በደራ ወረዳ እየተደረገ ባለው ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸው እና በርካቶች መቁሰላቸው ተገለጸ

0
279

እሁድ ነሐሴ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከነሐሴ 22/2015 እስከ ነሐሴ 26/2015 ባሉት ቀናት በተደረገ ግጭት፤ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን እንዲሁም በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የጉንዶ መስቀል ጤና ጣቢያ የሕክምና ባለሙያዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ በኹለቱ ኃይሎች መካከል በተደረገው ባለው ግጭት በተባራሪ ጥይት ተመትተው ከመጡ ሰዎች መካከል አምስቱ ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሰው፤ ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎችም ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለሙያው በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ተጎጂዎች የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ሪፈር መጻፍ አለመቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ “ሕክምና እየተከታተሉ ያሉትም ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው።” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የጎንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪዎች፤ በተለይም ከነሐሴ 22/2015 ወዲህ ያለው የጸጥታ ችግር ተባብሶ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ከአጎራባች የአማራ ክልል መርሐቤቴ እና ሚዳ ከተሞች በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች ወሰን ተሻግረው ወደ ደራ ወረዳ መግባታቸውን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ሥፍራው ያቀና መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ወደ ወረዳው ሲገቡ ቅድሚያ ጎደ ጨፌ፣ ቱቲ እና ቦዶ በተባሉ አካባቢዎች ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ቀጥሎ ወደ ጉንዶ መስቀል ከተማ ማቅናታቸውን ጠቁመዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በተለይም ነሐሴ 22 እና 23/2015 ባደረገው ኦፕሬሽን፤ በወረዳው ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል ከተማ የነበሩ በርካታ የፋኖ ታጣቂ አባላት ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል፡፡

በተያያዘ ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ከጠዋቱ ኹለት ሰዓት አካባቢ ከግንደ በርበሬ፣ ከራቾና ከዕሮብ ገበያ ቀበሌዎች ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል ለገበያ ይጓዙ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች፤ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የወረዳውን የጸጥታ ችግሮች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደራ ወረዳ የጸጥታ ተቋማት በተደጋጋሚ ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አርብ ነሐሴ 26/2015 በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ያለው የጽንፈኞች እንቅስቃሳሴ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ደርሷል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here