ግባቸውን ያልመቱት ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በአዲስ እይታ

0
1558

የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት አደረጃጀት ፖሊሲ ለበርካታ ዓመታት ሲሠራበት ቆይቷል። ለወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር ዓላማ ያለው ይኸው አሠራር፤ ሥያሜውም በብዙዎች አእምሮ ታትሞ ቀርቷል። ይሁንና የታሰበለትን ያህል ስኬት አላመጣም ብለው የሚሟገቱ አሉ። ከዘርፉ ባለሙያዎች ባሻገር በአደረጃጀቱ ውስጥ ሥራ ለማግኘት ሞክረው ያልተሳካላቸው እንዲሁም የተሳካላቸው በዚህ ላይ የተለያየ አስተያየት ይሰጣሉ። በዚህና እንደ አዲስ እየተሠራበት ባለው የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ባለሙያዎችንና በተቋማቱ አደረጃጀት ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶችን በማነጋገር፣ እንዲሁም ዘገባዎችን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳው በለጠ ሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በአዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ወጣት ብርሃኑ በቀለ ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር ከእንጦጦ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በብረታ ብረት ትምህርት የተመረቀው። አብረውት ከተመረቁ አራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን አንድ ለአምስት በተባለው አደረጃጀት በመደራጀት በሚኖሩበት የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት በመሔድ ተምረው በተመረቁበት የብረታ ብረት ሙያ ለመደራጀት ሐሳባቸውን ያቀርባሉ። ወረዳውም ለመደራጀት መነሻ ገንዘብ እንዲያዘጋጁ ከዚያም የብድር ድጋፍ እና ተያያዥ እገዛዎችን እንደሚያደርግላቸው ቃል ገባላቸው። አንደወጣቱ ገለጻም በተገባላቸው ቃል መሠረት 50 ሺሕ ብር በማጠራቀም እና ለሦስት ወራት ያህል ባደረጉት ደጅ ጥናት 250 ሺሕ ብር ብድር መነሻ ወረት ቀርቦላቸዋል።

በግንባታ ግብአት ማምረቻ ዘርፍ በመሰማራት በመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ዳስ በመሥራት ወደ ሥራ ገቡ። ሆኖም ሠርቶ የመኖር እና የመለወጥ ህልማቸውን ለማሳካት የጀመሩት ጉዞ ከአንድ ዓመት በላይ መጓዝ አለመቻሉን ለአዲስ ማለዳ የገለፀው ብርሃኑ በቁጭት ነበር።

‹‹ወደ ሥራ ስንገባ ክፍለ ከተማው የምናመርታቸውን ምርቶች የሚገዙን ግንባታ ተቋራጮች ጋር እንደሚያገናኘን ቃል ገብቶልን ነበር›› ሲል ብርሃኑ ስላጋጠማቸው መሰናክል ያስረዳል። ‹‹ሆኖም ምርት ብንጀምርም ገዢ ጠፋ፤ የተገባልን የገንዘብ መጠን፣ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የገበያ ትስስር እና መሰል ጉዳዮች ባለመፈፀማቸው ለሥራው የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን እንኳን በአግባቡ መግዛት ተስኖን በ 2011 የሥራ መሣሪያዎቻችንን ሸጠን ያለንን ብር ተካፍለን ተበታትንናል›› ሲል ይናገራል።
በወቅቱም ለወረዳ እንዲሁም ለክፍለ ከተማ አመራሮች በተደጋጋሚ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም ችግሩን የሚፈታ ይቅርና በአግባቡ የሚያዳምጥ ሰው ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻል።

እንደ ብርሃኑ እና ጓደኞቹ ያሉ እስከ ኹለት ሚሊዮን የሚደርሱ ወጣቶች በኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ ሠራተኛው የሕዝብ ቁጥር ይገባሉ። በተጨማሪም በከተሞች ያለው የሕዝብ ቁጥር በዓመት አምስት በመቶ በመጨመር ከ20 ዓመት በኋላ አሁን ካለበት በሦስት እጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል።

