መከላከያ ሚኒስቴር አዲስ የተሸከርካሪ ሰሌዳ በአገልግሎት ላይ አዋለ

0
361

ቅዳሜ ነሐሴ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ፤ ለተዋጊ ክፍሉ ግዳጅ አፈፃፀም ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን ቀላል ተሸከርካሪዎች ስታንዳርድ (ሰሌዳ) በማዘጋጀት ለዕዞችና ለክፍሎች የቁልፍ ርክክብ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

መምሪያው የሠራዊቱን አሁናዊ ዝግጁነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡

የተሸከርካሪዎቹን ቁልፍ ለኹሉም ዕዞች እና ለተለያዩ ተዋጊ ክፍል አመራሮች ያስረከቡት የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱራህማን እስማኤል፤ መከላከያ የሠራዊቱን ዝግጁነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉና ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ተሸከርካሪዎችን ማደል መቻሉን ገልጸዋል።በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ሙያተኞች ለንብረቱ ደህንነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እየታየ ያለውን የንብረት አያያዝ ክፍተት በመቀነስ ጥንቃቄ በማድረግ ስምሪት በመስጠትና በመቆጣጠር ማስተዳደር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የነበረውን የተሸከርካሪ ሰሌዳ በአዲስ ሠሌዳ የቀየረ መሆኑን እና ከነሐሴ 25 ቀን 2015 ጀምሮ ተሸከርካሪዎች ላይ በመለጠፍ አገልግሎት መጀመሩን ያበሠሩት ሃላፊው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኹሉም የተቋሙ ተሸከርካሪዎች አዲስ ሰሌዳ እንደሚደርስም ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት የተቋሙ በርካታ ሠሌዳዎች ከተቋሙ እውቅና ወጪ በሌሎች እጅ መገኘቱ ለሕገ-ወጥ ተግባር እንዳይውሉ ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ ሠሌዳው የተቀየረ መሆኑን በመግለጽም፤ አዲሶቹ ሰሌዳዎች አሁናዊ የሠራዊቱን ተልዕኮ እና ግዳጅ መነሻ አድርጎ በሚሰጡት አገልግሎት መሰረት በኮድ ጭምር ተለይተው የተዘጋጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቦታው የተገኙት የኹሉም ክፍል አመራሮችም፤ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ለተግባራዊነቱ ዝግጁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ቁልፍ መረከባቸውን የመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here