የምርመራ ጋዜጠኝነት ፈተናዎች

0
1185

የጋዜጠኝነት ሕይወታቸው የጀመረው በቀድሞው የአዲስ አበባ ክልል 14 ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ ነበር። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ እንዲሁም በሕግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ በማስታወቂያው ቢሮ በነበራቸው ቆይታ ከባድ የሚባሉ ድፍረት የሚጠይቁ ሥራዎችን ተጋፍጠው የመሥራትን ልምድ አካብተዋል። ክልል 14 ቢሮው የራሱ የሆነ ቴሌዝዥን፤ ሬዲዮ እና ጋዜጣ የሌለው በመሆኑ ዜናዎችን በመሥራትና ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመላክ ነው ጋዜጠኝነትን አሃዱ ያሉት፤ የቀድሞው የዐይናችን አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፍቅሬ።

በወቅቱ አይደፈሩም የተባሉ በርካታ ርዕሶችን በሥራቸው ዳስሰዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ የሙስሊም ማህበረስብ ውዝግብ፣ የመስጂድ አካባቢ የደረሱ የሞት አደጋዎችን በካሜራ በማስቀረት፤ በ1987 የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲጸድቅ የነበሩ ንትርኮችን በተቀናቃኝና በገዢው ፓርቲ መካከል በጋዜጣ በመጻፍ፤ በዛው ዓመት የአዲስ አበባ ጎርፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመስቀል አደባባይ ከፖሊስ ጋር ያደረጉትን ውዝግብ በመቅረጽ፣ ዜናዎችንም ዘግበዋል። ይህም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሮች በቀላሉ እንዲከፈቱላቸው አስችሏል።

ታድያ በሥራቸው ውጣ ውረድ ቀርቶ አይደለም፤ እንደውም በዚሁ መገፋት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅጥር በውድድር አሸናፊ ሆነው ተቋሙን እንዲቀላቀሉ መንገድ ሆኗቸዋል። በዛ ቆይታቸውም ዜና ፋይል፣ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም ትንታኔ የሚታወቁባቸው ሥራዎች ናቸው። በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊቱን ያሳተፈ የዘፈን ግብዣ የሚጋብዙበት የዘፈን ምርጫ ፕሮግራምም አይዘነጋም።

በዛላ አንበሳ ግንባር በኩል ከሠራዊቱ ጋር በመሆን እስከ አሲንባ ተራራ የተጓዙት ሳሙኤል፤ ከዚህ የግንባር ተልዕኮ መልስ የሠሯቸው ጠንካራ ዜናዎችን የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጠሉ ሲባል ከራዲዮ ክፍል ወደ ቴሌቪዥን እንዲዘዋወሩና በምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲመለመሉ አድርጓቸዋል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ድርጀት የአመራር ለውጥ የነበረበት ወቅት ሲሆን፣ ስኬት፣ አውደ ሰብ፣ ትኩረት እና ዐይናችን የተሰኙ አዳዲስ ፕሮግራሞች የተዋወቁበትም ነው።
ከእነዚህ ፕሮግራሞች መካከል ‹‹ዐይናችን›› በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ትኩረቱ ያደረገ ነው። ሳሙኤል ለዚህ ሥራ ብቁ ሆነው ተገኙ። ሳሙኤል የተወሰነ ቢያንገራግሩም ላለመቀበል በዚህ ምክንያት አልነበራቸውም። እናም በቀጥታ መጋፈጥን ከሚጠይቀው የምርመራ ጋዜጠኝነት የመገናኘት እንድልን አገኙ።