ይህም ለሚታየው ከፍተኛ የሥራ ማጣት እንደምክንያት ከመነሳቱም በላይ በየ ዓመቱ አምስት በመቶ የሚያድገው የከተማ ነዋሪ ቁጥር፤ ከ 20 ዓመታት በኋላ አሁን ካለበት በሦስት እጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል። ይህም የሥራ እድል እና ፈጠራን ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ 756 ሺሕ ስድሰት መቶ ሥራ ፈላጊዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ለአንድ ሚሊዮን የቀረበ ሥራ ፈላጊ መመዝገብ ተችሏል።

ከእነዚህ መካከልም 60 ሺሕ አምስት መቶ የሚሆኑት በመረጡት የአደረጃጀት ዓይነት 18 ሺሕ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ቁጥር አሁን ከሚታየው ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ ከሚደረገው ፍልሰትና ከሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ ጋር ተያይዞ ከሚጨምረው የሥራ ፈላጊ ቁጥር ጋር ተዳምሮ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የሚፈጥሩት የሥራ እድል አመርቂ እንዳይሆን አድርጎታል።

‹‹በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች በመንግሥት የተፈጠረላቸውን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሥራዎችን ያማርጣሉ›› የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ታደለ ይገልፃሉ።

መንግሥት ባለው አቅም ሁሉ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ቢሉም፣ እስከ አሁን የተመሠረቱት ኢንተርፕራይዞችን በውል መዝግቦ ምን ያህሉ በውጤታማነት እየሠራ እንደሆነ እንዲሁም ምን ያህሉ ከሥራ ውጪ እንደሆነ እንደማይታወቅ ይገልፃሉ። የተንዛዛ አሰራር ባላቸው ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች ወጣቶቹን በማሰላቸት ከጅምሩ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጉ እንዲሁም ከተደራጁ በኋላም አስፈላጊ እርዳታ ያለማድረጋቸው ፈተና መሆኑንም ኀላፊው ይገልጻሉ።
የሚደራጁት ወጣቶችም ሁሉንም ድጋፍ ከመንግሥት መጠበቃቸው ስኬታማ እንዳይሆኑ አድርጓል ሲሉ ጥላሁን ይሞግታሉ። ‹‹የገበያ ትስስር፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የቴክኒክ ድጋፍ እና የሂሳብ አያያዝ ሥልጠናዎችን ሁሉ መንግሥት እንዲያቀርብላቸው ይፈልጋሉ›› እንደ ጥላሁን ገለጻ። ይህም የግል ጥረታቸውን ወደ ኋላ በመጎተት ከመንግሥት ጠባቂ እንዲሆኑ ያደረገ ነው ይላሉ።

ታዲያ በየ ዓመቱ የሚፈጠረው ሥራ ፈላጊ -ቁጥር ከኹለት ሚሊዮን በላይ ከሆነ አሁን በከተሞች ያለው የሥራ አጥ ቁጥር 19 በመቶ ለመድረሱ በተለይም በተለያዩ ዓመታት ሲጠራቀም የመጣው የሥራ አጥ ቁጥር እንደምክንያት ይነሳል።

ለ 20 ዓመታት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማማከር ሥራ ላይ የቆዩት እና በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ እጩ ምሩቅ የሆኑት አሚን አብደላ እንደሚሉት፣ የተመሠረቱት ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ሲመሰረቱ ከታሰበላቸው የአምራችነት ሚና ይልቅ በንግድ እና በአገልግሎት ሰጪነት ላይ መሰማራታቸው በዘርፉ የታሰበው ስኬት እንዳይኝ አድርጓል። አንቀሳቃሾቹም ሲመሠረቱ አባላቶቻቸው የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ሌሎችን መቅጠር እና እንደታሰበውም እዳቸውን ከፍለው መቀጠል ያልቻሉ እንዲሆኑ አድርጓል።

