በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ለመልሶ ማልማት ፕሮጀክት 60 ሚሊዮን ዶላር በጀት ጸደቀ

0
648

የኢትዮጵያ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አቢይ ኮሚቴ፤ ለ2016 የበጀት ዓመት በግጭት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለመልሶ ማቋቋመምና ግንባታ ተግባር የሚውል የ60 ሚሊዮን ዶላር በጀት አጸደቀ፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው የአብይ ኮሚቴው ስብሰባ፤ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ በፕሮጀክቱ ማስተባበሪያና ማስፈጸሚያ ጽ/ቤቶች ሀላፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በውይይቱ በ2015 የበጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ ሥራ አፈጻጸም መሰረት የሚጥሉ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን የማደራጀት፣ ባለሙያዎችን የማሟላት፣ በማህበረሰብ ደረጃ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ አደረጃጀቶችን ማቋቋምና የማጠናከር፣ ለፕሮጀክቱ ባለሙያዎች በፕሮጀክቱ የፋይናንስ፣ የግዥ፣ የአካባቢያዊና የማህበራዊ ደህንነት መርሆችና አሰራሮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሂደት ለኅብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ሥራዎችን በሚጠበቀው ፍጥነት ለማከናወን የዝግጅት ሥራዎቹ ጊዜ በመውሰዳቸው በተጠቃሚው ኅብረተሰብ እና በፕሮጀክቱ ባለድርሻ አካላት የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውም በውይይቱ ተዳሷል፡፡

በቀጣይ የ2016 በጀት ዓመት ኹሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለኅብረተሰቡ መቅረብ ያለባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች ተግባራዊ ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፤ የታቀዱ ተግባራትን ለማከናወንም የ60 ሚሊዮን ዶላር በጀት በፕሮጀክቱ አብይ ኮሚቴ አባላት ጸድቋል፡፡

የአብይ ኮሚቴውን ስብሰባ የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰውና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሙት ሲሆኑ፤ በስብሰባው የአብይ ኮሚቴው አባላት የሆኑት የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማለትም የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና የአደጋ ስጋትና ዝግጁነት ተቋም ተወካዮች እንዲሁም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑት አምስት ክልሎች የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝና የትግራይ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግሥትና በአለም ባንክ መካከል በተደረገ ስምምነት እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ በ300 ሚሊዮን ዶላር በጀት ለአምስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት መሆኑ ተነግሯል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here