ሳሙኤል የምርመራ ጋዜጠኝነትን ሲገልጹ፣ ‹‹ለምርመራ ጋዜጠኝነት ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ጠላቶች ናቸው›› ይላሉ። ከተቋማት ተበድለው የወጡ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት መረጃው እንዲወጣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት መረጃ ከሞላ ጎደል የሥራው ማሟያ መሆኑን ይገልጻሉ። ከተበዳይ ወገን የሚመጣውን መረጃ በምርመራ ጋዜጠኝነት በጥንቃቄ መመርመርን የሚሻ፣ ይህም በምርመራ ጋዜጠኝነት ጊዜ ሰፊውን ሰዓት የሚወስደውና ሊሰጠውም እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።
በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍለ መምህር ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ‹‹የምርመራ ጋዜጠኝነት በጽንሰ ሐሳብ ወጥ ያልሆነ፣ በጋዜጠኝነት መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚመልስ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ዜና የምርመራ ዘገባን ነው።›› የሚል አመለካከት እንዳለ ያነሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ዜና ካልተመረመረ የሚሠራ ባለመሆኑ ዘገባ በራሱ የምርመራ ጋዜጠኝነት አካል መሆኑን ነው። በእያንዳንዱ ዜና ውስጥ በመሠረታዊ የጋዜጠኝነት ጥያቄዎች በጣም የተነባበሩ እጅግ ብዙ ደረጃና ጥልቀት ያላቸው ጥያቄዎች በመኖራቸው፣ በተሔደበት ርቀት ልክ የምርመራ ጋዜጠኝነት ወደ መሆን እንደሚሔድ አንስተዋል።
የመረጃ ምንጮች ሊሰጡ የማይፈልጉት አልያም በተቻላቸው አቅም ሊደብቁ የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች ፈልፈሎ የማግኘት ትርጓሜን ይይዛል። ነገር ግን የምርመራ ጋዜጠኝነት የጋዜጠኛው ማንኛውንም ነገር የማወቅ ጉጉት ለማሳካት የሚሠራ ሳይሆን፣ ባይገለጽና ባይዘገብ ሕዝብ የሚያጣው ነገር ካለ፤ በመዘገቡ ደግሞ ሕዝብ የሚጠቀመው ነገር ካለ፤ ይህን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ተሻገር ይጠቅሳሉ።

ዜና እሴት ሊኖረው የሚገባ፣ ተደብቆ የሚያዝ፣ በቀላሉ የማይገኝ፣ የጋዜጠኛውን ብርቱ ጥረት የቡድን ሥራ የሚጠይቅ ሆኖ ሲገኝ፣ አንዱ ‹‹ምንጭ ነው›› የሚለውን ሌላኛው ‹‹ምንጭ አይደለም›› ሲለውና፤ ተጨማሪ ምንጭ ፍለጋ መሔድን የሚያስገድድ ሆኖ ሲገኝ የምርመራ ዘገባ ሊባል እንደሚችልም ይገልጻሉ።
የምርመራ ጋዜጠኝነት መረጃዎችና ማረጋገጫዎችን በጋዜጠኝት ሙያ በመመዘን፣ በተለያየ መንገድና ምክንያት የተሸሸገውን ጉዳይ፤ የሙያውን ሥነ ምግባር በጠበቀ መንገድ እንዴት አድርጎ መፈለግ እንደሚቻል፤ ለዛ የሚሆኑ ተቋማት የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ማውጣት፤ መረጃዎችን የት ሊገኙ እንደሚችሉና መረጃው ቢወጣ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን መለየት የሚያስፈልግበት አግባብን የተከተለ መሆን እንደሚገባው የሚገልጹት ደግሞ የሕግና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያ ሰለሞን ጎሹ ናቸው።

በምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራዎችን የማውጣት ሒደቱ አድካሚና ፈታኝ የሚያደርገው የምርመራው ሥራ መዘዞች በግል ሕይወት፣ በሥራና በገንዘብ ላይ፤ እንዲሁም በብዙ መንገድ የሚታይበት በመሆኑ ነው። ለዚህም ትኩረት የሚፈልግ ጥበብ ነው ማለት እንደሚቻል ሰለሞን ያነሳሉ።

በምርመራ ጋዜጠኝነት የጉዳዩችን ጭብጥ ለይቶ ማወቅ ዋነኛ ለሥራው የሚረዳ ጉዳይ መሆኑንና ይህም መረጃዎችን በማጣራት ሒደት የሚሆን ነው፤ እንደ ሳሙኤል ፍቅሬ ገለጻ። ይሁንና የሚቀርብላቸውን የምርመራ መረጃ ሌሎችን ማስፈራሪያና እንደ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ለመጠቀም የሚሹ መኖራቸው የማይካድ ነው ይላሉ። ቢሆንም ጋዜጠኛው እውነታውን ለማግኘት ብቻ የሚሔድበት ስለመሆኑ ያስረዳሉ። እናም በጉዳዩ የሚዳሰሱ ሁሉም ግለሰቦች የመደመጥ መብታቸውን መገናኛ ብዙኀኑ ሊያከብሩላቸው የሚገባ ስለመሆኑም ያትታሉ።

