የገለጸበት መንገድ ከትክክለኛው ጋዜጠኝነት የቀረበ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ አትኩሮ ሙያዊ ጋዜጠኝነትን የሚሠራ ብለህ ማሰብ አንድ ነገር ነው። ለዛ አካባቢ ማኅበረሰብ ጥቅም ብቻ የሚቆምና እሱን ፕሮፖጋንዳ የሚሠራ ብለህ ማሰብ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ስለዚህ እኔ የምደግፈው በአካባቢ እና በመልክኣ ምድር ቀረብ ብሎ ቋንቋን፣ ባህልን የሚቀርባቸውን ነገር አድርጎ ሲያበቃ ሙያዊነቱን ለመደራደር መቅረብ አልነበረበትም፤ ግን ሆነ።

ችግሩ አሁን እሱ ነው። እንዴት ይቀረፋል ለሚለው አስቸጋሪ ነው። በጣም ብዙ ቀላልና ግልጽ ምላሽ ኖሮኝ ብሰጥህ ደስ ባለኝ ነበር። እኛም እዚህ የምንጨነቅበት ሁሌም የምናስብበት እንደ አገር በብዙ ችግሮቻችን ላይ ሁሉ እንደምንነጋገር እዚህም ላይ መነጋገር አለብን። በፊት መንግሥት ይሰጣል መንግሥት ይነሳል፣ ይሄ ልክ ነው ልክ አይደለም የሚለውን ደረጃ ሁሉ መንግሥት ያወጣ ነበር። እሱን መፍራት አለብን። የመንግሥትን እጅ ቶሎ ብሎ መጥራት አደጋም አለው። ክፉ መንግሥት በመጣ ጊዜ ሚዲያውን ሊጨቁነው ይችላል። የሁሉም ኅብረተሰብ ኀላፊነት እንዲሆን መወያየት አለብን።

ይሄ ሚዲያ ይበጀናል በዚህ ይቀጥል፣ እንዴት ይስተካከል፣ ምን በጎ ነገሮች አሉ እና እነሱም ተበረታተው ይቀጥሉ፤ የሚለው ላይ ውይይት በሰፊው ማድረግ አለብን። እኛ በበኩላችን በአራት ከተሞች ላይ ያደረግነው ውይይት የሚጠቁመው፤ ኅብረተሰቡ ቁጣም ጭምር አለው፤ ሚዲያው ላይ። ይሄ መደመጥ አለበት። ለምን ቢባል ለኅብረተሰብ ዐይን፣ ጆሮ እና አንደበት ነኝ እያለ ሚዲያው እየተናገረ ሁሉም ሚዲያ በኅብረተሰብ ስም ይምላል። የኹሉንም ሚዲያ ኢዲቶሪያል ፖሊሲ ሔደህ ብታይ ለሕዝብ ምናምን የማይል ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አታገኝም።

ግን እንደተባለው ነው። አንደኛ ሕዝብ ማለት በከፊል የተወሰነውን የማኅበረሰብ ክፍል ነው ወይስ ሰፊ? ሕዝብ የተተረጎመበት መንገድ ምንድነው? እና አንደዚህ በጠባቡ የተተረጎመ ከሆነ ወገንተኛ የሆነ ሚዲያ ሊሆን ይችላል። ግን ሕዝብን ሰፋ አድርገው ካሰቡ ደግሞ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚኖር ሳይሆን ትኩረቱ በአንድ አካባቢ ላይ ቢሆንም አገርን ግን አይሸፍንም ማለት አይደለም። የብሮድካስት ሕጉ 60 በመቶ ይዘት የአካባቢ ጉዳዮች ላይ ካተኮረ 40 በመቶ ደግሞ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለበት ይላል። ሚዛን መጠበቅ ስላለበት ነው ያ መጠቆሙ።

