ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት ከወርቅ ሽያጭ ያገኘችው ገቢ ከባለፈው ዓመት በ333 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱ ተገለጸ

የዘንድሮው ጠቅላላ የውጭ ንግድ ገቢ በ12 በመቶ ወይም በ500 ሚሊ ዶላር ቀንሷል

0
476

ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ወርቅን ለወጭ ገበያ በማቅረብ ያገኘችው ገቢ በ2014 በጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር፤ በ333 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን ማዕድን ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ከወርቅ የውጭ ንግድ 560 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን በማውሳት፤ በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ 3 ነጥብ 5 ቶን ወርቅ 226 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ነው የጠቀሰው።

ከአንድ ወር በፊት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፍ የውጭ ንግድ 251 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱና ይህም ከአጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ 6 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚሸፍን ተገልጿል። በበጀት ዓመቱ ከማዕድን ዘርፍ የውጭ ንግድ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ323 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱም ተገልጿል።

ከማዕድን ዘርፍ የውጭ ንግድ 90 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ወርቅ ቢሆንም፤ ገቢው የመቀነሱ ምክንያት ዋነኛ የወርቅ ማዕድን አምራች ከሆኑት ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ነው ተብሏል።

እንዲሁም በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ድንበር እየተባባሰ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ ከወርቅ ማዕድን የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ ምክንያቶች መሆኑ ተመላክቷል።

በጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ በ12 በመቶ መቀነሱም የተጠቀሰ ሲሆን፤ በ2015 በጀት ከውጭ ንግድ የተገኘው ጠቅላላ ገቢ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል።

ይህም በ2014 በጀት ዓመት ከተገኘው 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር፤ በ500 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱ ታውቋል። በ2015 በጀት ዓመት ከውጭ ንግድ ለማግኘት የታቀደው ጠቅላላ ገቢ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ነበር ተብሏል።

ከኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቡና ምርት መጠንም በባለፈው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው የቡና መጠን ጋር ሲነጻጻር፤ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን የቡና ላኪዎች ማህበር ለአዲስ ማለዳ መግለጹ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here