አርብ ነሐሴ 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ምድር በተለይም በኃይል ከያዘቻቸው የትግራይ አካባቢዎች እንድታስወጣ መጠየቃቸው ተገልጿል።
አምባሳደር ዳረን ዌልች ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት በግልጽ እንዳስቀመጠው ኤርትራ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ በተለይም ከትግራይ እንድታስወጣ የጠየቁ ሲሆን፤ ይህም እንዲሆን እንግሊዝ በጽኑ ትፈልጋለች ብለዋል።
የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተም አገራቸው እየተከታተለችው እንደምትገኝም ተናግረዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የፕሪቶርያውን ስምምነት አፈጻጸሙን የሚከታተለውን የአፍሪካ ኅብረት የክትትል፣ ማረጋገጥ እና የተልዕኮ ማስከበር ቡድንን ለማገዝ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የብሪታኒያ መንግሥት ልዑክ በትግራይ ጉብኝት እያካሄደ እንደሚገኝና ከክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ጋር መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሬዘዳንቱ የኤርትራ መንግሥት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላይ እንቅፋት በመሆኑ የብሪታኒያ መንግሥት ለፕሪቶርያው ስምምነት ትግበራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
በተያያዘ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይባህር አከባቢ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሳራህ ሞንትጎምሪ እና ሉዑካቸውን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
ከልዑካኑ ጋር በዩናይትድ ኪንግደም የቀጠናው ሰብአዊ ዕርዳት ዙሪያ፣ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር፣ ተግዳሮቶች እንዲሁም ሰላምን ለማጽናት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውንም ነው የገለጹት።
ልዑካኑ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ቦታ ድረስ በመሄድ ያለባቸውን ችግር መመልከታቸውንም በመልዕክታቸው አካተዋል፡፡



