ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትናንትናው ዕለት በወልቂጤ ከተማ መካሄድ በጀመረው “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” የምስረታ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል ታረቀኝ ደግፌ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አዲስ ማለዳ ከምክር ቤት አባሉ የቅርብ ሰዎች አረጋግጣለች።
የምክር ቤት አባሉ በጉባኤው ላይ የተቃውሞ ሃሳብ ከሰጡ በኋላ ስብሰባውን ረግጠው ሲወጡ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ነው የተገለጸው።
በከተማዋ እየተካሄደ ባለው የምክርቤት ጉባኤ፤ የነባሩ ደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የስብሰባውን አጀንዳ እያቀረቡ ባለበት ወቅት “እያቀረባችሁት ያለው አጀንዳ በዚህ ምክር ቤት ሊቀርብ አይገባም፤ አግባብም አይደለም” የሚል ንግግር ተናግረው እንደነበር ተሰምቷል።
የምክር ቤቱ አባሉ አክለውም፤ “ጉራጌ በክልል ለመደራጀት ወስኗል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ጉባኤ ሕገመንግስቱን የሚጻረር ነው።” በማለት በጉባኤው ላይ ቅሬታ ማሰማታቸውም ነው የተጠቆመው።
“ጉራጌ በራሱ ምክር ቤት በክልል ለመደራጀት መወሰኑን የማትቀበሉ ከሆነ ጉራጌን በመቅበር ሂደት ላይ ተሳታፊ መሆን አልፈልግምና ከጉባኤው ለመውጣት እገደዳለሁ።” ማለታቸውም ተገልጿል።
የምክር ቤት አባሉ በጉባኤው ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ፤ ምክር ቤቱ ሃሳባቸውን እንደማይቀበለውና ጉባዔውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸው፣ ከጉባኤው ሲውጡ በሥፍራው የነበሩ የጸጥታ አካላት ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ነው የተጠቆመው።
ነገር ግን የምክር ቤት አባሉ በጸጥታ አካላት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በሗላ አመሻሹ ላይ ከእስር መለቀቃቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
ታረቀኝ ደግፌ የደቡብ ክልል ምክር ቤትን የተቀላቀሉት፤ በ2013 በተደረገው አገራዊ ምርጫ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ወክለው በመወዳደር ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ለኹለት ጊዜ ያህል ለእስር ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ እንዳለ ስጦታው “ጉዳዩን በወሬ ደረጃ ሰምቻለሁ፣ በአካል ተገኝቼ ግን ማረጋገጥ አልቻልኩም።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እዩኤል ሰለሞንን የጠየቀች ሲሆን፤ ጉዳዩን ካደመጡ በኋላ ስልኩን በመዝጋታቸው ምክንያት የፓርቲውን ምላሽ ማካተት አልተቻለም።
የተሻሻለው የደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት፤ የክልሉ ምክር ቤት አባል “ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀል አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ ያለመታሰርና ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ለእስር ከተዳረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክርስትያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶክተር ካሳ ተሻገር እንዲሁም ከአማራ ክልል የምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያለው በመቀጠል አራተኛው የምክር ቤት አባል ሆነዋል።



