ላል-ይበላ – ስሙና እውነቱ

0
1249

ቤተልሔም ነጋሽ በሥራ አጋጣሚ በፓሪስ በሚካሔደው የሰላም ፎረም ላይ በተዘጋጀ “ላሊበላ የባህል- ለሰላም ፕሮጀክት” የተሰኘ ፕሮጀክት የተነሳው የላሊበላን ነገር መለስ ብለው ወደ ላሊበላ ያደረጉትን ጉዞ እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። በዚህም ላሊበላ ስላለው ገናና ስምና የታሪክ ስፍራ አንጻር ስላልተሰጠው ትኩረት ከነበራቸው ቆይታ ያጋጠማቸውን መሠረት አድርገው አካፍለዋል። በመንግሥት ደረጃ ተወካይ ባልተገኘበት በፓርሱ መድረክም ያነሷቸውን ጥያቄዎችና የተሰጣቸውን መልስ አካትተዋል።

 

“ያለፈ ታሪካቸውን፣ ምንጫቸውና ባህላቸውን የማያውቁ ህዝቦች ሥር እንደሌለው ዛፍ ናቸው”
ማርከስ ጋርቬይ
ላሊበላ – ላል- ይበላ (ማር ይበላል) ከሚል ቃል እንደመጣ ይነገራል። ላሊበላ በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ከአዲስ አበባ 645 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት። እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከዛሬ አርባ በላይ ዓመት በፊት በ1970 በዓለም ታሪክ ቅርስነት መዝግቦ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ዓለም የሚውቃቸው የሚያደንቃቸው እስከዛሬም አርኪኦሎጂና ታሪክ ተመራማሪዎች ትኩረት ያልነፈጓቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ናት።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በመካከለኛው ዘመን ከአንድ ወጥ ድንጋዮች ተፈልፍለው የታነጹ 11 አብያተ ክርስቲያናት ስብሰብ ናቸው። የተፃፉ መረጃዎች እንደሚሉት አብያተ ክርስቲያናቱ በ13ኛው ክፍለ ዘመን እስልምና ተስፋፍቶ ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞ ባስተጓጎለበት ወቅት ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን በኢትዮጲያ ሊሠራ አስቦ በተነሳው ኢትዮጲያዊ ንጉሥ ላሊበላ (ላል- ይበላ) አማካኝነት እንደተገነቡ ሲነገር፤ አመጣጣቸውም የአክሱም ዘመነ መንግሥት መዳከምን ተከትሎ መሆኑ ተፅፏል።

በዚህ ሳምንት ወዳለሁበት ፓሪስ ፈረንሳይ ከመምጣቴ በፊት ባለፈው ሳምንት መሥሪያ ቤቴ ለሠራተኞቹ ባዘጋጀው ዓመታዊ ስብሰባና የመዝናኛ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ከባልደረቦቼ ወደ ላሊበላ አቅንተን ነበር። ላሊበላ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ጀምሮ የማውቀው አካባቢና ምናልባትም ተወልጄ ካደኩበት ሐረርና ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ከተከታተልኩበት አዲስ አበባ ቀጥሎ ያየሁት አካባቢ እንደመሆኑ ከብዙ ጊዜ በኋላ ሳየው ለውጡን ለመገምገም እድል ነበረኝ።

እዚህ ላይ ከአራት ዓመት በፊት በመካከሉ አብያተ ክርሰቲያናቱን በሞሉ በሚገባ ለማየት እድል የሰጠኝን የአንድ ሳምንት ቆይታ ማድረግ መቻሌን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። ወደ ነገሬ ስመለስ ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ሆቴላችን ለመሔድ ያረፍንበት ላል ሆቴል አካል የሆነው ላል አስጎብኚ ባዘጋጀልን ምቹ መኪና ከጥሩ አቀባበል ጋር ተጭነን ወደ ከተማው ጉዞ ጀመርን። ላሊበላን በአውሮፕላን ለማታውቁ ከከተማው ተራራማ አቀማመጥ አንፃር አውሮፕላን ማረፊያው የሚገኘው 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ካለ ገላጣ ሥፍራ ላይ ነው። ዳገታማና አልፎ አልፎም ከታች ሆኖ እየተጠማዘዘ ወደላይ የሚወጣውን መኪና ሲያዩ ፍርሃት ከሚጭረው ተፈጥሮ ውጪ የመንገዱ አለመመቸት ትዝ አይለኝም።