በትክክል ይህን ስሌት ይከተሉታል ወይ ብለህ ካልክ አይደለም ነው ምላሹ። አንዱ እኛ ልናይ የጀመርነው እና ማየት ያለብን ነገር እሱ ነው። ስለዚህ ቆም እያልን በሙያዊነት ላይ መነጋገር፣ ውስጡ በሙያው ያሉ ሙያዬ ነው ብለው ይዘውት ጊዜያቸውን የሚያጠፉለት ሰዎች ከቀጣሪያቸው ባሻገር ለሙያቸው፣ ለህሊናቸው ታማኝ መሆን አለባቸው። የጋራ መግባቢያቸው ጋዜጠኝነት የሚባል ሙያ ስለሆነ ምን ይፈቅዳል፣ ምን ይከለክላል እሱን መስማማት እና የሥነ ምግባር መርሆዎችን እያወጡ በዛ መሰመር መሥራት ከጀመሩ፤ በውይይታቸውም አብሮ ሊጥሷቸው የማይገቡ ቀይ መስመሮችን ያሰምራሉ።

አብሮ የሚለውን እየደጋገምኩ ነው። በሌላ አካል መነገር የለበትም፤ ከመንግሥትም ከማንም። ከውስጥ ነው መምጣት ያለበት። ራሱ ከሚዲያ ባለቤቶች እና ባለሙያዎች፣ ከህብረተሰቡ። ከታች ወደላይ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት ደግሞ ሰምቶ ሲያበቃ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት፣ የማበረታቻ መንገዱ እየከፋፈለ መሔድ አለበት። በኃላፊነት ጋዜጠኝነትን የሚሠሩት የተሻለ ድጋፍ እና ማበረታቻ እየተደረገላቸው እና ዕውቅና እየተሰጣቸው መሔድ አለባቸው። ኹሉንም በአንድ ላይ እያስገባን መውቀጥ ተገቢ አይደለም። ከዛ ደግሞ ተለይተው ‹‹አይ! እኛ በዛው በፕሮፖጋንዳ መንገዳችን ነው የምንሔደው፤ አያገባንም›› የሚሉ ካሉ ደግሞ ትዕግስት ሊደረግላቸው አይገባም። ለጊዜው ተደርጓል፤ ግን እስከ መጨረሻው እንደዚህ ይቀጥላል ብዬ አላስብም።

ለምድን ነው የማይታሰበው? የትግል ሚዲያ የሚል የሚዲያ ፈቃድ አልሰጠንም፣ የፕሮፖጋንዳ ፈቃድ አልሰጠንም የአክቲቪዝም ፈቃድ አልሰጠንም፣ ፖለቲካ አክቲቪዝም ፈቃድ አልሰጠንም፤ ለጋዜጠኝነት ነው የሰጠነው። የጋዜጠኝነትን ሥራ እንዲሠሩ ነው የሰጠነው። በሦስት ዘርፎች በንግድ፣ በሕዝብ እና በማኅበረሰብ ሚዲያ ዘርፎች። የማህብረሰብ ሚዲያው በጣም ማህብራዊ ነገር ላይ ነው የሚያተኩሩት፤ ለኅብረተሰብም ቀረብ ያሉ ናቸው። የኅብረተሰብም የራሱ ተሳትፎ ስላለባቸው የሚገርምህ በጣም መጥፎ ይዘት፤ እንዲህ ያጋጫል፣ ያጣላል ወደ ግጭት ይሰዳል የሚባል ይዘት አላየንም።

እኛ አገር ብቻ አይደለም በሌሎች አገራትም የሚታይ ይኸው ነው። እንዲያውም በተቃራኒው ሲያስታርቁ፣ ግጭት ካለ በአካባቢያቸው እልባት እንዲያገኝ ሲያደርጉ፤ እዛ የለመዷቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የማስታረቅ ባህል፣ የሽምግልና ባህል ወደ ሚዲያ ላይ መጥቶ ያን እሴት እንዲደርሰው እና ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ እግር አውጥቶለት የተወሰኑ ሰዎች ጋር ደርሶ ችግርን እንዲያረግብ ሲጠቀሙበት ነው የምታየው። እንጂ በጣም ኃላፊነተ በጎደለው መልኩ ችግር ሲራገብበት የምንመለከተው የግል የሚባለው ሚዲያ እና የሕዝብ ሚዲያ ላይ ነው።

