በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የዱር እንስሳት ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው ተባለ

0
514

በደቡብ ክልል በሚገኘው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ ተብሎ በፓርኩ ይዞታ ውስጥ በሚቆፈር ቦይ የተነሳ፤ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ጨምሮ ብዙዎቹ የፓርኩ እንስሳት ወደ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሰደዳቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኑሩ ይመር በፓርኩ የተወሰነ ይዞታ ላይ ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት የስኳር ልማት ፕሮጀክት ተብሎ እየተሰራ ለሚገኝ ቦይ ተራራዎች በደማሚት በሚቆፈሩበት ወቅት በዱር እንስሳት ላይ በፈጠረው መደናገጥ፤ ዝሆንን ቀጭኔ እንዲሁም ጎሽና አውራሪስ ከፓርኩ ወጥተው ተሰደዋል ነው ያሉት።

እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ይገኝ የነበረው ዠንቢ የተባለ ከብት መሰል ዝርያ ከአካባቢው እየጠፋ መሆኑን ገልጸዋል።

ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት የስኳር ፋብሪካ በመንግሥት የሚሰራ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ያሉት ኃላፊው፣ ፋብሪካውን ለመገንባት በ2012 ከ75 እስከ 30 ሜትር ስፋት ያለውና ከሦስት እስከ 19 ሜትር ጥልቀት ያለው ከኦሞ ወንዝ ውሃ ለመጥለፍ የሚያስችል ቦይ መስራት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የዱር እንስሳቶች መዋለጃ፤ መኖሪያ እና መንቀሳቀሻ ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የዱር እንስሳቱ በፓርኩ ውስጥ ተቆፍረው ባልተደፈኑ ትልልቅ ጉድጓዶች ውስጥ እየገቡ ለሞት እየተዳረጉ ነው ብለዋል።

የስኳር ፋብሪካው የግንባታ ሥራው ካቆመ ኹለት ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰውም፣ ፋብሪካው እስካሁን አለመጠናቀቁም በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳትን ደህንነት በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

293 ሺሕ 600 ሄክታር መሬት አጠቃላይ ስፋት ያለው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ እስከ 40 በመቶ የሚደርሰው ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት የስኳር ልማት ፕሮጀክት መወሰዱ ተመላክቷል።

ስለሆነም የስኳር ልማት ፕሮጀክት እና ህገወጥ የዱር እንስሳት አደን በፓርኩ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅነዋል ነው የተባለው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here