ባሁኑ ጉዞ ግን ገና የአውሮፕላን ማረፊውን ቅጥር እንደወጣን አቧራማ ኮረኮንች ያዘን። በመካከላችን ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የውጪ አገር ዜጎች የሥራ ባልደረቦቻችን ያዩና አልፎ አልፎ እንደ አስተርጓሚም የሚያደርጋቸው ጎልማሳ ዕድሜ ላይ ያሉ ተቀባያችንን ‹‹ውይ ምነው መንገዱ?›› ብለን ለመጠየቅ ሳንበቃ፤ መንገዱ ከተጀመረ ስድስት ዓመታት ማስቆጠሩን፤ ከአንዱ ተቋራጭ ወደሌላ ሲሸጋገር ቆይቶ አሁን በቻይናውያን በመሠራት ላይ እንዳለ ነገሩን። እውነትም ከዚያው የማይመች መንገድ ግማሽ እየሆነ ተዘግቶለት፣ ለመተላለፍም መጠባበቅ ሆኖ ሥራው ሲጣደፍ ለማየት ችለናል።

መንገዱን ጨርሰን ወደ ከተማው ስንገባ ሁሉም ለማለት ይቻላል የሥራ ባልደረቦቼ ላሊበላን እንደማያውቁ ስገነዘብ በተለይ ኢትዮጵያውያኑን መጀመሪያ ስመጣ እንዳልኩት “ላሊበላን ሳታዩ እንዴት ኢትዮጵያዊ ነን ትላላችሁ?” እያልኩ ወደ ከተማው እየዘለቅን መጣን። ያው አቧራ፣ ያው ኮብልስቶን፣ የማይመች መንገድ፣ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት ተሠሩ ለሚባሉት የላሊበላ ድንቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የማይመጥን ዙሪያ ገባ አሁንም የከተማዋ መለያ ነው።
በበኩሌ ተዘዋውሬ ሳይ የተሰማኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ስመጣ የተሰማኝ ስሜት ነው። ላል ይበላ ስመጥሩ፣ አስደማሚው ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ለከተማዋ እንዴት በዝተውባታል የሚል ነው። አዲስ ካዩት ባልደረቦቼም የተገነዘብኩት እንዴት እነኝህ ፍጹም የሚመስሉ ባለግርማ ግንባታዎች ከከተማዋ ጋር ሲነፃፀሩ ያለቦታቸው የተቀመጡ መሰሉ የሚል ነው። ምናልባት ዛሬም ብዙ የማይባሉት ብቸኞቹ ህንፃ ያላቸው ሆቴሎቿ ሲቀሩ አካባቢው ኮስሶ አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲጎሉ ይሆን?

በነበሩን የቆይታ ቀናት አገሬውን በባጃጅ ስንጠቀም፣ አሽከርካሪዎቹን (በተለይ ደንበኛ አድርገን የተወዳጀነውንና ራቅ ወዳለ ሥፍራ መሔድ ስንፈልግ የምንጠራው አብርሃምን) በትናንሽ ሆቴሎች እየሔድን ስንመገብም እንዴት ናችሁ? ስንል ያላቸው አስተያየት ምሬት የተመላ ነው። አሉታዊ ነው። በአብያተ ክርስቲያናቱ አካባቢ ያለው አቀባበል ደካማ ነው።

ሌላው ቀርቶ ከምንሰማው ትርክት ጋር የሕዝቡ ምላሽ አይሔድም። ባለባጃጁ አብርሃም ሆቴላችን ካለበት አንዱ የከተማዋ ክፍል ራቅ ብሎ ተራራ ላይ ወደተሠራው የከተማዋን ውብ ተራራማ ገጽታ ወደሚያሳየው “ቤን – አበባ” ሆቴል ሲወስደን በመንገዱ አለመመቸት እንግልትና አቧራ ውስጥ ሆኜ በቀልድ መልክ “በቃ እናንተ አብያተ ክርስቲያናቱ ይነካሉ ብላችሁ አስፋልት አላሠራ አላችሁ አይደል?” ብለው “ማን ነው ያለሽ! ኧረ እኛ አላልንም ገንዘቡን በልተውት ነው” የሚል መልስ ነው የሰጠኝ።

