በዓይደር ሆስፒታል በኦክስጂን እጥረት ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸ ተገለጸ

በሳምንት በአማካኝ የኹለት ሰዎች ሞት እንደሚመዘገብ ተነግሯል

0
509

አርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የመቀሌ ዩንቨርሲቲ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከኦክስጂን እጥረት ጋር ተያይዞ በባለፈው ዓመትና ዘንድሮ ብቻ ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል፡፡

የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃ ገብረእግዚአብሔር፤ ከኹለት ዓመታት በላይ በክልሉ ሲደረግ በነበረው ውጊያ ምክንያት አብዛኛው የሆስፒታሉ ንብረት ጉዳት እንደደረሰበትና ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መኖሩን ለአዲስ ማለዳ  ገልጸዋል።

በተለይም ከኦክስጂን እጥረት ጋር ተያይዞ በኹለት ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በሆስፒታሉ የሚገኙ የኦክስጅን መስጫ ማሽኖች አብዛኞቹ ያረጁ፣ የተበላሹ እና አገልግሎት ማይሰጡ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ካለው ፍላጎት አንጻር ሆስፒታሉ እያመረተ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን አንድ ሦስተኛውን ብቻ መሆኑን ሜዲካል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በሆስፒታሉ ሲከታተሉ የነበሩ ታካሚዎች ካለው የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ጋር በተገናኘ ኹለት ሦስተኛው ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ ከስኳር ሕመም ጋር ተያይዞ የኢንሱሊን አቅርቦት ቢኖርም የሚዋጥ እንክብል እጥረት በከፍተኛ መጠን በመኖሩ ምክንያት በሳምንት የኹለት ሰዎች ሞት እንደሚመዘገብ ነው የጠቀሱት።

እንዲሁም ከቲቢ፣ ደም ግፊት እና ሌሎች ተያያዥ ሕመሞች ጋር በተገናኝ በየጊዜው ሞት እንደሚኖር ነው የተነገረው፡፡

ከሕክምና ቁሳቁስ ጋር በተገናኘም የራጅ ማሽን ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፤ ማሽኑን ጠግኖ ወደ ሥራ ለመመለስ 99 ሺሕ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

በሆስፒታሉ የሚገኙ የሲቲስካን እና የኤምአርአይ ማሽኖችም ብዙ ዓመት ያገለገሉ በመሆናቸው እና በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ አገልግሎት መስጠት እንዳቆሙ ተጠቁሟል።

አዲስ የሲቲስካን እና የኤምአርአይ ማሽኖችም ገዝቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋልም ነው የተባለው።

እንዲሁም ዓይደር ሆስፒታል በኢትዮጵያ ካሉ ሰባት የካንሰር ሕክምና አገልግሎት ሰጭ የሕክምና ተቋማት አንዱ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ በጦርነቱ ምክንያት የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ማሽን ወደ አገር በማስገባት ሂደት በመስተጓጎሉ ሕክምናው እየተሰጠ አለመሆኑ ተነግሯል።

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከተመሰረተ 15 ዓመታት እንዳስቆጠረ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ከጦርነቱ በፊት በዓመት ከ300 ሺሕ በላይ ታካሚዎችን ሲያስተናግድ እንደነበር ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፀጋዬ ተክለሐይማኖት በሆስፒታሉ ከመድኃኒት እና ከተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ጋር ተያይዞ በተለይም የኤችአይቪ፣ የስኳር እና የደም ግፊት ታማሚዎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ ከኹለት ዓመታት በላይ ሲደረግ በነበረው ውጊያ በላቦራቶሪ ማሽኖች ላይ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰ የተገለጸ ሲሆን አስከ አሁን ምንም አይነት ጥገና እንዳልተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ምንም ዓይነት የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በተጨማሪም በ2014 በጀት ዓመት ደሞዝ ለሠራተኞች መሉ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው፤ በሆስፒታሉ አሉ የሚባሉ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሶማሌ ላንድና ወደ መሀል አገር መስደዳቸውን ጠቅሰዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here