እኛ መቆጣጠር አለብን፤ ብሮድካስት ባለሥልጣን የተሰጠው ኃላፊነት አለ። በአዋጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥጥር እያደረግን ነው። ቁጥጥሩን በአንዴ ተነስተን እንዳናደርገው፣ በስሜት እና ተጨባጭ ባልሆነ ነገር ላይ እንዳይመሠረት፤ በፖለቲካ የተገፋፋ እንዳይሆን፤ ይልቅስ መረጃን መሰረት ያደረገ ጥናት እየሠራን ራሳቸውን እያሳየናቸው፣ እንዲታረሙ ዕድል እየሰጠን፤ ካልታረሙ ግን የሚቀጥለውን እርምጃ እንወስዳለን።

አንዳንዶች ግን ፈጽሞ የምትታገሳቸው እና ጥናት እያደረክ የማትጠብቃቸው አሉ።ይሄ ግጭትን በግልጽ የሚያነሳሳ፤ የእከሌ ብሔረሰብ ሰዎች እንትንን ይዛችሁ መውጣትና በተግባር መቃወም ነው እንጂ ያለባችሁ ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ምናምን አያስፈልግም፤ ብሎ ግጭትን በግልጽ የሚያስተጋባ፤ ይሄ የሚታገሱት አይደለም። ስለዚህ መረጃው እስኪሰበሰብ ምናምን የሚጠበቅም አይደለም። መቆም አለበት እንዲህ ያለው ጉዳይ።

ከግሉ ሚዲያ አስቀድሞ ብሮድካስት በክልሎች ያሉትን ሚዲያ የመቆጣጠር አቋም ላይ አይደለም የሚሉ ደግሞ አሉ። እውነት ብሮድካስት ባለሥልጣን ባለሥልጣን ነው ወይ የሚል ጥያቄም ያነሳሉ?
እውነት ነው ጥያቄው ይነሳል። አንድ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው በርካታ የሚዲያ ሕጎች ናቸው ያሉት። ብሮድካስት አንድ ሕግ ብቻ ነው ያለው። የብሮድካስት ሚዲያውን ዘርፍ ለመቆጣጠር የወጣ አንድ አዋጅ ነው የወጣው፤ እሱንም ለመተግበር ነው እኛ የምንተጋው። ኹሉንም ሚዲያዎች የመቆጣጠር ኃላፊነት የብሮድካስት እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ ሰው አለ። ይህ የግንዛቤ እጥረት ነው። የመረጃ ተደራሽነትም ሲመጣ፣ ወንጀል ነክ ነገሮችም ሲመጡ የብሮድካስት ብቻ ነው የሚደረጉት፤ ግን አይደለም።

የወንጀል ሕግ አለ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ አለ ብዙዎች እንዲያውም ሲከሰሱ የነበሩት እኮ የፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ተመርኩዞ እንጂ ብሮድካስት አዋጅ ላይ ተመርኩዞ የተከሰሰ ጋዜጠኛ የለም። ስለዚህ ኹሉንም በሚዲያው ዘርፍ ያሉትን አላግባብ ነገሮችን ኹሉ የምታርቅበት ብሮድካስት ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ ገና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት አለብን። ይሄ ግን ብሮድካስት ተለክቶ ከተሰጠው ኃላፊነት ለማፈግፈግ የሚጠቀምበት ምክንያት አይደለም፤ መወጣት አለበት።