ከቆይታ በኋላ ወደ ሆቴላችን ሲመልሰን ጥሩ ማር የት እንደሚገኝና ቤተክርስቲያን ለመግባት ነጠላ የት መግዛት እንደምንችል እየጠየቅነው በድንገት በቅርቡ በአማራ ክልል ከከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ በወንጀለኝነት ተጠርጥሮ ስሙ የሚነሳውን የአሳምነው ጽጌን መቃብር ማየት እንፈልግ እንደሆነ ጠየቀን። መንገድ ዳር መሆኑን በከተማው መካከል አደባባይ ተሠርቶ ሃውልት ሊቆምለት እንደታሰበም ጭምር ነገረን። በበኩሌ በብረት አጥር የታጠረውንና ሐውልት መሠራት የሚጠብቀውን መቃብር ሳይ ትዝ ያለኝ “የአንድ ሰው ሽብርተኛ ለሌላ ሰው የነፃነት ታጋይ ነው” የሚለው አባባል ነው።

ይህንን ጽሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ከላይ ጠቆም ለማድረግ የሞከርኩት ይህ የላሊበላ የኋሊት ጉዞ ነበር። ከላይ እንደገለጹኩት በመሥሪያ ቤቴ ፕሮጀክት በኩል ፓሪስ የሰላም ፎረም ለመሳተፍ ስገኝ ከሚቀርቡት ወርክሾፖች አንዱ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ የሚደረገው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ሥራ የሚመለከት መሆኑን ስመለከት የበለጠ በጉዳዩ ላይ ለመፃፍ የነበረኝ ፍላጎት ጨመረ።

በፓሪስ የሰላም ፎረም ላይ ባህልና እምነት ለሰላም ያላቸውን ጠቀሜታ ባየበት ባህልንና ማንነትን ማክበር ሌሎችን እንደማክበርና ዴሞክራሲን እንደማስፈን ይቆጠራል በሚል የሩቅ የሚመስል ተዛምዶውን ባየበት የፈረንሳዩ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ ያዘጋጀው ወርክሾፕ “ላሊበላ የባህል- ለሰላም ፕሮጀክት” የሚል ነበር። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በርትራንድ ዋልከኔር ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ግርድፍ መረጃ (የሕዝብ ብዛት፣ የቆዳ ስፋት- የፈረንሳይን እጥፍ ታክላለች ነው ያሉት መቼም ሁሉንም በእነሱው አንጻር ማየት ይወዳሉ- ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ወቅታዊ ሁኔታ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት በመንገር ከጀመሩ በኋላ) ውይይቱን ሲመሩ በውይይቱ ላይ ለጥያቄ የሚጋብዝ አጫጭር ማብራሪያ የሰጡት የአንድ የጥናት ተቋም ዳይሬክተርና የመካከለኛው ኢትዮጵያ ታሪክ አጥኚ ሜሪ-ላውሪ ዴራትና የሃውልቶች ጥናት ዋና አርክቴክት ሪግስ ማርቲን ነበሩ።

ማብራሪያውን ሲጀምሩ ሚስተር ዋልከኔር የጠቀሱት በዓለም ዙሪያ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ከጦርነትና ከአለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በታሪካዊ ቦታዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት፣ “ማንነታቸውን፣ ምንጫቸውን የሥልጣኔያቸውን ምልክት አጥፉ” የሚል ተልዕኮ ይዘው የተነሱ ሰዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ተናግረዋል። ማንነትና የጋራ ባህል፣ ታሪክን እርስ በርስ ለመረዳዳትና የጋራ ታሪክን መያዝ ለሰላም ያለው ጠቀሜታ ሲብራራ እንደ ላሊበላ ያለ ከአገር አልፎ ለዓለም ሥልጣኔ ምስክር የሚሆን ታሪክ ሰላም ለማምጣት ዓይነተኛ መሣሪያ ሊሆን ይችላልም ተብሏል።

