በደራ ወረዳ አስራ ሰባት ሰዎች በኦነግ ሸኔ መታገታቸው ተነገረ

ታጣቂ ብድኑ በዚህ ሳምንት አምስት የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች አግቶ እንደነበር ተገልጿል

0
424

አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ በመባል በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን 17 ሰዎችን ማገቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ታጣቂው ቡድን እገታውን የፈጸመው ሰኞ ነሐሴ 08/2015 ሌሊት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከታገቱት ውስጥ የአንድ ቤተሰብ አራት አባላት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

አስራ ሰባቱ ሰዎች በተወሰዱበት ሌሊትም የታጣቂ ቡድኑ አባላት በከተማዋ ከነበሩው የመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ እንደነበር ነዋሪዎቹ አክለዋል።

የኦነግ ሸኔ አባላት አሁንም በወረዳው ሥር ባሉ ባቡድሬ፣ ራቾ እና ድሬ መንቃታ የገጠር ቀበሌዎች በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተከትሎ፤ በርካታ ነዋሪዎች ባደረባቸው የጸጥታ ስጋት አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው ተብሏል።

የታጣቂ ቡድኑ አባልት ተሽከርካሪ በማገት ጭምር በተደጋጋሚ መሰል ተግባር በወረዳው እንደሚፈጽሙ እና በተለይም ወደ ዋና ከተማዋ ጉንዶ መስቀል በፈለጉት ሰዓት እንደሚገቡም ተገልጿል።

እንዲሁም “በወረዳው የሚኖሩ ወጣቶችን በማስታጠቅ ለቡድኑ ዓላማ መስፈጸሚያ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በርካታ ወጣቶች የዚሁ ታጣቂ ቡድን አባል እየሆኑ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በወረዳው በስፋት መንቀሳቀስ ከጀመሩ ከኹለት ዓመት በላይ እንዳስቆጠሩ በመጥቀስም፤ “ነዋሪዎች በማገት ገንዘብ መቀበል እንዲሁም ግድያና ማፈናቀል የመሳሰሉ ጥቃቶችን በተደጋጋሚ እያደረሰ ነው፡፡” ሲሉም ተደምጠዋል።

በሌላ በኩል፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በዚሁ ሳምንት ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት የሚገኘው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ አምስት ሠራተኞችን ሌሊት ላይ ከመኖሪያቸው አፍነው መውሰዳቸውን አዲስ ማለዳ ከሠራተኞች ሰምታለች።

ሆኖም በታጣቂ ቡድኑ ከተወሰዱት አምስት ሰዎች መካከል አራቱ የተጠየቁትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከፍለው ተለቀዋል የተባለ ሲሆን፤ ቀሪው አንድ ግለሰብ ግን የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው እስከ ዛሬ ድረስ አለመለቀቃቸው ነው የተገለጸው።

ታጣቂ ቡድኑ በፋብሪካው ሠራተኞች ላይ መሰል ድርጊት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም ተብሏል።

አዲስ ማለዳ በተለይም በደራ ወረዳ በታጣቂ ቡድኑ ስለታገቱ ሰዎችና ስላለው የጸጥታ ሁኔታ ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደራ ወረዳ አስተዳደር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገችው ተዳጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here