ሳሙኤል እንዳነሱት፤ ከቀረቡ ጥቆማዎችና ከተሔደባቸው ርቀቶች አንጻር ለእይታ ከበቁት ያልበቁ እንደሚበልጡ ነው። ለዚህም ጉዳዩ የተሳሳተ መረጃ ሲሆን፣ አንዳንዴም በአስተዳደራዊ እርምጃ የሚፈቱ መሆናቸው፤ ከዛ ባሻገር በመንግሥት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት እንዲቆሙ የሚደረጉ ሥራዎች ስለመኖራቸውም ያወሳሉ። ይህ የፕሮግራሙ አለመሠራትም በፕሮግራሙ ተከታታዮችና ፈላጊዎች ዘንድ ተዓማኒነትን የሚያሳጣ ሲያደርግ የቆየ ስለመሆኑም ያስታውሳሉ።
‹‹ዐይናችን ፕሮግራም ስንሠራ የትኛውንም ያህል በመረጃና በእውነት ላይ የተመሰረት ቢሆንም ቢያንስ የአንድ ቤተሰብ ጠላት እናፈራልን፤ ያ ጠላት ያለው ትልቅ መሣሪያ የሥም ማጥፋት ሥራ ነበር›› ሲሉ፤ ከዛም አልፎ የመደብደብ፤ የመንገላታት፤ የጥይት ተኩስ፤ በትዳር ሕይወት ላይ ፈተና እስከማምጣትና እስከማለያየት የሚያደርስ ፈታኝነት እንዳለው ከራሳቸው ሕይወት ልምድ ያነሳሉ።

ይህም ሆኖ ጋዜጠኞች የመገናኛ ብዙኀን የሚሰጧቸውን ዕድሎች በመጠቀም የሚያገኙትን መረጃ በአግባቡ በመያዝ በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ይመክራሉ። ጋዜጠኞች ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከሚሠሩበት መገናኛ ብዙኀን ምንም የሚበረከትላቸው ላይኖር ስለሚችል ሙያተኛው ለሥራው ያለው አክብሮት ላይ ብቻ ትኩረት ቢያደርግ የተሻለ ይሆናል ባይ ናቸው። ይሁንና በገለልተኛ ተቋም በ1994 ከቀድሞው ክቡር ፕሬዝደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሽልማት መቀበላቸውን ያስታውሳሉ።

ሳሙኤል በምርመራ ጋዜጠኝነት ለሽልማት የበቁበትና እውቅና ያገኙበት ‹ዐይናችን› የተሰኘው ፕሮግራም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት፤ ይልቁንም በቀድሞው የማስታወቂያ ኃላፊ በረከት ስምኦን ትዕዛዝ መቋረጡን ይጠቅሳሉ። በዛም ምክንያት እርሳቸው ከምርመራ ጋዜጠኝነት ስለመለየታቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውም ከሥራቸው መሰናበታቸውን አስታውሰዋል።

ምርመራ ጋዜጠኝነት በተጨባጭ
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን የሚታየው የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚሠሩ ሙያተኞች በቁጥር ጥቂት ከመሆናቸው በላይ ያሉትንም በብቃትም ሆነ በልምድ የካበቱ ማድረግን ይጠይቃል። ይህም ዘርፉ በርካቶች እንዲሳተፉበት የሚያሻ ዘርፍ እንደሚያደርገው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የመንግሥት ስርዓቶች ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ካስፈለገ የሕዝብ ጥቅም የሚታይባቸው የምርመራ ሥራዎች ላይ የተለየ ትኩረትና ብቃት ያላቸው ሰዎችን የመመደብ ሥራ ያስፈልጋል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታና አሁን እየተሠራበት ባለው ደረጃ ግን ጥሩ ሥራ እየሠሩ ላሉት ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል። ‹‹የተሻለ ለመሆን ግን የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ፤ መገናኛ ብዙኀንም ራሳቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት አንድ አካል እንዲሆን ማስቻል ይገባል።›› ሲሉ የሚያሳስቡት ሰለሞን ናቸው።

