በአፋር ክልል የተከሰተው አንበጣ የማሽላ በቆሎ ሰብሎችን ማውደሙ ተገለጸ

0
532

አርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአፋር ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የበቀለውን ሰብል በማወደሙ፤ አርሶ አደሮችን ደጋሚ አርሰው እየዘሩ መሆኑ ተገልጿል።

በአባላ ከተማ አስተዳደር የእርኩዚ ቀበሌ አስተዳዳሪ አሊ አብዱሩፍ፤ “የአንበጣው መንጋው መነሻውን ከቀይ ባህር አካባቢ በማድረግ ከሰኔ 15/2015 ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ በአካባቢው ውድመት እያሰከተለ ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው በክልሉ የሚገኙ 15 ወረዳዎችን ማዳረሱን ገልጸው፤ እርኩዚ በተባለ ቀበሌ ከ45 ሄክታር በላይ የበቆሎ እና ማሽላ ሰብልን ሙሉ ለሙሉ በማውደሙ አርሶ አደሮች ኹለተኛ አርሰው እየዘሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንበጣው የተከሰተው የደረሱ ሰብሎች በሚሰበሰቡበት እና ለኹለተኛ ዙር የእርሻ ሥራ በሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ ከማሽላ እና በቆሎ ሰብል በተጨማሪ ለእንስሳቶች የሚሆኑ እጽዋቶችን እያወደመ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በአጭሩ ለመቆጣጠር መድሃኒት እንዲሰጣቸው ለክልሉ ግብርና ቢሮ በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም፤ “የመድሃኒት እጥረት አለ” በሚል እስካሁን እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው ከአፋር ክልል በተጨማሪ ወደ አማራ እና ትግራይ ክልሎች እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት በደሮን በመታገዝ አንበጣውን ከአካባቢው ለማስወጣት ሲያደረገው የነበረውን ድጋፍ በመቆሙና እስካሁን ምንም አይነት ድጋፍ ባለማድረጉ፤ የአንበጣ መንጋውን የመከላከል ሥራ በአርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ እየተከናወነ ነው ተብሏል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከግብርና ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here