ለአንቀሳቃሾች የሚሰጠው የመነሻ ገንዘብ አነስተኛ መሆን፣ እያደገ የሚሔድ የገበያ ትስስር አለመፈጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ስደት በዋነኝነት መንስኤ መሆኑን አሚን ይስማሙበታል። በተጨማሪም ወጣቶቹ የሚሰማሩባቸው ዘርፎች ሌሎች ልምድ ያካበቱና አትራፊ ነጋዴዎች ተሰማርተው የሚገኙበት በመሆኑ፣ በገበያው ላይ ተፎካካሪ በመሆን ለመቆየት እንዲቸገሩ አድርጓል ይላሉ።

ግብ ያልመቱት ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት እና አዲሱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ
በኢትዮጵያ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በየ ዓመቱ ወደ ሥራ ፈላጊው የእድሜ ክልል ይቀላቀላሉ። በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታትም አጠቃላይ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ከ 90 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ይገመታል። ይህንን ከፍተኛ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ለማስተናግድ በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች በቂ ባለመሆናቸው፣ ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው መሥራት እንዲችሉ ከ 20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት አደረጃጀት ፖሊሲን በማውጣት ሲሠራበት ቆይቷል።

እነዚህ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የወጣቶችን ገቢ ለማሻሻልና ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም ፍትኀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር ለማድረግ ታስበዋል። እንዲሁም ተወዳዳሪና ቀጣይነት ያለው ፈጣን ልማት የሚያስመዘግብ፣ የገጠር ልማትን ለማስቀጠልና ለኢንዱስትሪው ልማት አስተማማኝ መሠረት የሚጥል ዘርፍ እንዲሆን ለማስቻል አልፎም በከተሞች ሰፊ መሠረት ያለው ልማታዊ ባለሀብት በመፍጠር የዘርፉን ልማት ማስፋፋት የሚሉ ዐበይት ዓላማዎችን ይዘው ላለፉት በርካታ ዓመታት እየተውተረተሩ ይገኛሉ።

ከዚህ ባሻገርም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከአጭር ጊዜ ካፒታልን ቆጥቦ ፈጣን ልማት በማረጋገጥ ከልማቱ ሕዝቡ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። በመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ ልማታዊ ባለሀብት የሚፈራባቸው ምንጮች ሆነው ከማገልገላቸው ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ባላት ውስን ካፒታልና ቴክኖሎጂ በመጀመር በሒደት የካፒታልና ቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር በማያቋረጥ የፈጣን እድገት ዑደት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ይሆናል የሚል ትልቅ ግብ የያዙም ናቸው።

በተጨማሪም በሀገራችን ያለውን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍና የወደፊት ኢንዱስትሪዎችን በመፈልፈልና በከተሞች ጠናካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ወሳኝ ድርሻ የሚጫወተው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበት፤ ትኩረት ተሰጥቶት ቆይቷል::
በመሆኑም መንግሥት በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት መስክ ቅድሚያ የሚሰጠው ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ልማት ይሆናል በሚል የወጣቱን የሥራ ክህሎትና የሥራ ፈጣሪነት አመለካከት በማጎልበት፣ የቁጠባ ባህሉን በማሻሻል ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋሞች የሚመረቁ ወጣቶች በዘርፉ በሰፊው እንዲሰማሩ ተደርጓል ሲል ይገልጻል።

እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካትም መንግሥት ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የሰው ኃይል ልማትና የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያረጋግጥ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በባለቤትነት በመስጠት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በኢንዱስትሩ ልማት ስትራቴጂ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሥልጠናዎችን መስጠት የሚል ሃላፊነትም ተጥሎበታል። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ዘርፉ ከግብርና፣ ከመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ጋር ተመጋግቦ እንዲያድግ መሰል ድጋፎችን በማድረግ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በስፋት ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የተቀመጡ የሥራ ድርሻዎችን ያሳያሉ።

