በደቡብ ወሎ ዞን መካነሰላም ከተማ እሁድ ሐምሌ 16/2015 የከተማው ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በተፈጠረ ግጭት ኹለት ሰዎች መገደላቸውን፤ የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አረጋ አህመድ፤ “እሁድ ሐምሌ 16/2015 ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ በከተማው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የቤተክርስቲያን የጥበቃ ሠራተኛ የነበረን አንድ ሰው “የፋኖ አባል ነው” በማለት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ በከተማው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ መከላከያ ሠራዊት አባላት “የፋኖ አባል ነው” ብለው የጠረጠሩትን ግለሰብ በከተማው አቅራቢያ ወደሚገኝ የመከላከያ ካምፕ በሚወሰዱበት ወቅት፤ የከተማዋ ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ደንጋይ መወርወራቸውን ገልጸው፣ የቆሰሉ የሠራዊቱ አባላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ በተኮሱት ጥይት ኹለት ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰው፤ ከስድስት በላይ ወጣቶች ቆስለው አራቱ ወደ ባህርዳር ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፋኖ ታጣቂዎች በቦረና ሳይት ብሔራዊ ፓርክ መሽገው እንደሚገኙና በነዋሪዎች ዘንድ ሌላ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ያነሱት ቡድን መሪው፤ አሁን ላይ ግን አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ወሎ ዞን በወገዲ ወረዳ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተኩስ ተከፈቶ እንደነበር ገልጸው፤ በዚያም አንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ አግሪት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሰኞ ሐምሌ 17/2015 ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ወጊያ ሲካሄድ ማደሩንና ስድስት የሚሊሻ አባላት መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ከተደረገው ውጊያ በኋላ በወረዳው እና አካባቢው በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸው ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል “መንግሥት በኃይል ለማውረድ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች አሉ” በሚል፤ የፌደራል መንግሥቱ እና የክልሉ አስተዳደር ለወራት የዘለቀ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛል።



