ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ የስጋ ምርት መጠን በከፍተኛ መጠን ቀንሷል ተባለ

የዘንድሮው ገቢ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ27 ሚኒየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል

0
319

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምትልከው የስጋ ምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተነግሯል።

ይህ የተገለጸው በአዲስ አበባ ከትናንት ጀምሮ ለኹለት ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው ብሔራዊ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ የተሳተፉ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እንደገለጹት፤ በተለይ በስጋ፣ በሰሊጥ እና በሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

ይህ የሆነውም የመንግሥት አገልግሎት ቀርፋፋና ብልሹ በመሆኑ ነው የተባለ ሲሆን፤ ሕገወጥ ንግድ የበላይነት መያዙ ዋነኛው ማነቆ መሆኑ ተገልጿል።

አንድ ኪሎ ስጋ 400 ብር (7 ነጥብ 2 ዶላር) ተገዝቶ ለውጨ ገበያ እንደሚቀርብ የጠቀሱት ተሳታፊዎች፤ “ሦስት ዶላር ገደማ ከሚገዙ እንደ ኬንያ ካሉ አገራት ጋር በዓለም ገበያ እኩል ነው የምንወዳደረው፡፡” ብለዋል።

“ችግሩን ለመንግሥት በተደጋጋሚ ብናቀርብም መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡” ያሉም ሲሆን፤ ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ችግሩ ሳይፈታ በመቆየቱ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

የሕገወጥ ንግዱ መባባስ ለስጋ ምርት የውጭ ንግድ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በማንሳትም፤ “ኢትዮጵያ በዱባይ ያላትን የስጋ ገበያ ሙሉ በሙሉ አቁማለች፡፡” ሲሉ ጠቁመዋል።

በሰሊጥ ምርት እና ንግድ ላይ የሚሰሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ከጎረቤት አገራት አንፃር የአገር ውስጥ ምርት በውድ ዋጋ የሚገዛ በመሆኑ የውጭ ንግድ አዋጭ እየሆነ አይደለም ሲሉ አመላክተዋል።

የሲልጥ ምርት መጠን እያደገ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ የውጭ ገበያ ስርዓት የተበላሸ በመሆኑ ከዘርፉ መገኘት የሚገባው የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ አይደለም ተብሏል።

ስለሆነም አስቸኳይ መፍትሄ የማበጅ ከሆነ በስጋና በሰሊጥ ላይ ያለው ችግር በሌሎች የውጭ ንግዶች ላይም መስፋፋቱ ስለማይቀር፤ መንግሥት ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ጠንካራ ፖሊስ በማውጣትች ጭምር መስራት ይኖርበታል ነው የተባለው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡልቡላ፤ ስጋን ወደ ውጭ በመላክ ባለፈው ዓመት 114 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በዘንድሮው ዓመት 87 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፣ “የስጋ ምርት ወደፊት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርገን ዘርፍ ነው፡፡” ብለዋል።

በራሳችን ሃብት ላይ የቁጥጥር ስርዓታችን ደካማ በመሆኑም፣ ምርታችን የጎረቤት አገራት ቀለብ ነው ሲሉ ገልጸው፤ “ችግሮችን ለመፍታት በስፋት የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ ንግድ በጋራ መከላከል አለብን” ነው ያሉት።

የባንክ ብድር ወለድ ከፍተኛ መሆን፣ የመንግሥት አገልግሎት አለመዘመን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እጥረት እንዲሁም የግብር አሰባሰብ ችግር እና የመንግሥት ተቋማት አሰራር አለመናበብ ሌሎች በመድረኩ የተነሱ የወጭ ንግድ ተጠቃሽ ማነቆዎች ናቸው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here