የዘርፉ ፈተናዎች – ከወጣቶቹ አንደበት
‹‹ማኅበሩን ስናቋቋም በርካታ ዕቅዶች እና ተስፋ ይዘን ነበር›› ይላል ብርሃኑ። በተለይም ወደ ቀጣዩ መካከለኛ ብረታ ብረት እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማደግ እና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሕይወታችንን ለመቀየር የነበረን ዓላማ ከግብ ሳይደርስ በአጭሩ ቀርቷል ሲል ያስታውሳል።
‹‹ከወረዳው ያገኛችሁትን ብድርስ መለሳችው ወይ?›› ስትል አዲ ማለዳ ላቀረበችለት ጥያቄ፤ ሲመልስ ‹‹በሥራ ላይ እያለን በየወሩ እንከፍል ነበር። ግን ግማሽ ያህሉን እንኳን የመለስን አይመስለኝም›› አለን። በቀጣይስ? ብርሃኑ እንዳለው፤ ‹‹ማኅበሩ ፈርሷል ወረዳው እና ክፍለ ከተማው አልፎ አልፎ ስልክ እየደወሉ ይጠይቁናል ከዚህ በኋላ ግንኅመክፈል አቅሙ የለንም። ሁላችንም በግል ሥራ ላይ ነው ያለነው።›› ብሏል።

ችግሩ ወደ ሥራው የገቡት ላይ ብቻ የሚስተዋል አይደለም። እንዳልካቸው ዘውዱ የተባለ አንድ ወጣት በተመሳሳይ ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር የዶሮ እረባታ ለመክፈት እንቅስቃሴ ከጀመሩ አራት ወረት ተቆጥረዋል። ሥልጠና ወስደው የሥራ እቅዳቸውን አስገብተው፤ ብደር ለማግኘት በጠየቁበት ወቅት ቦታ ራሳቸው ማዘጋጀት እንዳለባቸው ይነገራቸዋል። የቤት ካርታ ያለው አከራይ ማግኘት ባለመቻላቸው ወረዳውን ቦታ ቢጠይቁም ወረዳው ወደ ክፍለ ከተማው ክፍለ ከተማው ወደ ወረዳው እየጠቆሙ ቦታ ማግኘት ተስኗቸዋል።

እንደ እንዳልካቸው ገለፃ፣ በራሳቸው ብር ከፍለው እንዳይከራዩ ገና አዲስ ተመራቂዎች በመሆናቸው ለአራት እና አምስት ወራት የሚደርስ የቤት ኪራይ ክፍያን መፈፀም አልቻልንም፤ እናም የመሥራት ተስፋችን እና እቅዳችን በመሟጠጥ ላይ ይገኛል እንዳልካቸው ይገልጻል።

የሚመላለሱባቸው ምክንያቶች የመሥሪያ ቦታ ጥያቄ እና የመነሻ ገንዘብ ጉዳይ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል አቅርበን ምንም አይነት እርዳታ እና ትኩረት ማግኘት አልቻለንም ሲል ይገልጻል።

ደካማና ጠንካራ ጎኖች ምን ነበሩ?
ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በሚፈለገው ልክ ለማስፋፋት የገንዘብ እጥረት እንደ ዋነኛ ምክንያት ተጠቅሷል። በተጨማሪም ‹‹ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትን ባሉበት ሁኔታ መዝግቦ ለመያዝ እና በቂ ክትልል ለማድረግ የሚያስችል አቅም አልተገነባም›› ሲሉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አሸናፊ መለሰ ይገልፃሉ። ለዚህም የመንግሥት አካላት ሳይቀሩ ዓላማውን አለመገንዘባቸው እንዲሁም በየጊዜው መቀየያራቸው ሥራው ሁሌ እንደ አዲስ እንዲጀመር ምክንያት ሆነዋል ባይ ናቸው።

