ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው አቢቹ እና ኘአ ወረዳ ስምንት ሰዎች “ራሳቸውን ፋኖ ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች” ታግተው መወሰዳቸውን የታጋች ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአንድ ታጋች ሚስት ድርጊቱ የተፈጸመው ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 13/2015 መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለቤታቸው ገበያ ውለው በመኪና እየተመለሱ ባሉበት ወቅት መታገታቸውን ገልጸዋል።
እግታው የተፈጸመው በወረዳው በተለምዶ መገንጠያ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ታጋቾች የተያዙት ወደ መኖሪያቸው ለመድረስ በግምት አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀራቸው መሆኑም ተጠቅሷል።
አጋቾቹ ሰዎችን እና ሲጓዙበት የነበረውን ተሽከርካሪ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ ተብሎ ሚጠራ ቦታ እንደወሰዷቸው እና እስካሁን አለመለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
በተለይም የአገር መከላከያ ሠራዊት እና “ፋኖ” የሚባለው ታጣቂ ኃይል በአማራ ክልል ግጭት ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ፤ ታጣቂዎቹ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ መሰል ተግባራት ሲፈጽሙ ተስተውሏል ብለዋል፡፡
የአቢቹ እና ኘአ ወረዳ የኮሚዪኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብደታ ኃይልዬ፤ “ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ወረዳው በመግባት እያደረሱ ያሉት ጥቃት እየተባባሰ ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ ባለፈው ቅዳሜ ከታገቱት ሰዎች መካከል ማዳበሪያ ለገበሬው ሽጠው ሲመለሱ የነበሩ የግብርና ጽህፈት ቤት ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ነሐሴ 01/2015 የፋኖ ታጣቂዎች በወረዳው በምትገኝ መንዲዳ ከተማ ዘልቀው በመግባት ስምንት ንጹሃን መግደላቸውን እና ማቁሰላቸውን አስታውሰው፤ “የሚመለከተው አካል በጊዜ እልባት ካልሰጠው ጉዳዩ የከፋ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡” ነው ያሉት።
አሁን ላይ የታገቱት ሰዎች የኹሉም ስልክ እንደማይሰራ እና ቤተሰብ በከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ እና ለማስለቀቅ በአካባቢው የታጣቂ ቡድኑ አባላት በስፋት ስለሚንቀሳቀሱ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡



