በአዲስ አበባ፣ ሸገር፣ ቢሾፍቱ እና ወልቂጤ ከተሞች ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ እስር መኖሩ ተገለጸ

0
374

እሁድ ነሐሴ 7 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ወልቂጤ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ብሔርን መሰረት ያደረገ የጅምላ እስር መኖሩን አዲስ ማለዳ በየከተሞቹ ካሉ ነዋሪዎች ቅሬታ ደርሷታል።

በመዲናዋ ኮተቤ፣ ሳሪስ፣ ቄራ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ሃና ማሪያም እና የተለያዩ ቦታዎች ላይ የጅምላ እስር መኖሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 28/2015 አዲስ አበባ ውስጥ ወንድሜ በድንገት ታስሮብኛል ያሉ አንዲት ሴት፤ “ልክ ሲይዙት ‘ይዘውናል ግን የት እንደሚወስዱን አላወቅንም’ ብሎ ነው ቴክስት ያደረገው። በአካባቢው የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ስንሄድ እዚህ የሉም ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ነው ያሉት አሉን። እዚያ ስንሄድም እዚህ ያሉት ሐሙስ ዕለት የተያዙት ናቸው አሉን። ከብዙ ልፋት በኋላ ኮተቤ አካካቢ ወንድይራድ ትምህርት ቤት መኖራቸውን አወቅን። ትምህርት ቤት ዉስጥ ስለሆነ ያሉት በየቀኑ ምግብ የምናደርሰው እኛ ነን።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የታሰሩ ሰዎች አልፎ አልፎ መለቀቅ ከፈለጉ ብር እንደሚጠየቁም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በተዋቀረው ሸገር ከተማ አስተዳደር እንዲሁ ማንነትን መሰረት ያደረግ እስር በስፋት እየተፈጸመ ነው የተባለ ሲሆን፤ ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ ግለሰብ በተለይ በሰበታ ከተማ በርካታ የአማራ ተወላጆች ታስረዋል ብለዋል።

ለአብነትም የሚፈልጉትን ሰው ሥም ዝርዝር የያዙ የኦሮሚያ ፖሊሶች ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ አራት ሰዎችን እንዲሁም በቅርብ እርቀት ከሚገኘው ከባለዛፍ ፋብሪካ ስምንት የአማራ ተወላጆችን ወስደዋል ነው ያሉት።

የሰበታ ማርሚያ ቤት በእሰረኞች መጨናነቁን እስረኞችን ለመጠየቅ ከሄዱ የተመረጡ ሰዎች መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸውም፤ “እኛም አንድ ቀን መታሰራችን አይቀርም። የሚመለከተው አካላት በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን በድል ሊያስቆም ይገባል።” ብለዋል።

ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ ሌላኛው በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ሰሞኑን በወልቂጤ ከተማ ባልተለመደ መልኩ የክልሉ ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በጋራ በመሆን በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ቅኝት ያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ አርብ ነሐሴ 05/2015 ሌሊት አምስት ሰዓት ጀምሮ በብሔር አማራ የሆኑ ንጹሃን እና ሰላማዊ ዜጎችን እየተለዩ ወደ እስር ቤት በጅምላ መወሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሎቹ ሌሊት ላይ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በማቅናት እና በር በማስከፈት እንዲሁም በኃይል ገንጥይሎ በመግባት፤ ያላንዳች ምክንያት እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመያዝ ወደ እስር ቤቶች እና ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚወሰዷቸውም አስረድተዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሎች ሰዎችን በሚይዟቸው ወቅትም አካላዊ ድብደባ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽሙባቸው ተናግረዋል፡፡

“የሚያዙ ሰዎች ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሌሉ እና አብዛኞቹ የጉልበት ሰራተኛ የሆኑ ናቸው” ያሉት ነዋሪዎች፤ “የጸጥታ ኃይሎቹ ለምን ይህን እንደሚያደርጉም የምናውቀው ነገር የለም።” ብለዋል።

አክለውም፤ “ምንም ዓይነት ወንጀል ላይ ተሳትፎ ሳይኖረን ሊያስሩን ይችላሉ በሚል ስጋት ተደብቀን ነው ያለነው።” ሲሉም ተደምጠዋል።

በሌላ በኩል በቢሾፍቱ ከተማ በተለይም ቀበሌ አራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸም ከጀመረ ሳምንት ሆኖታል ይላሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የከተማው ነዋሪዎች፡፡ ከቤት ለቤት ፍተሻ በተጨማሪ በሥራ ቦታ እና በመንገድ ላይ ድርጊቱ እንደሚፈጸም ገልጸው፤ “ድርጊቱን የሚፈጹሙት የኦሮሚያ ፖሊስ እና ሚሊሻ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን ነው።” ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ድርጊቱ በአማራ ክልል በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ካለው ውጊያ ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ “ምንም ዓይነት ወንጀል ላይ ያልተሳተፉ ንጹሃንን በጅምላ ማሰር ተገቢ አካሄድ አይደለም።” ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ዜጎች ያቀረቡትን ቅሬታ መሰረት በማድረግ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የጠየቀች ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሠ “በአካል መጥታቹ ያለውን ሁኔታ መታዘብ ትችላላችሁ።” በማለት በስልክ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጠጄ መሐመድ እንዲሁ፤ “ለሥራ ጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ ሄጃለሁ ስለ ጉዳዩ የሰማሁት ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ስልክ ባለማንሳታቸው ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here