በዚህም የምርመራ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሲታይ፤ በሚፈለገው ልክ የምርመራ ሒደታቸው ሳይጠናቀቅ በአጭር ጊዜ መረጃ የሚወጣባቸው ጉዳዮችና አካሔዶች የሙያ ሥነ-ምግባርና ክልሎት በሚጠበቀው ደረጃ የተሔደበት እንዳልሆነ ማሳያ ነው ይላሉ። ስለዚህም አሳታፊና አበረታች የሆኑ መድረኮች መፍጠርን የሚሹ ስለመሆኑ፤ የሕግና መገናኛ ብዙኀን ባለሙያው ሰለሞን ጨምረው አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲጀምር ምክንያት የሆነው በተቋሙ ኤዲቶሪያል ጽሑፍ የተቀመጠው የሕዝብ ወገንተኝነት ያላቸውን የምርመራ ይዘት ፕሮግራሞች ለመጀመር የታየው መነሳሳት ነው። ይህንን እና በጊዜው የነበረው የሚዲያ አማራጭ ጥቂት መሆኑን የሚያወሱት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሰሎሜ ታደሰ ናቸው።

የምርመራ ጋዜጠኝነት በማይደፈርበት ጊዜ እንዴትና በምን መተማመኛ የምርመራ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች ለመሥራት እንደታሰበ የተጠየቁት ሰሎሜ፤ ‹‹በጽሑፍና አዋጅ ደረጃ የሕዝብ ጣቢያ በመሆኑ በጽሑፍ የተቀመጠውን የሕዝብ ወገኝተኝትን የተገበርኩበት የጽሑፍ መተማመኛ ስለነበረኝ እንጂ ሌላ የጨመርኩት የለም›› ይላሉ። ነገር ግን በሥራው ሒደት በባለሙያው ላይ የሚመጣውን ወቀሳ፤ የባለሞያው ራስን ለመስጠት በመወሰን ሙያውን አንድ እርምጃ የማራመድ ሒደት ነበር ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ለምርመራ ጋዜጠኝነት ያሳዩት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደካማ እንደነበረ ይጠቅሳሉ፤ ሰሎሜ።

አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው አሁን ላይ መገናኛ ብዙኀን ብሔርና ጎሳ ተኮር እየሆነ መምጣቱ፤ አንዱን የማስጠላትና ሌላውን የማስወደድ አካሔድ እንዳለ አስታውሰው፤ መገናኛ ብዙኀኑ የሕዝብ ወገኝተንነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያሰምሩበታል። ለዚህም አሁን እየታዩ ያሉ ነባራዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ መገናኛ ብዙኀን በቂ የምርመራ ሥራዎችን እየሠሩ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሳሙኤል መለስ ብለው በማስታወስ በእነሱም ጊዜ ከነበሩ ጉዳዮች ስፋት አንጻር ምንም እንዳልተሠራ እንደሚቆጥሩት ይጠቅሳሉ። ዝግጅቱም አድናቆትን ያተረፈው በማይሞከርበት ጊዜ የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመሥራቱ እንጂ የዜጎች መፈናቅል፤ የመብት ጥሰቶችንና በጊዜው መሠራት ያለበትን ሁሉ በመሥራቱ አይደለም ይላሉ።
ሰሎሜ ታደሰ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኀኑ በምርመራ ጋዜጠኝነት ገፍተው እንዳይወጡ ፍርሃት አስሮ እንደያዛቸው ከማሳያ ጋር አቅርበዋል። በምርመራ ጋዜጠኝነት የተያዘ ጉዳይ መጨረሻው ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አለማወቅ በመቀጠልም ሊመጣ የሚችለውን ጫና አለመረዳት በርካቶችም በእጃቸው መረጃን ማስረጃም ቢይዙም የሚያመጣውን መዘዝ በማሰብ እንደሚሸሹ ይገልጻሉ።

የምርመራው ባለሙያዎችም በዘርፉ ላይ ወጥተው እንዳይሠሩ በሚገጥማቸው ነገር የሚታገሉላቸው ማኅበራት አለመኖራቸው፣ ለሕዝብ በሚሠሩት ሥራ ለብቻቸው መጠየቃቸው ለዘርፉ ወደ ኋላ መቅረት ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ። ሰሎሜም በነበራቸው የሥራ ኀላፊነት ጊዜ ሥራውን ተግባራዊ ማድረግ ቢጀመርም በጊዜው የተፈጠሩ ችግሮች ከድርጅቱ ውስጥም ጭምር የተነሱ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይህም ከቅርብ ባልደረቦቻቸው ጭምር የቀረበላቸው ‹‹የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች አልተረዳሽም›› የሚል አስተያየት ጭምር እንደነበር ያስታውሳሉ።