የማይካደው ግን ምንድነው፤ ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ፤ እኔ እንኳን ከመጣሁ ስድስት ወር ነው። ከፈት ያለውን አየርና የፖለቲካ መንፈስ፤ የመንግሥትን መልካም መሻት ተከትሎ ይሔን ብሮድካስትም እጁን ሰብሰብ የማድረግና የመንግሥትን ፍላጎት እድል የመስጠት ነበር። ትንሽ አዘናግቶታል። ከዛ በኋላ ባልጠበቅነው ፍጥነት የብልሽቱ መጠን ጨምሯል። ለዛ ዝግጁ አልነበረም፤ ስለዚህ ቶሎ ተነስቶ ምላሽ መስጠት ያልቻለበት ምክንያት መረጃውን እየገነባ ስላልመጣ ነው።
እኔ ከመጣሁ በኋላ አሠራራችን ቀየር ለማድረግ፣ ሳይነሳዊ ለማድረግ፣ መረጃን ለመገንባትና ማንም ቢመጣ ለምንወስዳቸው እርምጃዎች እኛ ራሳችን ገለልተኛ ሆነን በተጨባጭ መረጃ የወሰድነው ነው ብለን ልናብራራ በምንችልበት መልኩ ለሚዲያዎች ልናሳይ፤ ለራሱም እርምጃ ለተወሰደበትም ‹‹የትም መሔድ ትችላለህ፤ ግን ይሔ ነበር መነሻው›› ብለን እንድናሳይ የሚያስችለንን አሠራር መፍጠር ነበረብን። ሥራው ትንሽ ጊዜ ወስዷል፤ ግን ከነሐሴ ጀምሮ ግብረ መልስ መስጠት ጀምረናል።
ዓላማችን ሚዲያዎች እንዲሻሻሉና የጀመሩትን ኅብረተሰብን በጋዜጠኝነት የማገልገልን ሥራ እንዲያሰፉት እንዲሁም ሙያዊነታቸውን እየጨመሩ ሔደው ጥሩ እንዲሆኑ ነው። እንጂ ሚዲያ አንዳንዱ እንደ መንደር ሱቅ ይመስለዋል ዝም ብለህ የምትከፍት፤ ዝም ብለህ የምትዘጋው አይደለም። የተከፈተው ሲፈቀድም የተፈቀደበት ምክንያት ለንግድ፣ ነጋዴ ገንዘብ እንዲያፈራ፣ በዛ ዘርፍ ዕድል ለመስጠት አይደለም። ኅብረተሰብን እንዲያገለግልበት ነው። ጠንካራ የሥራ ዘርፍ ነው። ባለቤትነቱ ይለያይ እንጂ የግል በለው የመንግሥት የሚያገለግለው ኅብረተሰብን ነው።

ስለዚህ ለምንድነው ብሮድካስት ቶሎ እርምጃ የማይወስደው? ያንን አገልግሎት ለሚያገኘው ኅብረተሰብ ነው የሚሳሳው እንጂ ለሚዲያው ባላቤት አይደለም። ተደራሽነት ያንሳል ብለናል። አሁን ያሉት ሚዲያዎች አገራችን ውስጥ ላለን የሕዝብ ብዛት ሲታሰብ እጅግ በጣም በዓለም ላይ ዝቅተኛ የሚዲያ ተደራሽነት ያለን አገር ነን። በተለይ ወደ ሕትመት ሚዲያው ደግሞ ሲመጣ ጭራሽ የለም ሊባል በሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ሕዝባችን ከሕትመት ቁጥር ያለው መስተጋብር ዝቅተኛ ነው። ይሕንኑ ዘርፍ እንደገና ደግሞ ተነስተህ ብታሳቅቀው እና ሳትታገሰው ቀርተህ ወደ መዝጋት ብትሔድ ሌላ የተደራሽነት ችግር ይመጣል።