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አሠራርና ልዩ መሆን (ከታች ወደላይ የተገነቡ ሳይሆኑ ከላይ ተነስቶ ወደ ታች እየተፈለፈሉ የመጡ መሆናቸው) ሲገለጽ ከአሠራራቸው ድንቅ መሆን ጋር ተያይዞ ለስምንት መቶ ዓመታት በጎርፍና ዝናብ መፈራረቅ ከድንጋይም ቢሠሩ ከጊዜ ብዛት በደረሰባቸው ጉዳት አደጋ ውስጥ መሆናቸው ተገልጧል። ባለፉት ዐስር ዓመታት በዩኔስኮ አስተባባሪነትና በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ጉዳቱና ስጋቱ ለጠናባቸው አብያተ ክርስቲያናት ጣራ መደረጉን (ጣራው ብዙ ሚሊዩን ብሮች የወጣበት ከመሆኑ በላይ ከላያቸው ተጭኖ ውበታቸውን ማጥፋቱ እንዳለ ሆኖ) ተገልጾ፤ እነኚሁ ከለላዎች ከለላ ካልተደረገላቸው ጋር ተነፃፅሮ አብያተ ክርስቲያናቱ ባሉበት እንዲቆዩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ዋና አርክቴክቱ ሲገልጹ፤ ከተሠሩበት ቁስና ከአሠራራቸው ጋር የሚሔዱ ባለመሆናቸው ግን አሁንም መነሳት ያለባቸው መሆኑና በሌላ መተካታቸው የግድ ነው ብለዋል።

ማብራሪያው ከምናውቀው ላይ (እንደ ኢትዮጵያዊ) ብዙም የጨመረ አለመሆኑን ካሰብኩ በኋላ መድረኩ ለጥያቄና መልስ ክፍት ሲደረግ ጥያቄ ለማቅረብ የመጀመሪያዋ ነበርኩ። ላሊበላ የዓለም ቅርስ ሆኖ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ከመሆኑና ለአስርት ዓመታት አደጋ እንደተጋረጠበት ሲነገር ከመቆየቱ አንፃር (በተለይ አንደኛዋ ተመራማሪ ለአስርት ዓመታት በላሊበላ ላይ ጥናት ማድረጋቸው መገለጹን ተንተርሼ) የኢትዮጲያ መንግሥት በአገር ውስጥ ያለውን ሃብት አሰባስቦ ጥገና እንዲደረግ በማድረግም ይሆን መፍትሔ ከመፈለግ አንፃር ያለውን ቁርጠኝነት እንዴት ያዩታል የሚል ሲሆን ኹለተኛው ጥያቄዬ እዚያ የነበሩትን ኹለት ፈረንሳውያን ባለሙያዎች የኢትዮጵያውያንና የአገሬው ዕውቀትና ልምድ በምን መልኩ የጥገና ሥራው ላይ ይካተታል የሚል ነበር።

ለመጀመሪያው ጥያቄዬ የታሪክ ተመራማሪዋ ሜሪ-ላውሪ እና ሚስተር ዋልከኔር አሁን የሚደረገው መልሶ የመጠበቅ ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፈረንሳይ ባደረጉት የእርዳታ ጥሪ መሠረት የሚደረግና የዳሰሳ ጥናት ሥራው ተጀምሮ ወደ መጠናቀቁ መሆኑን ገለጹ። ይህም መንግሥት ያሳየውን ከፍተኛ ትኩረት ያመለክታል ብለውኛል። ለኹለተኛው ጥያቄ ዋና አርክቴክት ሪግስ ውስብስብ የሆነውን የጥናትና መልሶ የመጠገን ሥራ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከፈረንሳውያኑ መሳ ለመሳ በእኩል ቁጥር እንደሚያከናውኑት ሲያረጋግጡልኝ፤ የቱሪዝም ሚኒስትሯ የሚሰበስቡት ኮሚቴ አጠቃላይ ሥራውን እንደሚመራውም ተገልጾልኛል።