መንግሥት ከሚያደርገው ቁጥጥር በተጨማሪ የግል ሳንሱር (Self-Censiorship) በመንግሥት ሚዲያ ጸረ-መንግሥት አካሔዶች ሊኖሩ አይችሉም የሚሉ አመለካከቶች የሚንጸባረቁት ጭምር እንደነበር ይገልጻሉ። ሥራው ከተጀመረ በኋላ ጋዜጠኞች በተነሳሽነት የወጡበትና እምቅ አቅም የታየበት ፕሮግራም መሆኑን በማስታወስ የምርመራ ጋዜጠኝነት በመገናኛ ብዙኀን ዘንድ የሥራ ሁኔታና የአእምሮ ለውጥ ዝግጅትን የሚጠይቅ ስለመሆኑ ያሳስባሉ።

‹‹በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለው የምርመራ ጋዜጠኝነት አረዳድ ያልጠራ ስለመሆኑና የፖለቲካ ተጠያቂነትን ያልለመደ፤ ይህም ባለሥልጣናቱ ጠያቂ እንጂ ተጠያቂ ሆነው የማያውቁበት አሰራር በመኖሩ ነው።›› የሚሉት ሰሞሌ፤ የምርመራ ጋዜጠኝነት ይህን በማፍረስ የሚሠራ በመሆኑ የተላከውን ባለሙያ ለመገናኛ ብዙኀን በምርመራ ጋዜጠኝነት የሚሠሩ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ከማራመድ ይልቅ፤ ‹የሆነ ጠላት አለኝ፤ ጠላት ነው የላከብኝ› የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ይጠቅሳሉ። ይህም በምርመራ ሥራ ወቅት መገናኛ ብዙኀኑ ከቦርድ፣ ከመገናኛ ብዙኀን ኮሚቴ የሚደወልባቸው መሆኑ፣ የተገኘው መረጃ ጥፋቶችን ስለሚገልጥ አስቀድሞ የሚደረግ ከለላ ማሳያዎች ናቸው ይላሉ። መገናኛ ብዙኀን መብታቸው መሆኑን አውቆ የሚተው የመንግሥት አካል ስላለመኖሩም ሰሎሜ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

መሥሪያ ቤቶች መረጃዎችን መከልከላቸው አንዱ ከባድ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ሰሎሜ፤ ነገር ግን መገናኛ ብዙኀኑ በሥራው ዘልቀው ከገቡበት ከኅብረተሰቡ የሚመጣው መረጃ ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ። በወቅቱ ይመሩት የነበረው ‹ዐይናችን› የተሰኘው የምርመራ ፕሮግራም እንደ ፍርድ ቤቶች ሁሉ መረጃዎችን ከኅብረተሰቡ መቀበል የሚችሉበት አሰራር በመዘርጋታቸው መረጃዎች በብዛት ይመጡ እንደነበር ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ለመገናኛ ብዙሃን ዕምነት እንዲኖረው በተቻለ መጠን ተዓማኒነትን ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት መንቀሳቀስ የሚጠይቅ መሆኑንም አያይዘው አንስተዋል። በቀጣይነት ጋዜጠኞች በምርመራ ጋዜጠኝነት ለሚያደርጉት አንድ እርምጃ መጀመሪያ መድፈር ግዴታዬ ነው ብሎ በማሰብ የሙያው አቅም ማዳበር ያለበት ስለመሆኑም ያነሳሉ። የማኅበራት መጠናከር የመገናኛ ብዘኀን አቅም ነው ባይም ናቸው። በተጓዳኝ መረጃ የመስጠት ግዴታን ማኖርና ነባራዊ ሁኔታዎችን ማስተካከል ከተቻለ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ሊሰሩበት የሚችሉት ዘርፍ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።

በ2011 የመገናኛ ብዙኀን ተደራሲያን አስተያየትና የሕዝብ፣ የንግድ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ይዘት አገር አቀፍ ጥናት እንደሚያሳው የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች በአብዛኛው መገናኛ ብዙኀን የሚገባቸውን ድርሻ ተወጥተዋል ብለው እንደማያምኑ ያሳይል። ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎችና ተደራሲያን የጋዜጠኝነት የሙያ ነጻነት እንደሌለ በአጽንኦት እንደሚገልጽ ይጠቅሳል። የችግሩ መገለጫ የሚያደርገው ደግሞ የባለሥልጣናትና የመገናኛ ብዙኀን ሥራ መሪዎች ጣልቃ ገብነት ነው። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚሰጧቸው የጋዜጠኝነት፣ ሚዲና ብዙኀን ኮሚኒኬሽን ትምህርቶች የምዕራብያን የኒዮ ሊብራሊዝም የተቃኘ የጋዜጠኝነት ‹‹የሙያ ነጻነት›› ጎልቶ የወጣበት በመሆኑ የማይቀበሉትና የሚተቹት እንዳሉ ጥናቱ ያሳያል።

