አርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ሳምሪ በመባል የሚጠራው የታጠቀ ቡድን በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ፣ ሽንፋ እና ሹመት መንዶካ በተባሉ ቦታዎች በኩል ሰርጎ በመግባት ጥቃት መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ጥቃት የፈጸመው ረቡዕ ነሐሴ 03/2015 ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ በሱዳን ድንበር የነበሩ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከአካባቢው አለመኖራቸውን አረጋግጠው ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው በመግባት ተኩስ ከፍተዋል ነው ያሉት።
ታጣቂ ቡድኑ በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞ ነው ጥቃት የሰነዘረው የተባለ ሲሆን፤ በወቅቱ ድንበር ሲጠብቁ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቋራ እና መተማ አካባቢ ለኹለት ሰዓታት ያህል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ ነበር ተብሏል።
ሆኖም የመከላከያ ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ ማድረግ በጀመሩ በትንሽ ደቂቃዎች ውስጥ፤ የሳምሪ ቡድን ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች የእርስ በእርስ ውጊያቸውን በማቆም ተባብረው ቡድኑን ወደመጣበት መመለሳቸውና የተወሰኑ የሳምሪ ቡድን አባላትንም እጅ እንዲሰጡ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው።
ቡድኑ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጨፍጨፍ አስቦ በሰነዘረው ጥቃት ጉዳት አላደረሰም የተባለ ሲሆን፤ ከሳምሪ ታጣቂ ቡድን በተጨማሪ ሌሎች ታጣቂዎችም በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ በመጠቀም ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ እንደሚያደረጉ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ሳምሪ በሚል ሥም የሚጠሩ የታጠቁ ኃይሎች ከኹለት ዓመት በፊት በማይካድራ ከተማ እና አካባቢው የሚኖሩ በርካታ ንጹሃንን ጨፍጭፈው ወደ ሱዳን ማምለጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የሰላም አስከባሪ ባለሙያ ሻንበል ነጋ፤ “አሁን ላይ ሰላም ነው” የሚል ምላሽ በመስጠት፣ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡



