ቅዳሜ ነሐሴ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዘዳንት እና የሱዳን ብሔራዊ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በአገራቸው እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ግጭት የማይቋጭ ከሆነ የሱዳን መፈራረስ አይቀሬ ነው ብለዋል።
ጀነራሉ ይህን ያሉት ሐሙስ ዕለት በፖርት ሱዳን ከተማ ለአገሪቱ የፖሊስ አባላት ባደረጉት ንግግር ሲሆን፤ “ጦርነት ውስጥ ነው ያለነው በፍጥነት መፍትሄ የማይሰጥ ከሆነ ሱዳን ሰሜን ምስራቃዊቷ የአፍሪካ አገር ትፈራርሳለች፡፡” ብለዋል።
የሱዳንን ሕዝባዊ መንግሥት በኃይል አስወግደው ስልጣን የያዙት አልቡርሃን የሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ አገር አቅንተው፤ ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር የሱዳን ግጭት በሚያበቃበት መንገድ ላይ መክረዋል።
ግብጽ ከሱዳን ጦር እና ጀነራሎች ጋር የቆየ ግንኙነት ያላት ሲሆን፤ በባለፈው ወር ውስጥም የሱዳን ጎረቤት አገሮችን ጠርታ በግጭቱ ዙሪያ መክራለች።
ኹለቱ የሱዳን ጦርነት ተፋላሚዎች ዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ እና ሳውዲ አረቢያ በተደጋጋም ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል።
በጀነራል አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር እና በጀነራል መሀመድ ዳጋሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለወራት ከቆየው ውጥረት በኋላ ሱዳን ወደለየለት ቀውስ ገብታለች።
አራተኛ ወሩን ባስቆጠረው የሱዳን ግጭት ከ4 ሺሕ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የገለጸ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከዚህም በእጅጉ የላቀ ነው ይላሉ።
በግጭቱ ሳቢያ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል።