በመገናኛ ብዙኀን የሚገኙ መሪዎች የጋዜጠኞች ‹‹የሙያ ነጻነት›› የተጠበቀ እንደሆነ ቢያነሱም በርካታ ጋዜጠኞች ሙያዊ ነጻነት እንደሌላቸው የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ ለዚህ ሙያዊ ነጻነት ማጣት የአለቆች ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ባለሥልጣናት ፍላጎታቸው ብቻ እንዲንጸባረቅ ስለሚሹ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ አለ።

ጠንካራ የመገናኛ ብዙኀን አለመኖራቸው ዘርፉ በመንግሥት እጅ ስር የወደቀ፤ መንግስት ደግሞ ለመገናኛ ብዙኀን ራሱ የሚያቀብልና የሚፈልገውን እንዲሠራ የሚደርግ አልፎም ሊደብቃቸው የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች እያጋለጡ አንዲሠሩ የማይፈቅድ አድርጎታል። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኀን የሚመሩት ማዕቀፍ በምርመራ አውድ የተቃኘ ባለመሆኑ የሕዝብን ድምጽ የሚያሰሙ ሳይሆን የፓርቲንና የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት የሚሰጧቸውን የሚያቀብሉ፤ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያልበራቸው የመንግሥት መጫወቻ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው ሲሉ ሰለሞን ጎሹ ይገልጻል።

አጠቃላይ ዘርፉ የተለያየ ጫናን ይዞ ባለበት የምርመራ ጋዜጠኝነት መጠበቅ አይችልም ሲሉ ሰለሞን ይሞግታል። የግል መገናኛ ብዙኀን ዕድገት አናሳ በመሆኑ የሥነ-ምግባር ጉድለት፣ ሥልጠናዎች ለምርመራ ጋዜጠኛነት የሚያዘጋጁ አለመሆናቸው፣ ጋዜጠኞች እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን ሲሠሩ የሚሰጣቸው ጥበቃ አስተማማኝ አለመሆኑ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተደራረቡ ፈተናዎች ናቸው።

የመገናኛ ብዙኀንን የመቆጣጠርና የመደገፍ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፣ መገናኛ ብዙሃኑ ምን ያህል ጠንካራ ናቸው የሚለው ሃሳብ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን እንዳለበት በማንሳት አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚገባም ይገልጻሉ።

መገናኛ ብዙኀን አሁን ያሉበት ደረጃ ለምርመራ ጋዜጠኝነት መንገድ ጠራጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዐይናችን ፕሮግራም በምሳሌነት የሚያነሱት በባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ገብረጊዮርጊስ አብርሃ ናቸው። ለምርመራ ጋዜጠኝነት የዳር ተመልካች ለሆኑት መገናኛ ብዙኀን በሙያው የሠለጠነ የሰው ኀይልን ከፍላጎት ጋር አቀናጅቶ ያለመሔድ አንዱ ችግር ነው ባይ ናቸው።

መገናኛ ብዙሃኑ በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ክፍተቶች እንዳሉባቸው የማይካድ ሃቅ ነው ያሉት ገብረጊዮርጊስ፤ ለዚህም ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠጥ ተገቢ እንደሆነ ባለሥልጣኑ ያምናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ሰፋ አድርጎ ማሰብንና ትልልቅ የፖለቲካ፣ የፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንት ተቋማት ብቻ ሳይሆን የታችኛውን ማኅበረሰብ በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚታዩ ነገሮችን የጋዜጠኝነት ምርመራ ሊካሔድ የሚችል ነው። መገናኛ ብዘኀን የምርመራ ጋዜጠኝነት በአርትኦት መመሪያ ግልጽ የሆነ አቋም መያዝን የሚጠይቅ ነው። ማኅበራዊ ችግሮችን የሚያጋልጥ መገናኛ ብዙኀን በሕዝብ ዘንድ ተደማጭ ከመሆን ባለፈ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት፤ ተዓማኒነት እና ተደራሽነት እንደሚፈጥር ተሻገር ይገልጻሉ። ለደከመ የሚዲያ ተዓማኒነት አይነተኛው መፍትሔ በምርመራ ጋዜጠኝነት ውስጥ መግባት መሆኑን አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here