ከክልሎች እና ከከተሞች የሚመጣው መረጃ በየጊዜው የሚለዋወጥ መሆኑ ምን ያህል ኢንተርራይዞች ተመሥርተው እንደ ከሰሙ፣ ምን ያህሉስ በስኬት ላይ እንደሚገኙ እና ወደ ቀጣይ ደረጃ እንደተሸጋገሩ ለማወቅ እንዳይቻል አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራ አና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ከ 2003 ጀምሮ እስከ 2007 ባሉት አራት ዓመታት ከዐስር ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠር መቻሉን ያመላክታል። ባለፉት ኹለት ዓመታት ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ይገልጻል። የሥራ እድሎቹም በአምራች ዘርፍ፣ በግንባታ፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት እና በንግድ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል።

ከሥራ እድል ፈጠራው በተጨማሪ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋመቱን ከቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ጋር በማገናኘት ሥራዎችን በእውቀት እና በሥልጠና ላይ መሠረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።

የከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ ከተማ አስተዳደሩ በ 2008 ከደረሰው አራት ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ባለፉት ኹለታ ዓመታት በማሰራጨት ወለዱን ጨምሮ አምስት ሚሊዮን ብር መለሶ መስጠቱን ያመላክታል።

አሚን በበኩላቸው፤ ወጣቶች ሥራ ጠባቂ ብቻ እንዳይሆኑ እና በራሳቸው ጥረት ሥራ መፍጠር እንዲለማመዱ በማድረግ የፀባይ ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ ረድቷቸዋል ይላሉ። ከእነዚህ ስኬቶች በተጨማሪ ስኬታማነቱ ላይ ክፍተት ቢኖርበትም ኢንዱስትሪዎችን እና አምራቾችን ለመፍጠር የተደረገው ጥረት በወጣቶች ዘንድ ‹‹ሠርቶ መለወጥም ይቻላል!›› የሚል አመለካከት እንዲፈጠር አድረጓል ሲሉ መልካም ጎኖቹን ያነሳሉ።

የሴቶች ተሳትፎ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ
የከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ሴቶችን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ይገልፃል። ለአብነትም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሰጥ ከነበረው 1.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ለሴቶች እንደተሰጠ ያመላክታል። ሴቶችን በይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግም ለፈንዱ ተጠቃሚነት ከተወሰነው ከ18 ዓመት እስከ 34 ዓመት እድሜ ገደብ በማንሳት በርካታ እናቶች ተደራጅተው ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ እንደተቻለ የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ውስጥም የወጣቶች ድርሻ 70 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል።

ከ 2009 ጀምሮ በፌዴራል ደረጃ ሲሰራጭ ከነበረው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ላይም እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሴቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ የወንዶች ቁጥር ከዚህ በእጥፍ ከፍ ያለ መሆኑን የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የተዘዋዋሪ ፈንዱ ውጤትስ?
መንግስት ላለፉት አስር ዓመታት ወጣቶችን በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሰሴ ውስጥ በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ቀርጾ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተለይ በ1998 ዓ/ም ተቀርጾ ተግባረዊ ሲደረግ የቆየው የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ወጣቶች ሥራ ፈጥረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አስችሏል። ይሁን እንጂ፤ ይህ ፓኬጅ እያደረ በሚፈለገው ልክ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም።

ከኹለት ዓመታት በፊት በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአቀረቡት ንግግራቸው በቀጣይ ይህን የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ችግር ለመፍታት በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ አንስተው በዚህ መሰረት፤ የወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ገልፀው ነበር፡፡

ተሻሽሎ የተዘጋጀው የወጣቶች የልማትና የእድገት ፓኬጅ በየጊዜው የሚነሱትን የወጣቶች ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ የተቀረፀ ነው የተባለለት ይህ ፓኬጅ መንግስት ከድጋፍ ሚናው ባሻገር የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል አደረጃጀት እንደሚያቋቁምም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በስራ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ቢያንስ አምስት ሆነው በመደራጀት በየአካባቢያቸው ባሉ አዋጭ የሥራ መስኮች እንዲሰሩ ያደረጋል።

ከዚህ በተጓዳኝ በወቅቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ አጽድቋል። ፈንዱም በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ እስከ ሶስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠርን አላማው ያደረገ ነበር፡፡

ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ የማምረት አቅም ተጠቅመው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ይችላሉ። ለዚህም ተደራጅተው ለሚያካሒዱት የገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት በ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወሳል።

ከፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከ18 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ሲሆኑ፣ ወጣቶቹ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ መደራጀት ይጠበቅባቸዋል። የንብረት ዋስትና ማቅረብ ሳያስፈልግ እርስ በእርስ ዋስ በመሆን መበደር እና ገንዘቡን በሥራ ላይ ማዋል እንዲችሉ እንደሚረዳ ታምኖበት ነበር።

ፈንዱን በፌዴራል መንግሥት ሥም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስተዳድረው ሲሆን፤ ለወጣቶች ብድር ማቅረብ የሚችሉት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው። አነስተኛ የፋይናስ ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድሩን የሚያቀርብ እንደሚሆንም ንግድ ባንኩ ተዘዋዋሪ ፈንዱን ለማስተዳደር ከኹለት ዓመታት በፊት ባወጣው መመሪያ ላይ ላይ ተገልጿል።

የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ ከ 2008 ጀምሮ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ በፌደራል ደረጃ ከተመደበው 10 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰራጨቱን ያሳያል። ከዚህም ውስጥ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ክልል እና አማራ ክልል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ያሳያል።

በዚህም መሰረት ኦሮሚያ (3.4 ቢሊዩን ብር)፣ አማራ (2.6 ቢሊዮን ብር) እና ደቡብ (1.8 ቢሊዮን ብር) ከክልሎች የብድሩ ከፍተኛ ተጠቃሚ በመሆን ቀዳሚ ናቸው። አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ መስተዳድሮች 418.8 ሚሊዮን ብር እና 43.9 ሚሊዮን ብር ከፌዴራል መንግሥት ወስደዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ተዘዋዋሪ ፈንዱን በሚመለከት ባወጣው ኦዲት ሪፖርት የየክልሉን ወጣቶች ቁጥር መሠረት በማድረግ ከፈንዱ ገንዘብ ላይ ለየክልሉ መከፋፈል የሚገባውን ድርሻ በማስላት በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተሟላ መልኩ ማሳወቅ ይገባው ነበር። ነገር ግን ከ10 ቢሊዮን ብር ውስጥ 5 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው ባንኩ እንዲያውቀው የተደረገው። ሙሉ በሙሉ የክልሎች ድርሻ የማሳወቅ ሥራ ሳይሠራ ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ የፈንድ ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና ወጪ ተደርጎ ለተጠቃሚዎች እንዲሰጥ መደረጉን ኦዲት ሪፖርቱ ያመላክታል።

የተሰራጨው ተዘዋዋሪ ፈንድ አመላለሱ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት እና እንደ ብደር ሳይሆን እንደ ስጦታ እየተቆጠረ በአመላለሱ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለበት እንደሆነ ገልጿል። ለአብነት እስከ ባለፈው በጀት ዓመት ድረስ ብቻ የተመለሰው ብር ከ 560 ሚሊዮን አይበልጥም።

ይህ 10 ቢሊዮን ብር በአግባቡ መመለሱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወጣቶች ከተመደበው 2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት 1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ተከፋፍሏል። ይህንን ብድር የወሰዱ ወጣቶች በማስያዣነት ምንም ካለማቅረባቸውም በላይ ቡድንን እንደዋስትና በመቁጠር እንዲከፋፈል ተደርጓል።

ብድሩን 7 ሺሕ በሚሆኑ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ የተደራጁ ከ 21 ሺሕ በላይ ወጣቶች የወሰዱ ሲሆን፣ በኮንስትራክሽን አገልግሎት አምራች እና መሰል ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው። እንደየ ተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ አዋጭነት እና በአጭር ጊዜ ትርፍ የማስገኛት አቅም ከአንድ ወር ጀምሮ እስከ አራት ወራት የሚደርስ የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

