የፌደራል ድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

0
1014

በክልሎች እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለውን የጋራ ገቢዎችን እንዲሁም የፌዴራል መንግሥቱ ለክልሎች የሚያደርገውን ድጎማ የሚያስተዳድር አዲስ ኮሚሽን ሊቋቋም ነው።

ኮሚሽኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥናት ላይ ተመሥርቶ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብለት ሲሆን ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሆኖ የሚቋቋም ነው። እንዲሁም የክልሎችን ድጎማ እና የክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱን የጋራ ገቢ ክፍፍል ቀመር በማዘጋጀት በምክር ቤቱ እንዲጸድቅ ያቀርባል። ይህም የፌዴራል መንግሥቱ ተቋማት ለተወሰነ ተግባር የድጎማ ፕሮጀክቶችን ለማሻሻል የሚያዘጋጇቸው ፕሮጀክቶች ላይ ምክረ ሐሳብ ማቅረብን ያጠቃልላል።

ኮሚሽኑ በፌዴራል መንግሥቱ ባለቤትነት የሚዘረጉ የመሠረተ ልማት አውታሮችና በክልሎች ውስጥ ያለውን ፍትኀዊ ስርጭት አስመልክቶም በጥናት ላይ የተመረኮዘ ክትትል በማድረግ በየጊዜው ሪፖርቱን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ ይሆናል ሲል ለሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ያስረዳል።
በተጨማሪም የተተገበሩ የጋራ ገቢዎች እና ድጎማ ማከፋፈያ ቀመሮችን አተገባበር በቅርብ የመከታተል ሥልጣን የሚኖረው ኮሚሽኑ፣ በተጨማሪም ከምክር ቤቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት የሚያከናውን እንደሚሆን ረቂቅ አዋጁ ደንግጓል።

የኮሚሽነር አመራረጥን በተመለከተም አንድ ሰው ለአምስት ዓመት የሚያገለግል ሲሆን ከኹለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንደማይችል የሚደነግገው ረቂቁ፣ ለምክር ቤቱ ቀርበው የሚሾሙት ኮሚሽነር 66 በመቶ (2/3) ድምፅ ካገኙ ብቻ ሹመታቸው የሚፀድቅ ይሆናል ሲልም ያስቀምጣል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ኹለት የፌዴራሉ መንግሥት ለተመጣጠነ ዕድገት እንቅፋት ካልሆነ በቀር ለክልሎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ሥልጣን ሰጥቶታል። የድጎማ ክፍፍሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ 7 ላይ ቢያስቀምጥም ለክፍፍሉ አስፈላጊ የሆኑ አሰራሮችን በዝርዝር አለማስቀመጡ እንደ ክፍተት ታይቶበታል።

ኮሚሽኑ የድጎማ ዓይነት፣ ዓላማ፣ መስፈርት፣ የክፍፍል ዘዴ፣ የክትትል ቁጥጥር ስርዓት ምን መሆን እንዳለበት እንዲሁም የትኞቹ ተቋማት በዚህ ስር ውስጥ ምን አይነት ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጭምር ይዘረዝራል።

ለቀመር ዝግጅት የሚውሉ ማናቸውም ዓይነት መረጃዎች በዋነኝነት ከፌዴራሉ መንግሥት ተቋማት የሚመነጩ ናቸው የሚለው ረቂቁ፣ እስከዛሬ የነበረውን ክልሎች የሚያቀርቡት መረጃ እና በተለይ በማእከላዊ ስታስቲክስ የሚቀርቡ መረጃዎች መካከል እጅግ የተጋነነ ልዩነት በመኖሩ መቸገሩን የፌደሬሽን ምክር ቤት በተደጋጋሚ ሲገልፅ መቆየቱም የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን የፌዴራል መንግሥቱ መረጃዎች በዋነኝነት ጥቅም ላይ ቢውሉም፣ ከክልል መንግሥታት የሚገኙ አስተማማኛ መረጃዎችን ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችልም ረቂቁ ደንግጓል። ለቀመሩ ዝግጅት አስፈላጊውን መረጃ ያልሰጠ ማንኛውም ሰው በመገናኛ ብዙኀን የመረጃ ነጻነት አዋጅ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል ሲልም አዋጁ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በጀቱን በመንግሥት ከሚመደብ በጀት የሚያገኝ ሲሆን፣ ከተለያዩ ክፍሎች እና አጋር ድርጅቶች የሚገኝ ድጋፍም በረቂቁ እውቅና የተሰጠው የገቢ ምንጭ ነው።

የጋራ ገቢዎች ክፍፍልን መደበኛ እና ሕጋዊ ስርአት እንዲኖረው የረቀቀው ሕጉ ከአንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ፓርቲ የሥልጣን ዘመን ዘላቂ ህልውና ያለው የገቢ ክፍፍል ለመዘርጋት ታስቦ የተረቀቀ ሕግ መሆኑንም ረቂቁ ያስረዳል። የፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የሚደረጉ የተለያዩ የፋይናንስ ድጋፎች ወጥነት እና ቅንጅት እንዲኖራቸው ለማድረግ የታሰበ መሆኑንም ይደነግጋል።

ምንም እንኳን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድጎማና የጋራ በጀት ክፍፍል ላይ ሥልጣን ቢኖረውም፣ የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን እንዲያጸድቅለት የማቅረብ ሥልጣን እንዳለው በረቂቁ ተገልጿል።

መስከረም 27/2011 ባካሔደው ጉባኤ አዲስ ይተገበራል የተባለውና አሁን በሥራ ላይ ያለው የጋራ ገቢ ክፍፍል እና ድጎማ ቀመር፣ የቀመሩ የተግባር ጊዜ ለኹለት ዓመት እስከ 2014 ድረስ እንዲራዘም እና አዲሱ ቀመር ከ 2015 ጀምሮ እንዲፈጸም እንዲሁም የበጀት ዝግጅቱ ከ2012 ጀምሮ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
ለዚህም እንደምክንያት የተጠቀሰው ቀመሩን ለማዘጋጀት ግብአት የሚሆነው የሕዘብ እና ቤት ቆጠራ አለመደረጉ ነበር። በምክር ቤቱ ከፍተኛ ክርክር የተደረገበት ሲሆን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በ1999 በተጠናቀቀው ሕዝብ ቆጠራ ላይ መመስረቱ አሁናዊ መረጃ የማይሰጥ ነው ተብሏል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔውን ከተቃወሙት መካከል ሲሆኑ፣ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ቀመሩ በ2014 እንዲተገበር ወስኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here