ምስክር የማያሻው እውነት!

0
907

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አንድን ሰው መልኩን ብቻ አይቶ ስለዛ ሰው ማንነት፣ ስብእና፣ አስተሳሰብና ጸባይ ምን ያህል መናገር ይቻላል? ምንም ያህል የሚቻል አይመስለኝም። እናም የሚታየው መልካችን ተፈጥሮንና አፈጣጠርን ስላየንበት የምናደንቀው፤ ለሁላችን ለየአንዳንዳችን ብቻ ተለይቶ የተሰጠን ስለሆነ የምንንከባከበው ነው። መልክ ስል ውበትን ነው። ውበት እንደተመልካቹ መሆኑን ልብ ይሏል!

እኔን ጨምሮ ለእህቶቼ መጠየቅ የምፈልገው ጥያቄ ግን አለኝ። መቼና በምን ሁኔታ ነው ውብ እንደሆንሽ የሚሰማሽ? ሰው ሲነግርሽ? ስትደነቂ? መዋቢያ ቀለማትን ስትጠቀሚ? መቼ?

በአገራችን ‹‹መልክ ይኑራት እንጂ ሙያ ከጎረቤት!›› የሚሉት አባባል አለ። እውነታቸውን ነው ብዬ አላምንም። እንደሚታወቀው ዘንድሮም እንጀራ መጋገር፣ ወጥ መሥራትና ዶሮ መገንጠል ከሥልጣናቸው የማይነቃነቁ ብቸኛ የሙያ መለኪያ ናቸው። ታድያ አንዲት ሴት መልክ አላት ብለው ሙያ ሲያስተምሩና ‹‹ሙያ የላትም›› ብለው ሳያሙ ቀርተው የሚያውቁ አይመስለኝም።

የውበት መስፈርቱ ምን እንደሆነም ግልጽ አይደለም። ሞናሊዛን ደጋግመን አይተናል፤ የተባለላትን ያህል ውብ መሆኗን እንጃ። ደግሞ በዚህ በኩል፤ ለዐይነ ስውራን ውበት በመልክ ሳይሆን በድምጽ ውስጥ ይገኛል። እንዲሁም ለወደዱ ሰዎች ውበት ሳያውቁት የማንነት መንትያ ሆኗል እንጂ በካሜራ ለማስቀረት የሚጓጉለት የሚታይ ነገር አይደለም። በዚህ ሁሉ መካከል ታድያ በሰዎች ዐይን መልከ ጥፉ መባልን በመፍራት ከ‹‹ውበት መጠበቂያ›› ነገር ግን አጥፊ ከሆኑ ኬሚካሎች ጋር ውለው የሚያድሩ እህቶች አሉን።

ውብ መሆንሽ የሚሰማሽ ጌጣጌጥ ስታደርጊ እንዳይመስልሽ ወይም ከለበስሽው ጋር የሚዛመድ ቀለም በገጽሽ ላይ ስላኖርሽም ነው ብዬ አላምንም። ጌጣጌጥም ሆነ የውበት ማድመቂያ ያምርብሽ ይሆናል እንጂ ውብ ሊያደርግሽ አይቻለውም። የሴት ልጅ ውበት ያለው ራስን ከመጠበቅ በተጓዳኝ ከራስ መተማመን ላይ ነው።
የትኛውም ሰው መልኩን አልመረጠም። መለሎ ለመሆን ትግል ገጥሞ አሸንፎ ያገኘ፣ አፍንጫውን ወይም ቅንድብና ዐይኑን ‹‹ይሄ ይሻለኛል›› ብሎ የተደራደረም የለም። መልክ ለሁሉም የተሰጠ ነገር ነው። አንዱም በጥረታችን ያገኘነው አይደለም። በአንጻሩ የእኛ የሆነ ነገር ግን አለ፤ ፊታችን ላይ የሚታየው በራስ መተማመን።
አንዲት ሴት መስታወት ፊት ስትቆም የምታየው መልክ ለራሷ ሊያስደስታት ይገባል። ምስክር የሚያስፈልገው ለዳኝነት ነው፤ ‹‹አታምሪም›› ብሎ ክስ የሚመሰርት ካለ ይሞክር። ለሁሉም ተመልካች ዐይን ምሉዕ ሆኖ መታየት የቻለ መልክና ውበት ግን የለም። ታድያ ሜካፕ ይቅር ሲባልም ‹‹ሰው ምን ይላል!›› በሚል ይሉኝታ መሆን የለበትም፤ በራስሽ መቆም ስለመቻል ነው። ስለ ሜክ አፕሽ የሚናገር ሁሉ ያሻውን ቢል እንደማይደንቅሽ ሁሉ፤ በተፈጥሮ መልክሽ ከራስ መተማመን ጋር ሲያይሽ የሚናገር ካለ ተይው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ተብሏል። የውበት መጠቀሚያ የተባሉትን የማትጠቀም ሴት የጎደለባት ነገር እንደሌለ እንድታውቅ ለማስታወስ ነው ይህን ጉዳይ ማንሳቴ። በማንም ላይ ጥገኛ አለመሆን ከቁሳቁስ ይጀምራል። የውበት ‹‹መጠበቂያዎች›› ሊያገለግሉ እንጂ በተጠቃሚ ላይ ሊነግሡና ‹‹ያለእኛ መኖር አትችሉም!›› ሊሉ አልተሠሩም። እናም አላስፈላጊ መስለው ከታዩሽ ትክክል ነሽ።

በዚህ ሁሉ የዓለም ግርግር፣ በዚህ ሁሉ የአገር ውጥንቅጥ መካከል ራስን ፍለጋ የሚያቆም ነገር አይደለም። እናም በዚህ መንገድ ውብ መሆንሽን አትርሺ። በተፈጥሮ ከተሰጠሸ በላይ ሴት መሆንሽ፣ ክብርሽና በራስ መተማመንሽ ውበትሽ ነው። ጌጣጌጥና ቀለማ ቀለሙ ‹‹ያምርብሽ›› ይሆናል፤ ግን ለምን እሱ ይመርብሽ? አመሪበት። አንቺ ከማድመቂያ በልጠሽ ደምቀሽ መታየት ስትችይ!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here