ለዚህም የከተማ ሥራ እድል ፈጣራ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጥላሁን፣ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ለመነሻ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት እንደሚቸገሩ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ወይይቶች ለመረዳት ችለናል ይላሉ። ከዚህ ቀደም እስከ ዐስር በመቶ የሚደርስ ቁጠባ እንዲቆጥቡ ይደረግ የነበረውንም በመቀነስ እስከ አምስት በመቶ እንዲወርድ አድረገናል ሲሉ ያክላሉ።

የመመለስ አዝማሚያውን በተመለከተ፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ እና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ እንዲሁም በዘርፉ የሚታየውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ቡድንን ዋስትና በሚያደርግ መንገድ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። አመላለሱም በመተማመን ላይ የተመሰረተ እና ልምድ ሊገኝበት የሚችል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አሚን አብደላ በበኩላቸው፣ ተዘዋዋሪ ፈንዱ ሲሰጥ የነበረበት መንገድ ክፍተት ያለበት ነው ይላሉ። ያለ በቂ ጥናት ባልተደራጀ የሥራ እቅድ የተሰጠ በመሆኑ ወጣቶች የገቢ ማግኛ መንገድ አድረገው እንዲወስዱት ምክንያት ሆኗል የሚል ሐሳብን ያነሳሉ።

በቀጣይ የታሰበው የስራ ዕድል ፈጣራ ዕቅድ
የኢትዮጵያ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ 14 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በዚህ እቅድ መሰረትም የሥራ እድል የመፍጠር አቅም አላቸው ተብለው የታሰቡ የኢኮኖሚ ክፍሎችን እና ፖሊሲዎችን እንዲሁም የገንዘብ ስርዓቱን በማስተካከል በሀገር ውስጥ የተመሰረቱ እና የማደግ ተስፋ አላቸው ተብለው የሚገመቱ የግል እና ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የተሻለ የሥራ ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ማገዝ የሚሉ ሐሳቦችን ይዟል።

ከዚህ በተጨማሪም ከትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ ወጣቶች ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የሙያ ደረጃቸውን ማሻሻል እና ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃ መቅረፅ የሥራ ፈጣሪነትን አስተሳሰብ በወጣቶች ላይ መፍጠር፣ በትምህርት እና በሥልጣና ተቋማት እና በማምረቻዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናክር የሚሉ ዐበይት ዝርዝር ጉዳዮች አሉት።

እምብዛም ትኩረት ያልተሰጣቸውን መረጃ ማግኛ ቴክኖሎጂዎች፣ ቱሪዝም እንዲሁም ሥነ ጥበብን በመጠቀም በቀጣይ አምስት ዓመታት 14 ሚሊዮን፤ በዐስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል።

በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳድሮች የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸውን ዜጎች ቁጥር አስቀምጧል። በኦሮሚያ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ በአማራ 716 ሺሕ 123 ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች 604 ሺሕ 449፣ በትግራይ 212 ሺሕ 796፣ በአፋር 52 ሺሕ 075፣ በሶማሌ 121 ሺሕ 685፣ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ 31 ሺሕ 065፣ በጋምቤላ 12 ሺሕ 637፣ በሐረር 9ሺሕ 756 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 214 ሺሕ 738 ዜጎች፣ በድሬዳዋ ደግሞ 19 ሺሕ 864 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ታውቋል።

የሥራ እድል ፈጠራውና ጠጠሮቹ?
በአሁኑ ሰዓት አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ለሀገር አቀፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ተፈጻሚነት የሚያስፈልገውን ሀብት ለመለገስ/ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ላይ እንደሚገኙ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል። ይህም ጋንን በጠጠር እንደመደገፍ ለሥራ እድል ፈጠራው አቅም እንደሚሆን ይጠበቃል።
በዚህም መሰረት ቃል የገቡ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን DFID የተባለ የእንግሊዝ ለጋሽ ድርጅት፣ የኔዘር ላንድ ኤምባሲ፣ ዓለም ዐቀፍ የሠራተኞች ድርጅት /ILO/ ከዩኤስ ኤ አይ ዲ / USAID/ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅት፣ ቢግ ዊን ፍላንትሮፒ የተባለ ዓለማቀፍ ለጋሽ ድርጅት ለወጣቶች ሥራ እድል ለመፍጠር እና በወጣቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። ይህን ተከትሎ በቀጣይ 10 ዓመታት 20 ሚሊዮን የሥራ እድል ለወጣቶች ለመፍጠር እንሚሠራም ተያይዞ ተገልጿል።

ከነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥም ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለዚሁ ዓላማ የሚውል 300 ሚሊየን ዶላር በጀት መመደቡን አስታውቋል። ይህንንም ገንዘብ በተለይም በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ፈጠራ በታከለበት መልኩ የተሻለ ምርታማነትን እንዲያስመዘግቡ በማገዝ ላይ የሚያተኩር ነው። ኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ታሳይ ዘንድ ፖሊሲ እና ደንቦችን ለማሻሻል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴም ለዚሁ ሥራ በማስተር ካርድ እንድትመረጥ ማስቻሉም ተመላክቷል።

በቀጣይ ምን መደረግ አለበት?
እንደ የኢኮኖሚ አማካሪው አሚን አስተያየት፣ በሀገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስም ይሁን ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ ኢኮኖሚው ላይ መሠረታዊ ሥራ መሠራት አለበት። ኢኮኖሚው ወደ ማምረት እና ኢንዱስትሪው በስፋት ግብቶ ብዙ ሰዎችን መቅጠር የሚችሉ ትላልቅ ተቋማትን መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ፣ አሁን በከተሞች በሚስተዋለው አገልግሎት እና ንግድ ብቻ እያደገ፤ የሚመጣውን የሥራ ፍላጎት ሟሟላት ከባድ ነው። ‹ሁሉም ነጋዴ ሆኖ ማን ሊገዛ ነው› የሚል ሐሳብን ያነሳሉ።

መንግሥት ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትን ሲመሠረትም ጥልቅ የገበያ ጥናት እንዲያደርጉ ማበረታታት፣ አካባቢያቸውን እና ገበያው የሚፈለገውን ምርት እንዲለዩ የሚያደርጉ ሥልጠናዎችን መስጠት ይኖርበታል። ከዚህም በላይ ገንዘብ በእጃቸው ከመስጠት ይልቅ የመሥሪያ መሣሪያዎችን እና ቁሳቁሶችን ቢያቀርብላቸው እና ጥራት ባለው ምርት ከዓለም ሠቀፉ ገበያ ጋር እንዲፎካከሩ ቢያደርጋቸው የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ሲሉም ምክረ ሐሳባቸው ያቀብላሉ።

በሌላ መልኩ መንግሥት ብዙ ሰው የመቅጠር አቅም ባላቸው እንደ ጨርቃጨርቅ፣ ማዕድን እና ብረታ ብረት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከመሥራት በላይ በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የተሻለ ገቢን ለማግኘት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ያክላሉ። በተጨማሪም ሥራ ለሚፈጥሩ ወጣቶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ ወደ ሥራ ለመግባት ሲነሱም ይሁን በሥራ ላይ እያሉ የሚገጥሟቸው ቢሮክራሲያዊ አካሔዶችን ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች መጀመር አንዳለባቸው ገልጸዋል።
የከተማ ሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ጥላሁን በበኩላቸው፣ የከተማችን ወጣቶች መንግሥት በሚያቀርባቸው የሥራ አማራጮች ሁሉ ሥራን ሳይንቁ ሊሳተፉ ይገባል ይላሉ። ወጣቱ ለመብቱ መቆም እና ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን መታግል እና ማስቆም እንዳለበትም ያሳስባሉ። እንደዛ ሲሆን ሀገራችን ፍትኀዊ የሀብት ክፍፍል ያለባት የበለጸገች እና ሰላም የሰፈነባት ትሆናለች የሚል ሐሳብ አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here