ሰዎች የከፈሉለትን ዋጋ ማሰብ ያስፈልጋል። ይሄ ነፃነት እንዲመጣ ሞተዋል ሰዎች ታግለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ ተሟግተዋል፤ መንግሥትን ሞግተዋል። ስለዚህ የተገኘውን ነገር ወዲያው ደሞ ወስደው መመለስ የተወሰኑ ነገሮች ታዩ ተብሎ አይገባም። መወሰድ ያለበት እርምጃ ካለ ግን እንደነገርኩህ ደብዳቤ ይፃፋል። እውነት እልሃለሁ በቀጣይ ደብዳቤ የደረሰው ሚዲያ ካልታረመ ከሳተላይት እናግደዋለን። አይሆንም ብለን አይደለም፤ ግን በጥንቃቄ መወሰድ ያለብን እርምጃዎች ስላሉን ነው።
ደቡብ አፍሪካ በሔድን ጊዜ ‹‹በታሪካችሁ ከተቋቋማችሁ ጊዜ ጀምሮ ስንት ሚዲያ ዘግታችኋል?›› ብዬ ስጠይቃቸው አንድ ብቻ አሉኝ። እሱም የማኅበረሰብ ሬዲዮ በጣም ያልተገባ ሥነ ምግባር ታይቶበት እንጂ ሚዲያ እንዲህ በቀላሉ አይዘጋም። ከውስጣችን ስናስብ ሚዲያው ደኅንነት፣ ማደግ፣ ኅብረተሰቡ ሊያገኝ ይችል የነበረው ጥቅም እንጂ ስለዚህና ስለዚያ ሚዲያ ተቋም አይደለም።

ስለሚዲያ ነጻነት አለ ተብሎ እንደመከራከሪያነት በብዙዎች የሚነሳው የኦንላይን ሚዲያው ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በነበረው ውይይት ግን ለእነዚህ ሚዲያዎች ተገቢው ትኩረት እየተሰጠ እንዳልሆነ ታዝበናል። ኦንላይን ሚዲያውን ለመድረስ ብሎም ለመቆጣጠር በእናንተ በኩል ምን ታስቧል?
አስከ አሁን ያሉት ሕጎች እኛም የተሰጠን ብሮድካስት አዋጅም ሚዲያውን አያካትትም፤ ሚዲያ ፖሊሲም አልነበረንም። ኦንላይን ሚዲያው እንዴት እንደነበር አላውቅም። በአብዛኛው እንደስጋት ይታዩ ነበር፤ ከዛም የተነሳ ይዘጉ ነበር። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲመጡ 256 ገደማ ሳይቶች ተከፍተዋል። እናም ከባድ ስጋት ነው የነበረው፤ እንደ ጠላት ነበር የሚታዩት። ጠቀሜታ እንዳላቸው እና እንደ አማራጭ የመረጃ ምንጭ አልነበረም የሚታዩት።

ይሄ ግን ወጥነት ያለው አልነበረም። አሁን እየተረቀቀ ያለው የሚዲያ ሕግ በፖሊሲ ላይ ኦንላይን ሚዲያውም እንዴት ይታያል የሚል የሚጠቁም ነገር አለው። እሱን ተመስርቶ ሕጎች ይወጣሉ፣ ፖሊሲ ይኖራል። ፖሊሲው አቅጣጫ ያሳያል፣ ከፖሊሲው የሚቀዱ ሕጎችና መመሪያዎችም ይኖራሉ። ለምሳሌ የሳይበር ወንጀልን፣ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ፤ ፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግ ተረቅቆ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል ሒደት ላይ ነው። እሱ ሕግ ፀድቆ ሲወጣ የኦንላይ ሚዲያውን የመቆጣጠር ኀላፊነት ለአንድ አካል ይሰጠዋል። እኛ ልንሆን እንችላለን፤ ላንሆንም እንችላለን።

