ቅዳሜ ነሐሴ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥር በቅርቡ በተደራጀው አማሮ ኮሬ ዞን፣ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ የሕዝብ እንደራሴዎች ወደ ቦታው ቢያቀኑም፤ ውይይቱን እንዳያደርጉ በዞኑ አስተዳደር መከልከላቸውን የፌደራልና የክልል የሕዝብ ምክር ቤት አባላት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር አወቀ አምዛየ “ሕገ መንግሥቱ ‘በክረምት ወቅት እና በየካቲት ወር የሕዝብ ውይይት መካሄድ አለበት’ በሚለው መሰረት፤ ወደ አማሮ ኮሬ ዞን በመሄድ ከመረጠን ሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ አስተዳደሩን ብንጠይቅም ተከልክለናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከሰኞ ነሐሴ 22/2015 ጀምሮ የቀድሞው የአማሮ ኮሬ ልዩ ወረዳ የአሁኑ የአማሮ ኮሬ ዞን አስተዳዳሪ ወገኔ ብዙነህን በጉዳዩ ዙሪያ ለማናገር ቢሯቸው ድረስ ቢሄዱም፤ ቢሮ ውስጥ እያሉ ‘የለም በሏቸው’ በማለት ለማግኘት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ነው የገለጹት፡፡
“ለኹለተኛ ቀን በስልክ ደውለን ለማነጋገር ብንሞክርም ‘ስብሰባ ላይ ነኝ አሁን አልችልም’ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ “ለሦሰተኛ ጊዜ ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም፤ ‘ታምሜ ቤት ተኝቻለሁ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑትን ታረቀኝ በቀለን አነጋግሯቸው’ በማለት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።” ሲሉም አክለዋል፡፡
ከሰኞ ሐምሌ 22/2015 ጀምሮ እስከ ትናንት አርብ ሐምሌ 26/2015 ድረስ በተደጋጋሚ የዞኑን አስተዳዳሪ ለማግኘትና ሰለጉዳዩ ለማውራት ያደረጉት ሙከራ፤ አመራሮቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አለመሳካቱን የገለጹት አወቀ፤ በዚህም ከሕዝቡ ጋር ተገናኝተን ለመወያየት አልቻልንም ብለዋል።
“ከመረጠን ሕዝብ ጋር እንዳንወያይ የተፈለገው፣ በዞኑ ከፍተኛ የሙስና ችግር በመኖሩ ነው።” ሲሉም ገልጸው፤ በመንግሥት አመራሮች ምን ያህል ብር እንደወጣ የማይታወቅበት ደረቅ ቼክ እንደሚፈረም እንዲሁም፣ በሕገወጥ መንገድ ከግለሰቦች የሞተር ብስክሌቶችን ገዝተው እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል።
እንዲሁም “ግለሰቦች በጀምላ እየታሰሩ ያለፍርድ ሂደት ብዙ ጊዜ የሚቆዩበት ቦታ በመሆኑ፤ ችግሩን ሕዝቡ ይፋ እንዳያወጣው ስጋት ስላደረባቸው ነው ውይይቱን የከለከሉት።” ብለዋል፡፡
ሊደረግ የነበረው የሕዝብ ውይይት፤ “በዞኑ ውስጥ ያለውን የአስተዳደር እና የልማት ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በዞኑ በኩል መፈታት ያለበትን ዞኑ እንዲፈታ፣ በክልሉ በኩል መፈታት ያለበትን ደግሞ ክልሉ እንዲፈታው እንዲሁም በፌደራል መንግሥቱ በኩል መፈታት ያለበት የሕዝብን ጥያቄ በፌዴራል በኩል እንዲፈታ የማድረግን ዓላማ የያዘ ነበር።” ሲሉም ጠቁመዋል።
የአማሮ ኮሬ ዞን አስተዳዳሪ ወገኔ ብዙነህ፤ “በዞኑ የጸጥታ ችግር በመኖሩ፣ ችግሩን እስከሚፈታ ድረስ ታገሱንና ውይይት እናደረጋለን የሚል ምላሽ ሰጥተናቸዋል እንጂ፤ የከለከላቸው የለም።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም፤ “የሕዝብ እንደራሴዎቹ ከእኔ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው አላወሩም” ሲሉ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከምክትል አስተዳዳሪው ጋር ተነጋግረው ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡



