ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሞከሩ ከ60 በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ባህር ውስጥ ሰጥመው መሞታቸ ተገለጸ
ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከአንድ ወር በፊት፣ ከኬፕ ቨርዴ ተነሥተው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ጉዞ ላይ ከነበሩ፣ ከ100 በላይ ሴኔጋላውያን ስደተኞች ውስጥ፤ ከ60 በላይ የሚሆኑት በባሕር ሰጥመው መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) አስታውቋል።
ፍልሰተኞቹ በተሳፈሩበት ጀልባ ላይ፤ ሰባት አስከሬኖች እንደተገኙና የደረሱበት ያልታወቁ 56 ተሳፋሪዎች ደግሞ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ነው ድርጅቱ የገለጸው።
የሴኔጋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ 38 ፍልሰተኞችን ከኬፕ ቨርዴ የባሕር ዳርቻ እንደታደገ ተናግሯል።
ፍልሰተኞቹን ያገኛቸው የስፔን ዓሣ አስጋሪ መርከብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አንድ የስፔን የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጀት ፍልሰተኞቹ፥ በአንድ ትልቅ የዓሣ ማስገሪያ ጀልባ ተጭነው ከአንድ ወር በፊት ከሴኔጋል እንደተነሡ ጥቆማ ሰጥቷል።
ኬፕ ቨርዴ፣ ከአፍሪካ የሚነሱ ፍልሰተኞች ወደ ስፔን ለመግባት በሚያደርጉት አደገኛ የባሕር ጉዞ መሥመር ላይ ትገኛለች።
በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ እንዲሁም በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በየዓመቱ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተጠቅሷል።