በአቅራቢነትም ይሁን በተሳታፊነት አንድም ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ አለመጋበዙ ግን ማረጋገጫቸውን በሙሉ ልብ እንዳልቀበል አድርጎኛል። ላሊበላን የእኛ ካልን ባህል ሚኒስቴርም ይሁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ይህን መሰል ወርክሾፕ የፓሪስ የሰላም ፎረም አካል እንደሚሆን ካወቁ፣ ተወካይ ለመላክ ያልቻሉት ለምን ይሆን? መመዝገቡና ጥበቃ መደረጉስ ጥሩ ሆኖ ሳለ በየዓለም አቀፍ ፎረሙ ስለኛ ቅርስ ሌሎች እያወሩ የምንዘልቀው እስከመቼ ነው?

በተረፈ ዛሬም ጥበቃዎችን አልፈው ወደ አብያተ ክርስትያናቱ መግባት ባይችሉም፤ ገና ወጣ ሲሉ በልመና አላንቀሳቅስ የሚሉ ታዳጊዎች ብቻ ሳይሆኑ ወጣት ጎረምሶትና አዛውንቶች ሞልተዋል። አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጎብኘት ከቱሪስት ቢሮው ካልተነሱና ቢሮው ለኢትዮጵያውያን ጉብኝቱ ነፃ ነው ቢልም ድጋፍ ግን አድርጉ ብሎ የሚያስከፍለው ሠስር ብር (ድጋፉን ማድረጉ ምንም አይደለም ቢባልም) ሳይከፍሉ እንደ እኔና ጓደኞቼ ተሳላሚ መስሎ በጓሮ በሮች በአቋራጭ ለመጣው ደረሰኟ ትጠየቃለች፣ ካልሆነ ኢትዮጵያዊ ለመሆናችሁ መታውቂያ ትባላላችሁ።

በእግር ተጉዘን ስለመጣን መታወቂያ ያልያዘች የሥራ ባልደረባችን መግባት ተከልክላለች። እኔም ‹‹በቃ ብቻሽን ከምትሆኚ ውጪ ልቆይ›› ብዬ አብሬያት ስቆም፤ ከበር ላይ መታወቂያ እየጠየቁ የሚስገቡት ነጠላ የለበሱ ሰው፤ ከውጪ ጠመንጃ የያዘ ጥበቃ ጠርተው ከግቢው እንድንወጣ እንዲያደርግ ጠይቀውታል “ቤተክርስቲያን አይደለም ወይ የእርስዎን ቋንቋ እያወራች፤ ባልደረባችን ናት እያልን ጭራሽ ከእግዜር ቤት እንዴት ለማስወጣት ያስባሉ” ብላቸው “ለራሳችሁ ደኅንነት ነው” ብለው ከቁብ ሳይቆጥሩን ወደ ቦታቸው ተመለሱ። መከፋቴ የገባው ጥበቃ ቀስ ብሎ ሊያናግረኝ ሲሞክር ነው ያ ሁሉ ጣጣ እንዳሉት መታውቂያ ስላልያዝን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ዐስር ብር ሳንከፍል በጓሮ በር በመግባታችን እንደሆነ የገባኝ።

ሌላው ምን አገባሽ ባትሉኝ አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጎብኘት የሚከፈለው 50 ዶላር በጣም ተወደደ ብዬ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ስከራከር የነበረ ሲሆን ዛሬ ይህን ጽሑፍ ባዘጋጀሁባት ፓሪስ የከተማዋ መለያ የሆነውን አይፍል ታወር (ይቅርታ አድርጉልኝ ለነሱ ከታሪክ አንፃር ያለው ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ) ላይ ወጥቶ ለማየት 45 ዮሮ ስጠየቅ ላሊበላስ ቢያንስ 11 አብያተ ክርስቲያናትን ይዟል፣ ይገባዋል ብያለሁ።
የፍቅር ከተማዋን ፓሪስን በሚቀጥለው ሳምንት ለማስቃኘት ቃል እየገባሁ የዛሬ ጽሑፌን በዚህ ላብቃ።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here