ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያና የመን ድንበር ላይ “በድንበር ጠባቂዎች ተፈጽሟል” የተባለውን የኢትዮጵያዊያን ግድያ በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ- የመን ድንበር ላይ “በጅምላ ተገድለዋል” በሚል ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት ላይ የተላለፈውን መረጃ በትኩረት እየተከታተልኩኝ ነው ብሏል፡፡
መንግሥት ከሳዑዲ መንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ጉዳዩን በአስቸኳይ በማጣራት እንደሚያሳውቅ የገለጸ ሲሆን፤ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስም አላስፈላጊ የሆኑ ግምቶችን ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባም አሳስቧል።
ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረብያ መሰል አሰቃቂ ድርጊቶችን እንደሚያወግዙ የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ኹለቱ አገራትም የረዥም ጊዜ ጠንካራና ጥሩ የኹለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ሂዩውማን ራይትስ ዎች እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ወር ድረስ፤ የየመን ድንበርን ለመሻገር የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች መገደላቸውን ትናንት ነሐሴ 15/2015 ባወጣው የምርመራ ሪፖርት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ እማኞች “የሳዑዲ ወታደሮች ከባድ መሳሪያዎች በመጠቀም ድንበሩ ለማቋረጥ በሚሞክሩ ሰዎች ላይ ኹሉ ተኩስ እንደሚከፍቱና ጉዳት ደርሶባቸዉ ሕይወታቸዉ ያላለፈ ሰዎችንም እየፈለጉ ወደ ማጎሪያ ካምፕ እንደሚያስገቡ ነግረውኛል” ሲል ባወጣው ሪፖርት ላይ ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅቱ፤ ለእነዚህ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሕጻናት እና ሴቶች ሞት፣ የአካል ጉዳት እና ስቃይም የሳዑዲ ባለስልጣናትን ተጠያቂ አድርጓል።



