በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከአክሱም ከተማ የተሰረቁ ጥንታዊ ቅርሶች እስካሁን አለመገኘታቸው ተገለጸ

0
248

እሁድ ነሐሴ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ)

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከአክሱም ከተማ የተሰረቁ ጥንታዊ ቅርሶች እስካሁን አለመገኘታቸውን የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገብረመድህን ፍጹምብርሃን፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በአክሱም ከተማ የነበሩ በርካታ ቅርሶች መሰረቃቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ቅርሶች ተመርጠው መወሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ተሰርቀው ከተወሰዱት ቅርሶች መካከል አክሱምን ጨምሮ በሩስያ እና ሮም ለመገበያያነት ሲያገለግሉ የነበሩ፣ በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም በውድ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉ፣ 23 ከወርቅ የተሰሩ የከበሩ ሳንቲሞች እንዲሁም በርካታ የብራና መጽሐፍት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

በጥንት ጊዜ ተሰርተው ለመስህብነት ሲያገለግሉ የነበሩ የሸክላ ውጤቶች መሰረቃቸውንና መሰባበራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ አብዛኞቹ የተሰረቁት ቅርሶች በከተማዋ በሚገኘው አርኪዮሎጂ ሙዚየም የሚገኙ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ግኝቶች መሆናቸውንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጦርነቱ ወቅት በአርኪዮሎጂ ሙዚየም ውስጥ የኤርትራ ኃይሎች ምሽግ ሰርተው እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፤ ቅርሶቹ በኤርትራ ኃይሎች ወይም በአካባቢው በነበሩ አንዳንድ ነዋሪዎች ተወስደው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በከተማዋ ሰለተሰረቁት እና ዳብዛቸው ስለጠፋው ቅርሶች ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ሪፖርት የተደረገ ቢሆንም፤ እስካሁን ምንም ዓይነት ተስፋ ሰጭ ነገር አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም፤ “የጠፉት ቅርሶች በግለሰቦች እጅ ላይ ከሆኑ በሚል ከአገር እንዳይወጡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለተለያዩ ተቋማት ያሳወቅን ቢሆንም፤ እስካሁን አንድም የተያዘ ቅርስ የለም።” ብለዋል፡፡

ቅርሶቹን ለማስመለስ የሚደረግ ጥረት አለመኖሩን በመግለጽ፤ “የተሰረቁት ቅርሶች በቱሪስቶች በኩል በጣም ተወዳጅና በአብዛኛው ከአክሱም ከተማ ውጭ ሌላ ቦታ የማይገኙ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።” ሲሉ አሳስበዋል።

በከተማዋ የሚገኘው የአክሱም ሐውልትም ጥገና ካልተደረገለት ሊወድቅ እንደሚችል ኃላፊው አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ በቱሪዝም መስህብነት በቀዳሚነት የምትታወቀው አክሱም ከተማ፤ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በሦስት ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቷ መገለጹ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here