የተጠቆመ ነገር አለ፤ እኛም በአንድ ወይም በኹለት ቦታዎች ላይ እንደተጠቆምን አስታውሳለሁ። ገና ረቂቅ ስለሆነ ተጨርሶ እስኪታወቅ ድረስ እንዲህ ነው ማለት ይቸግራል። ነገር ግን እስከዛሬ ኦንላይን ሚዲያው እንዲሁ በደመነብስ የመደገፍ እና የመቃወም ነገር የማስፋትና የመያዝ ዓይነት ነገር ነው ያለው። በተፈጥሮ ደግሞ በቀላሉ ልትቆጣጠረው የማትችል በመሆኑ አድጓል። ያደገበት ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ በዋና ዋና ሚዲያዎች ላይ በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተሟላ መረጃ አያገኝም፣ በቂ መረጃ አያገኝም፣ በጊዜውም አያገኝም። በጣም ብዙ ነገሮች እየተከናወኑ በዋና ሚዲያ አይሸፈኑም፤ ስለዚህ ወደ ኦንላይ ሚዲያው አዘነበለ።
ጉዳቱ ግን ሁሉም ሙያዊ ሥነ ምግባር ያላቸው አይደሉም። ማንም ያንን ማድረግ በቴክኖሎጂ አቅሙ ስላለው መረጃ አገኘ አስተላለፈ። ምን ይተላለፋል፤ ምን አይተላለፍም የሚለውን ነገር እውቀቱ የላቸውም። በዛ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ጋዜጠኝነትን ሙያዬ ብለው የያዙ ላይሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ፖለቲካል አክቲቪዝም፣ ምናልባትም የማጋጨት ፍላጎት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በእርግጠኝነት ግን ወደፊት አንድ የሚበጅለት ነገር ይኖራል ብዬ አምለሁ። አንዳንድ አገራትም ኦንላይን ሚዲያውን እንዴት ነው የምንቆጣጠረው የሚለውን እያሰቡ ነው።

መንግሥት ይሄን መቆጣጠር ካልቻለ እንደምናየው ዋና ዋና ሚዲያው የሚደርሰው ሰው ትንሽ ነው። በተለይ ሕትመቱ ደግሞ እጅግ ጥቂት ነው። ስለዚህ የሚያመጣው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሰፊ ተደራሽነት ያለውን ሚዲያ ቸል ብሎ ኅብረተሰብን ከጉዳት መከላከል ይቻላል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል።
ጋዜጠኛ ማነው?
ጋዜጠኝነትን ያልተማረ ወይም በትምህርት ቤት ገብቶ ያልተማረ ጋዜጠኛ አይደለም ብትል በጣም ብዙ ሳይማሩ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች አሉ። እነሱ ያቆዩልንን ነው አሁን በቅርብ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የገቡ ጋዜጠኞች ተቀብለው እያስቀጠሉ ያሉት። አሁንም ቢሆን ጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ገብተው ያልተማሩ ግን ደግሞ ጥሩ በዘርፉ እየሠሩ ያሉ ሰዎችን እንታዘባለን።

ሊያስማማ ይችላል ብዬ የማስበው አንድ ነገር ግን አለ፤ የግድ እንኳን ትምህርት ቤት ገብቶ ባይማር በሥራ ላይ ይሁን ከሥራ በፊት መሠረታዊ የጋዜጠኝነትን መሠረታዊያን ሳይማር ግን በጋዜጠኝነት ዘርፍ ላይ መሰማራት በጣም ከባድ ነው። ያን ያክል የጠለቀ፣ ዓመታትን የሚፈጅ ዲግሪ ዲፕሎማ የሚወሰድበት እንኳን ባይሆን፤ አጫጭር የጋዜጠኝነት መሠረታዊነት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ግን ወስዶ ማለፍ ይገባል እላለሁ።

አሁን ከአክቲቪስቶቹም እንደምናው ተከታዮች ስላላቸው ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን ስለሚጽፉ፣ ስለሚናገሩ ራሳቸውን በሒደት እንደ ጋዜጠኛ የመቁጠር ነገር አላቸው። ሙያው ተቆርቋሪነት እንዲኖር፤ ሙያው እኔ ተቆርቋሪ ነኝ ሊሉት የሚችሉ ባለቤቶች ኖሮት የማናልፋቸው መስመሮች አሉ። ከዚህ በታች የማንወርድባቸው የሙያ መርሆዎች እና የሥነ ምግባር መመሪያዎች ናቸው ብሎ የሚቀበላቸውን ይፈጥራሉ፤ በውስጣቸው። ‹‹ይሔማ ሙያዬ አይፈቅድም›› የሚሉ ሰዎችን መፍጠር ካልቻልን ማንም በወደደው መልኩ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ጋዜጣ መጽሔት ላይ ሐሳቡን ሲያስተላልፍ ጋዜጠኛ ነው ብለን ከወሰድን በጣም ከተጠያቂነትም አንጻር ችግር ነው፤ ኅብረተሰብንም ያሳስታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here